ኮሮናቫይረስ፡ ዓለም ‘ከኅዳር በሽታ’ በኋላ ምን መሰለች? ከወረርሽኙስ ምን እንማራለን?

እአአ በ1920 የጃፓን ልጃገረድ የአፍና አፍንጫ መሸፈና አድርጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ‘ስፓኒሽ ፍሉ’ የተሰኘ ወረርሽኝ ተከስቶ ነበር። በኢትዮጵያውያን ዘንድ ‘የኅዳር በሽታ’ በሚል የሚታወቀው ወረርሽኝ ለ‘ኅዳር ሲታጠን’ ልማድ መነሻ ምክንያትም ነበር።

‘የወረርሽኞች ሁሉ እናት’ በሚል የሚጠራው ይህ ወረርሽኝ በሁለት ዓመት ብቻ ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ሕይወት ቀጥፏል።

ያኔ የዓለም ሕዝብ 1.8 ቢሊዮን ነበር። ከሕዝቡ አንድ ሦስተኛው በወረርሽኙ ተይዞ እንደነበር ተመራማሪዎችና የታሪክ አጥኚዎች ይናገራሉ።

ወረርሽኙ ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በላይ ሰዎችን ገድሏል።

ዓለም በኮቪድ-19 ጭንቅ ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት፤ ወደ ኋላ መለስ ብለን ከ‘ስፓኒሽ ፍሉ’ በኋላ ምድር ምን ትመስል እንደነበር ቃኝተናል።

ወረርሽኝ ሳይንስ ባልተራቀቀበት ዘመን

ያኔ ሳይንስ እንደዛሬው አልተራቀቀም ነበር። በሽታ መከላከልም ቀላል አልነበረም።

ሐኪሞች ‘የኅዳር በሽታ’ ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ቢያውቁም፤ የበሽታው መንስኤ ባክቴሪያ እንጂ ቫይረስ መሆኑን አልተገነዘቡም ነበር።

በወቅቱ የሕክምና አገልግሎትም ውስን ነበር። ፀረ እንግዳ አካላት (አንቲባዮቲክ) የተገኘው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1928 ነበር።

ለጉንፋን ክትባት የተገኘው ደግሞ በ1940ዎቹ ነው።

ያኔ ዓለም አቀፍ የጤና ሥርዓት ማዕቀፍ አልነበረም። ሀብታም በሚባሉ አገራት ሳይቀር የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ እንደ ቅንጦት ይቆጠር ነበር።

‘ስፓኒሽ ፍሉ ዓለምን እንዴት ለወጠ’ በሚል መጽሐፍ ያሳተሙት ፔል ራይደር፤ ያኔ ኢንዱስትሪ በተስፋፋባቸው አገራት ሐኪሞች የእራሳቸው ቅጥረኛ ነበሩ ይላሉ። ሐኪሞች በተራድኦ ድርጅቶች ወይም በሐይማኖት ተቋሞችም ይደገፉ ነበር።

በዘመኑ አብዛኛው ማኅበረሰብ ሐኪም አያገኝም።

በወረርሽኙ ወቅት የነበረ ጊዜያዊ ሆስፒታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ወረርሽኙ ከፍተኛ ቁጥር ያለቸውን ወጣቶች በመግደሉ የተለየ ነበር

‘የኅዳር በሽታ’ ከዚያ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ነበር ጉዳት ያስከተለው። በብዛት የሞቱት ከ20 ዓመት እስከ 40 ያሉ ናቸው።

ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት የተመለሱ ወታደሮች ይኖሩበት በነበረ ማቆያ ውስጥ እንደተቀሰቀሰ የሚታመነው ይህ ወረርሽኝ፤ በዋነኛነት ያጠቃው ወንዶችን ነበር።

