ኮሮናቫይረስ፡ በሞት የተደመደመው የልደት በዓል

የፎቶው ባለመብት, Family album
ዓለም በዚህ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ከተከሰቱ ነገሮች ታገግም ይሆን? "ያ ክፉ ወቅት" ተብሎስ ይወራለት ይሆን?
ማን ያውቃል? ይሆን ይሆናል።
በብራዚል እንዲህ ሁኔታው ሳይከፋ ልደት ለማክበር የተሰባሰቡት ቤተሰቦች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሦስት አባላታቸውን በሞት ተነጥቀዋል።
የልደት በዓሉ አከባበር በሞት ይደመደማል ብለው ያላሰቡት ቤተሰቦች እዝንም አላወጡም፣ ሃዘናቸውን ለብቻቸው በቤታቸው ይዘው የእግር እሳት ሆኖባቸዋል።
ከሦስቱ የቤተሰብ አባለት መቀጠፍ በተጨማሪ አስሩ ደግሞ መታመማቸውን የብራዚል ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የልደት አከባበሩሽርጉድ
የልደቱ በዓል በሳኦፖሎ በምትገኘው ኢታፔሪካ ዴ ሴራ ከተማ ነበር መጋቢት 4/2012 ዓ.ም።
በዚያን ወቅት በብራዚልም በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር እንደ ዛሬው በመቶ ሺህዎች አልነበረም፤ ገና 98 ነበር።
የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ሞትም አልተከሰተም።
በወቅቱም በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 60ዎቹ በዓለማችን ከፍተኛ ሕዝብ ይኖርባቸዋል ከሚባሉት ከተሞች መካከል አንዷና የ21 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ በሆነችው ሳኦ ፖሎ ነው።
ከሦስት ሳምንታት በኋላ መጋቢት 30/2012 ዓ.ም በብራዚል በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 16 ሺህ ያህል ደረሰ፤ 800 ዜጎቿንም አጣች።
ቬራ ሉሺያ ፔሬራ የኮሮናቫይረስ ብራዚል መግባቱንና እየተስፋፋም መሆኑን ታውቃለች። 59ኛው የልደት በዓሏን ለማክበር ሽር ጉድ እያሉ በነበረበት ወቅት፤ እንዲያውም "ልደቴ ባይከበርስ?" የሚል ሃሳብም ብልጭ ብሎላት ነበር።
"ጥርጣሬዎች ነበሩን፤ ሆኖም አይ እናክብር በሚል ገፋንበት" ትላለች።
በወቅቱም በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ባለመኖራቸው እንዲሁም አገሪቱም አስገዳጅ ቤት ውስጥ የመቀመጥ አዋጅም ካለማውጣቷ አንፃር ጥርጣሬዎች ቢኖሩም የከፋ ይሆናል ተብሎ አልታሰበም ነበር።
28 የቤተሰብ አባላት የተሳተፉበት የልደት በዓል
ቀኑም ተቆረጠ በግቢዋ ውስጥ በሚገኘው ጓሮ ውስጥ 28 የቤተሰብ አባላቱ ተሰባሰቡ።
ለልደቷ ከተጋበዙትም መካከል የባለቤቷ ፖውሎ ቪየራ ወንድምና እህት ይገኙበታል።
ፓውሎ ከወንድሙ ክሎቪስና ከእህቱ ማሪያ ጋር ሆነው ነገ አማን ይሆናል በሚል ተስፋም ልደት እያከበሩ ነበር።
በኮሮናቫይረስ ተይዘን እንሞታለን የሚል ሃሳብ በጭራሽ አልታያቸውም።
ቬራ ሉሺያም እህቶቿን፣ የእህቶቿን ልጆች እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቿንም ጠርታ ነበር።
ቤቱም በቤተሰቡ ሳቅ ደስታ ደመቀ፤ "መልካም ልደት" ብለው ለቬራ ዘመሩላት፤ በዓመቱም አብረን እናከብራለን ብለው ቃል ገቡ።
ስለነገው ተስፋ የተደረገውና የተገባውን ቃል እውን ስለመሆኑ ማን ያውቅ ይሆን?
