ኮሮናቫይረስ፡ በኮሮና ምክንያት ሁለት ልጆቻቸው ብቻ የቀበሯቸው የአስራ ሁለት ልጆች እናት

የፎቶው ባለመብት, Abiy Mekonen
ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ቤተሰብ፣ ወዳጅ፣ ዘመድ አዝማድ ሲሞት ቀብር ከፍተኛ ትርጉም አለው፤ ሟቾችን የመሸኘት እርም የማውጣትም ሂደት አካል ነው።
በጦርነት፣ በግድያ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት መቅበር ያልቻሉ በርካታ ቤተሰቦች አብዛኛውን ጊዜም ሲባዝኑ "እርሜን ሳላወጣ ቀረሁ" ሲሉም መስማት የተለመደ ነው።
እርምንም ለማውጣት ሐዘን ይደረሳል፤ ሙሾ ይወረዳል፤ በአንዳንድ ባህልም ፀጉራቸውን የሚነጩ፣ የሚላጩ፣ ጥቁር የሚለብሱ፣ አመድ ላይ የሚተኙና ሌሎች የሐዘን መግለጫ የተለያዩ መንገዶችም አሉ።
በሰው ልጅ አኗኗር፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ዘዬ ላይ ስር ነቀል ለውጥ እያስከተለ ባለው የኮሮናቫይረስ ምክንያት ሐዘን መድረስም ሆነ አልቅሶ መቅበር እየቀረ፤ ብዙዎችም ሐዘናቸውን በውስጣቸው አድርገው እየቆዘሙ ይገኛሉ።
ከሰሞኑም በሐገር ፍቅር ቴአትር ታሪክ ውስጥ በ1950ዎቹ ስመጥር ከነበሩ ሙዚቀኞች ጋር እንደሰሩ የሚነገርላቸው ደመቀች አሊዩ ህይወታቸው አልፏል። ደመቀች የአስራ ሁለት ልጆች እናት ቢሆኑም ቀብራቸው ላይ መገኘት የቻሉት ግን ሁለቱ ልጆቻቸው ብቻ ናቸው።
አራተኛ ልጃቸው አብይ መኮንን በኮሮናቫይረስ በተጣለ የጉዞ እገዳ ምክንያት ቀብራቸው ላይ መገኘት አልቻለም። በዳላስ ቴክሳስ ነዋሪነቱን ያደረገው ካፕቴን አብይ የእናቱ ቀብር ላይ መገኘት አለመቻሉ ሐዘን ልቡን እንደሰበረው ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል።
"እነዚህ ሁሉ ልጆች ያሏት እናት የቀበሯት ሁለት ልጆች ናቸው። ለመሄድ ገንዘብም አላጠረም፤ ሄዶ የመቅበርም አቅሙ ነበረን። ነገር ግን መሄድ አንችልም" በማለት ነው ሐዘኑ የፈጠረበትን ግራ የመጋባት ስሜት የሚናገረው አብይ።
"በኢትዮጵያ በሐዘን እርማችንን እናወጣለን። እርም እናወጣለን ስል ሟቾችን ወደ መቃብራቸው እንሸኛለን። በአሜሪካ ለአርባ ዓመታት ያህል ኖሬያለሁ፤ እናም እዚህም አሜሪካ ውስጥ አሜሪካዊ ጓደኞቼ ጋር የቀብር ሥነ ሥርዓትም ሆነ የሐዘን ሥርዓትም ላይ ተገኝቻለሁ። ቀብር ላይ አስከሬኑን ተሰናብተው ነው የሚሄዱት። እኛ ግን ሟቾች ወደ ጉድጓድ ሲገቡም ሆነ ሲቀበሩ እናያለን። እናታችን አለመቅበራችን፤ በጣም ልብ የሚሰብር ነገር ነው" በማለትም ይናገራል።
ወንድሙ የሥርዓተ ቀብሩን ሂደት እንዲቀርፁ በቀጠራቸው ግለሰቦች አማካኝነት ቪዲዮ እንዲሁም ፎቶዎች ተልከዋል። አብይም የሚወዳቸው እናቱን ቀብር በቪዲዮ እንዲሁም በፎቶዎች ተመልክቷል።
"አንድ የቅርብ ጓደኛዬ የሐዘን ሥነ ሥርዓቱን በዙም ለምን አናካሂደውም የሚል ሃሳብ አመጣ። እናም አራት መቶ ያህል ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ወዳጅ በተሳተፉበት የእናታችንን የሐዘን ሥነ ሥርዓትን በዙም አካሄድን። ፀሎትም አደረግን። መቼም የልባችንን ሐዘን ትንሽ ቀለል አደረገልን። የምናውቃቸውን ሰዎች በአንድ ላይ መሰባሰብ በመቻላችን አንድ ላይ ሐዘናችንን ለመወጣት ሞከርን።"
የሚለው አብይ እናቱ ቀብር ላይ አለመገኘቱ ልቡን እንዴት እንደሰበረው፤ ከዘመድ፣ አዝማድ ከቤተሰብ ወዳጅ ጋር ተሰባስቦ እርም አለማውጣት፤ አብሮ አለማልቀሱም የፈጠረበትን ውስጣዊ ሐዘንም ለቢቢሲ አጋርቷል።
"እናታችንን የሚያውቋት ሰዎችም በዙም አማካኝነት ተገኝተው ነበር። በተቻለም እርማችንን ለማውጣት ሞከርን። የቤተ ክርስቲያን አባላትም መጡ። ከቤታችንም ፊት ለፊት ተገኝተው አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው በተቻለ መጠን ዘክረዋታል። በተቻለ መጠን የቻልነውን ለመድረግ ሞክረናል። ሆኖም ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምናደርገው ከልባችን ተላቅሰን ሊወጣልን አልቻለም" ብሏል።