ድሃ አገሮችም በግንባር ቀደምነት ተጎድተዋል።

ዘንድሮ በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የተሠራ ጥናት፤ በስፓኒሽ ፍሉ 550 ሺህ አሜሪካውያን (ከአጠቃላይ ሕዝቡ 0.5 በመቶው) እንዲሁም 17 ሚሊዮን የህንድ ዜጎች (ከአጠቃላይ ሕዝቡ 5.2 በመቶው) መሞታቸውን ያሳያል።

የጥናቱ መሪ ሮበርት ባሮ፤ በሽታው ምጣኔ ሀብትን አሽመድምዶት ነበር ይላሉ። አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ስድስት በመቶ ያሽቆለቀለበት ዘመን መሆኑንም ይጠቅሳሉ።

“የመጀመሪያው የዓለም ጦርነትና ወረርሽኙ ተደማምረው የዓለምን ምጣኔ ሀብት እንዳልነበረ አድርገውታል” ሲሉም ያስረዳሉ።

የቤተሰቦቻቸውን ንግድ የሚረከቡ፣ የሚያርሱ፣ ባቡር የሚነዱ፣ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ወጣት ወንዶች በብዙ አገራት አልቀዋል።

“በወቅቱ የወንዶች ቁጥር መቀነሱ ሴቶች የትዳር አጋር እንዳያገኙ አድርጓል” ይላሉ ሮበርት።

ሴቶች ብሪታኒያ ውስጥ ባለ አንድ ፋብሪካ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በርካታ ወንዶች በመጀመሪያው የዓለም ጦርነትና በወረርሽኙ በመሞታቸው ሴቶች በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩ በር ተከፈተ

“በአገሬ የሴቶች መብት ትግል ወረርሽኙ ሚና እንደነበረው ማስረጃ አለ”

ወረርሽኙ በወንዶችና በሴቶች መካከል የነበረውን የጾታ ሚዛን ለውጧል።

የቴክሳስ ዩኒቨርስረቲ አጥኚ ክርስቲን ብላክበር እንደሚሉት፤ አሜሪካ ውስጥ ወንድ ሠራተኞች በወረርሽኙ በመሞታቸው ምክንያት ሴቶች በተለያዩ መስኮች መሰማራት ጀምረዋል።

በ1920 ሴቶች ከአገሪቱ ሠራተኞች 21 በመቶውን ይሸፍኑ ነበር።

ያ ዓመት ሴቶች እንዲመርጡ የሚፈቅድ ሕግ የፀደቀበትም ነው። በቂ የሠራተኛ ኃይል አለመኖሩ የሴቶች ደሞዝ (ከ21 ሳንቲም ወደ 56 ሳንቲም) ከፍ እንዲልም አድርጓል።

“በአገሬ የሴቶች መብት ትግል ወረርሽኙ ሚና እንደነበረው ማስረጃ አለ” ይላሉ ተመራማሪዋ።

በወቅቱ የተወለዱ ሕፃናት ከወርሽኙ በፊት ከተወለዱት በበለጠ በልብ ህመም ይያዙ እንደነበር ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።

ወረርሽኙ የፈጠረው ጭንቀት የእናቶች ጤና ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ መላ ምቶች አሉ።

በዘመኑ የተወለዱ ወንዶች ከሌሎች በአንድ ሚሊ ሜትር ያጥሩ እንደነበረ አሜሪካ ውስጥ የተሠራ ጥናት ይጠቁማል።

ጋንዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከወረርሽኙ በኋላ ጋንዲና ሌሎች የነጻነት ታጋዮች ድምጽ ጎልቶ መሰማት ጀመረ

ፀረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ

በ1918 ህንድ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ከወደቀች አስር ዓመት አልፎ ነበር።

ወረርሽኙ ህንድ ውስጥ ከእንግሊዞች በላቀ ህንዳውያንን ጎድቶ ነበር። የሚገለሉ የሂንዱ ማኅበረሰቦች የሞት መጠን በአንድ ሺህ ሰው 61.6 እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ።