ከቬራ ልደት ጥቂት ቀናት በኋላም ግማሹ እንግዳ የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን ሳል፣ ትኩሳትና ትንፋሽ ማጠር ያሳዩ ጀመር።
የአብዛኛዎቹ መካከለኛ የሚባል ምልክት ስለነበር ወደጤና ማዕከላት መሄድ አላስፈለጋቸውም።
ነገር ግን የቬራ ባለቤት እንዲሁም ወንድምና እህቱ በሳምንቱ ህይወታቸው አለፈ።

የፎቶው ባለመብት, Family album
ሁሉም የሞቱት በኮቪድ-19 ነው ቢባልም የቬራ ባለቤት እህት ማሪያ አሟሟት ግን በኮሮናቫይረስ መሆኑ ተረጋግጧል።
ልጇ ራፋኤላ ለቢቢሲ እንደተናገረችው "እናቴ በኮሮናቫይረስ መሞቷን እርግጠኞች ነን" ብላለች።
"በሽታው ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ያሳያል። ምንም እንኳን እናቴ ሆስፒታል ሄዳ ቬንትሌተር ቢገጠምላትም ህይወቷን ማትረፍ አልቻሉም" ብላለች።
እናቷ ማሪያ የስኳር ህመም ያለባት ሲሆን የጤናቸውም ሁኔታ ያሽቆለቆለው ከልደቱ ጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
ቤተሰቡ አሁንም ቢሆን የፓውሎና ክሎቪስን የምርመራ ውጤት እየጠበቀ ነው።
"ያዩዋቸው ዶክተሮች ኮቪድ-19 መሆኑን 99 በመቶ እርግጠኛ ናቸው" በማለት ቬራ ሉሺያ ተናግራለች።
የተረፈው ልጅ
ቬራ ሉሺያ ምንም እንኳን እሷም ሆነ ልጇ የኮሮናቫይረስ ምልክት ታይቶባቸው የነበረ ቢሆንም ሁለቱም አገግመዋል።
"አካላዊ ሁኔታዬ ደህና ነኝ፤ ትንሽ ሳል ብቻ ነው ያለብኝ። ነገር ግን ፈታኝ የሚባል ወቅት ላይ ነን ያለነው። በሽብር ውስጥ እየኖርን ነው" ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, Family album
እንዴት ይታመናል?
በመጀመሪያ ሁሉም የቤተሰብ አባላት በኮሮናቫይረስ እንጠቃለን የሚል ስጋት አልነበራቸውም።
"በወቅቱ በብራዚል በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በጣም ጥቂት ነበረ። ቫይረሱ እኛ ላይ ይደርሳል ብለን አላሰብንም። ገና በርቀት ላይ ነው ያለው ብለን ገምተን ነበር" በማለት ከተረፉት አንዱ ገልጿል።
በፓርቲው ላይ የነበሩት በሙሉ ጤንነታቸው ደህና ይመስል ስለነበር፤ ማን በቫይረሱ እንደተያዘ ለመገመት ፈጽሞ አይቻልም።
"ለነገሩ አሁን ማን መጀመሪያ እንደተያዘ ማወቅ አለማወቁ ምንም የሚቀይረው ነገር የለም" ብሏል።
ማሪያ ከሞተች በኋላ የ62 ዓመት ወንድሟ ክሎቪስ የጤናው ሁኔታ እየከፋ መጣ።

የፎቶው ባለመብት, Family album
"ከልደቱ ሦስት ቀናት በኋላ አባቴን በከፍተኛ ሁኔታ ያስለው ጀመር" በማለት የክሎቪስ ልጅ አርተር ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ራስ ምታት እንዲሁም ከፍተኛ ትኩሳት ነበረው። ከዚያም በተጨማሪ የማሽተት እንዲሁም የመቅመስ ስሜቱንም ሙሉ በሙሉ አጥቶ ነበር።"
