ሃይማኖት በዳዳን በመግደል የተጠረጠረን ግለሰብ መያዙን ፖሊስ ገለጸ

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጤና ኮሌጅ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ የነበረችው ሃይማኖት በዳዳ በመግደል የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ኢቢሲ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ አንድ ሰዓት በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ በ20ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኝ ደግነት ወርቁ የተባለ፣ የአስራ ሁለተኛ ክፍል የአርባ ምንጭ ነዋሪ ነው ተብሏል።
ተጠርጣሪው ከሟችም ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው የጠቀሰው ዘገባው ግለሰቡ የኤች አይቪ ኤድስ መድኃኒት ለማግኘት ምርመራ ላይ መሆኑን በመግለፅ የጥቁር አንበሳ ሐኪሞች እንዲረዱት በተደጋጋሚ ይመላለስም ነበር ተብሏል።
ሃይማኖት በተገደለችበትም ግንቦት 17፣ 2012 ዓ.ም እንደተለመደው መምጣቱንና በዕለቱ ቢላዋም ይዞ እሷ የነበረችበት የቤተሙከራ ክፍል ክፍት በመሆኑ መግባቱ ተገልጿል።
ተጠርጣሪው ገንዘብ ተቸግሮ እንደነበረና ላፕቶፕ፣ ሞባይል ካገኘም ሰርቆ ለመሸጥ አልሞ ሲዘዋወር እንደነበርና ሃይማኖትንም በዚሁ ምክንያት እንደገደላት ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሃይማኖት በዳዳ በኮሌጁ አስተዳደር ህንፃ ላይ በሚገኘው የላቦራቶሪ ቤተ ሙከራ ክፍል ለምርምር በገባችበት ወቅት የተለያየ የሰውነት ክፍሏ በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተወግቶ ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ/ም ከቀኑ 11 ሰዓት አስከሬኗ መገኘቱን ገልጿል።
ቢቢሲ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት ያናገራቸው የሟች ሃይማኖት በዳዳ ወላጆች በበኩላቸው ለልጃችን ሞት መንግሥት ፍትህ ይስጠን ሲሉ ጠይቀዋል።
ፖሊስ በሃይማኖት በዳዳ ግድያ ተጠርጣሪ ናቸው ያላቸውን አራት ሰዎች በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ትናንት አስታውቆ ነበር።
የሃማኖት ወላጅ አባት አቶ በዳዳ ፈይሳ መንግሥት በልጃቸው ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ወንጀል በማጣራት ተጠያቂዎችን ከሕግ ፊት እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።
የሚፈልጉት ይዘት የለም
በ Facebook ተጨማሪ ይመልከቱቢቢሲ ከሌሎች ድረ-ገጾች ለሚመጡ መረጃዎች ሀላፊነት አይወስድም.የ Facebook ይዘት መጨረሻ
ሃይማኖት ማነች?
የ28 ዓመት ወጣት ሃይማኖት ተወልዳ ያደገችው መተሃራ ከተማ ሲሆን ወላጆች በአሁኑ ወቅት በአዳማ ከተማ ጎሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይኖራሉ።
የሃይማኖት አባት አቶ በዳዳ ፈይሳ ልጃቸው 2009 ዓ.ም ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ በ'ክሊኒካል ፋርማሲስት' በማዕረግ ተመርቃ በዩኒቨርስቲው በመምህርነት ስታገለግል መቆየቷን ያስታውሳሉ። ከዚያም ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመማር ወደ ጥቁር አንበሳ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተልካ ትምህርቷን በመከታተል ላይ እንደነበረች ይናገራሉ።
"2010 ላይ የጀመረችውን የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት የፊታችን ሰኔ ላይ ትመረቅ ነበር። የመመረቂያ ጽሑፏን ለመጨረስ ወደ ትምህርት ቤት እየተመላለሰች ትሰራ ነበር" ይላሉ አቶ በዳዳ።
"ልጄ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ዩኒቨርሲቲ እስክትገባ ድረስ አንድኛ ነበር የምትወጣው" ሲሉ የልጃቸውን ጥንካሬ ያስረዳሉ።

አቶ በዳዳ ልጃቸው በአገሪቱ አለ በሚል ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ በአንዲህ አይነት አሰቃቂ ሁኔታ መገደል እጅጉን እንዳሳዘናቸው ይናገራሉ።
ሃይማኖት ይዛው የነበረው ላፕቶፕ ኮምፒዩተር፣ ሞባይል ስልክ እና እርሳቸው ጽፈው የሰጧት የ5ሺህ ብር ቼክ እንደተወሰደ ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት የጻፉት የ5 ሺህ ብር ቼክ በስም በሚጠቅሱት አንድ ግለሰብ ስም እና የባንክ ቅርጫፍ ወጪ ተደርጓል።
የልጃቸውን መሞት እንዴት ሰሙ?
ሃይማኖት ሰኞ ዕለት ከቤት ወጥታ ወደ ቤት ሳትመለስ ማደሯን እና ስልኳም እንደማይሰራ የሃይማኖት እህት በስልክ እንደነገራቸው አቶ በዳዳ ያስረዳሉ። ምናልባት ጓደኞቿ ጋር አድራ ይሆን ብለው ሲያጠያይቁ ጓደኞቿ ጋር አለማደሯን ተረድተዋል።
በዚህ መካከል ከባንክ ተደውሎ ለሃይማኖት የጻፉት ቼክ ስለመኖሩ መጠየቃቸው እና የጻፉትም ቼክ መጠን በሌላ ሰው ወጪ መደረጉ እንደተነገራቸው አቶ በዳዳ ያስታውሳሉ። ይህ ጥርጣሬ የፈጠረባቸው አቶ በዳዳ ጉዳዩን ለፖሊስ ሪፖርት ለማድረግ መውጣታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ወደ ፖሊስ እያቀኑ ሳለ ለሃማኖት እህት ሰልክ ይደወላል። ስልክ የደወሉት ሃይማኖት የመመረቂያ ጽሑፍ አማካሪ የሆኑት መምህር ሲሆኑ፤ ከእርሳቸው የላብራቶሪ ቁልፍ ወስዳ እንዳልመለሰችላቸው በመናገር ሃይማኖትን ማግኘት እንዳልቻሉ ለእህቷ ይናገራሉ።
እሷም ለመምህሩ ሃይማኖት የት እንዳለች ቤተቡም እንደማይውቅ ከተናገረች በኋላ ወደ ጥቁር አንበሳ መሄዳቸውን ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Marsaalee Hawaasaa
ጥቁር አንበሳ ደርሰው ፖሊስ እስኪመጣ ተጠብቆ የላብራቶሪው በር ሲከፈት የልጃቸው አስክሬን መገኘቱን ተናግረዋል። "ተከፍቶ ሲገባ ልጄ አንገቷ ታርዶ፤ ደሟ መሬት ላይ ፈሶ፤ አስክሬኗ ተገኘ" ይላሉ።
"ልጄም ሆነች እኔ ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የለንም" በማለት ልጃቸው ላይ ይህ አይነት ወንጀል ለምን እንደተፈጸመባት ምንም የሚጠረጥሩት እንደሌለ ይናገራሉ።
የሃይማኖት ወንድም የሆነው ኢንጅነር ታደስ በዳዳ "የእህቴን ደም ያፈሰሰውን ወንጀለኛ መንግሥት ይለይልን" ሲል ጠይቋል።
"ከአሁን በኋላ አባቴ እና እናቴ ሰው የሚሆኑ እንኳን አይመስለኝም። እሷን ማጣታችን ከባድ ሃዘን ውስጥ ከቶናል" ይላል ታደሰ።