ከእህቱ ማርያ በተቃራኒ ክሎቪስ ምንም አይነት ተደራራቢ ህመም አልነበረበት። ህመሙ ሲብስበትም አርተር አባቱን ወደ ህክምና ማዕከል መውሰድ እንዳለበት ተረድቶ ቢወስደውም ሆስፒታሉ ወደ ቤቱ መለሰው።
"ዶክተሮቹ በጭራሽ ኮሮናቫይረስ ነው ብለው አላሰቡም" ብሏል።
በፅኑ ህክምና ላይ
የቬራ ሉሺያ ባለቤት ፓውሎም ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ነው የተነገረው።
ከዚህ ቀደም በየቀኑ ስፖርት ይሰራል እንዲሁም ተራራ ይወጣም፣ ብስክሌትም ይነዳ ስለነበር ሲታይ ደህና ነበር።
ፓውሎም ሆስፒታል በገባበትም ወቅት ጤናውን ሲገመግሙት ደህና እንደሆነና የትንፋሽ ማጠር አጋጥሞኛል ማለቱንም ባለቤቱ ትናገራለች።
"ከሁለት ቀናት በኋላ ፅኑ ህሙማን ክፍል ገባ" በማለት ያልተጠበቀችው እንደሆነ ቬራ ታስረዳለች።

የፎቶው ባለመብት, Family album
ሁለቱ ወንድማማቾች ክሎቪስና ፓውሎ ከህፃንነታቸው ጀምሮ የማይነጣጠሉ ነበሩ፤ በሞትም አልተነጣጠሉም።
መጋቢት23/2012 ዓ.ም ማሪያ ስትሞት በተከታዩ ቀን ክሎቪስ እንዲሁም መጋቢት 25/2012 ዓ.ም ፓውሎ ይህችን ዓለም ተሰናብተዋል።
በኮሮናቫይረስ መሞታቸው ለተረጋገጡ ወይም ለተጠረጠሩ ሰዎች በሚደረገው የቀብር ሥነ ሥርዓት መሰረት ማሪያና ፓውሎ በተዘጋ የሬሳ ሳጥን ተቀብረዋል።
ክሎቪስ ለቤተሰቦቹ በተናዘዘው መሰረት አስከሬኑ ተቃጥሏል። የሦስቱም የቀብር ሥነ ሥርዓት የተፈፀመው በተለያዩ ቀናት ነው።
የሐዘኑ ሥነ ሥርዓትም ከጥቂት ደቂቃዎች እንዳያልፍ በተሰጠ መመሪያ መሰረት ከአስር ያነሱ ሰዎችም ብቻ ሐዘናቸውን ውጠው ተሰናብተዋቸዋል።
በልደቱ ቀን ታድመው የተረፉት ደግሞ ራሳቸውን ለይቶ ማቆያ ውስጥ ያስገቡ ሲሆን፤ ኡን ሁሉም አገግመዋል ማለት ይቻላል።
በአሁኑ ሰዓት ሁሉም "እኛን ያየ ይቀጣ" እያሉ ነው። ቸልተኝነት እንደማያስፈልግ እንዲሁም በተቻለ መጠን ቤት ውስጥ ሰዎች እንዲቀመጡም እየመከሩ ነው።
'ጄይር ቦልሶናሮ የማይረቡ ነገሮችን ይቀበጣጥራል'
የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ጄይር ቦልሶናሮ አካላዊ ርቀት የመጠበቅ ሕጎች ላይ ሲዘባበቱ እንዲሁም ህመሙንም "ቀላል ጉንፋን" ነው በማለት በማጣጣላቸው አወዛጋቢ ሆነዋል።
የፕሬዚዳንቱም ድርጊት እንደ ቬራ ሉሺያ ላሉት ብዙ ህመም ለተሸከሙ እንዲሁም ቤተሰብ ላጡ ሰዎች ከመጠን በላይ የሚያበሳጭም ነው።
"ጄይር ቦልሶናሮ የማይረቡ ነገሮችን ይቀበጣጥራል። በስልጣን ላይ ያለ ሰው እንደመሆኑ መጠን ያለበትንም ኃላፊነት ልብ ሊል ይገባል" ብላለች።
በአሁኑ ጊዜ ለቬራ ፈታኙ ነገር ያለ የህይወት አጋሯ በብቸኝነት ህይወትን መግፋቱ ነው።
"ምንም ቢፈጠር ያው እንኖራለን። ማንኛውም ቤተሰብ የእኛ እጣ ፈንታ እንዲያጋጥመው አልፈልግም" በማለትም በሐዘን ተናግራለች።