እንግሊዞች በሽታውን ለመቆጣጠር ተገቢውን እርምጃ እንዳልወሰዱ የህንድ ብሔርተኞች ይናገራሉ።

በ1919 በታተመው መጽሐፋቸው ማኅተመ ጋንዲ የእንግሊዝን አስተዳደር ኮንነዋል።

በሌላ በኩል በሽታው በመላው ህንዳውያን ዘንድ ብሔራዊ ትብብርን ፈጥሯል።

ያኔ የዓለም ጤና ድርጅት የተቋቋመው ከተባበሩት መንግሥታት በፊት በነበረው ሕብረት አማካይነት ሲሆን፤ በሐኪሞች በመመራት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መቆጣጠሪያ መንገዶችን ይቀይስ ነበር።

አሁን ያለው የዓለም ጤና ድርጅት የተመሰረተው በ1948 ነው።

ሐኪም ህጻን ልጅን ሲመረምር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በርካታ አገራት ከወረርሽኙ በኋላ የጤና ሚኒስቴራቸውን አጠናከሩ

ብረተሰብ ጤና ምርምር መሻሻል

ወረርሽኙ በኅብረተሰብ ጤና ዘርፍ ለሚሠሩ ምርምሮች መነሻ ሆኗል።

በ1920 ሩስያ ኅብረተሰቡን ያማከለ የጤና ሥርዓት በመመስረት ግንባር ቀደም ሆናለች። ሌሎች አገራትም ተከትለዋት የጤና ሚንስቴር ማቋቋም ጀምረዋል።

አንትሮፖሎጂስቷ ጄኔፈር ኮል እንደሚናገሩት፤ ወረርሽኙ እና የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ለአቅመ ደካሞች ከለላ የሚሰጡ ተቋሞች እንዲመሰረቱም አስችለዋል።

“ብዙ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ የትዳር አጋራቸውን በሞት የተነጠቁም ነበሩ” ይላሉ።

በዚያን ዘመን የተነሳውን ‘የኅዳር በሽታ’ ለመቆጣጠር አካላዊ ርቀት መጠበቅን የተገበሩም ነበሩ።

የአሜሪካዋ ፊላዴልፊያ ግዛት አንድ የአደባባይ መሰናዶ ስታካሂድ ሴንት ልዊስ ግዛት ግን ለመሰረዝ ወስና ነበር። ይህ በሆነ በወሩ በፊላዴልፊያ 10 ሺህ ሰዎች ሲሞቱ፤ ሴንት ልዊስ ግን ያጣችው 700 ሰዎችን ብቻ ነበር።

አጋጣሚው በሽታው ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ መራራቅ አስፈላጊ መሆኑን አስተምሮ አልፏል።

ቴአትር ቤት፣ ትምህርት ቤት፣ ቤተ ክርስቲያንና ሌሎችም ሕዝብ የሚበዛባቸውን ቦታዎች የዘጉ ግዛቶች በአንጻራዊነት ጥቂት ሰው የሞተባቸው ሆነዋል።

በ1918 ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ የጣሉ ግዛቶች በቶሎ ምጣኔ ሀብታቸው እንዳገገመ የፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።

ወረርሽኙ 700 ሺህ አሜሪካውያንን የገደለው የእንቅስቃሴ ገደብ መነሳት ከነበረበት ጊዜ ቀድሞ በመነሳቱ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሮበርት ባሮ እንደሚሉት፤ ለ12 ሳምንታት የቆየ የእንቅስቃሴ ገደብ ቢጣል ኖሮ የሟቾችን ቁጥር መቀነስ ይቻል ነበር። ሆኖም በነዋሪዎች ግፊት ምክንያት ገደቡ ያለ ጊዜው ተነስቷል።

በኮቪድ-19 ወቅትም ተመሳሳይ ነገር እየተስተዋለ መሆኑን ባለሙያው ያስረዳሉ።

በርካታ ሕዝብ ካሊፎርኒያ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከመቶ ዓመት በፊትም ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ ይመከር ነበረ

የተረሳው ወረርሽኝ?

‘የኅዳር በሽታ’ ብዙ ነገር አስተምሮ ቢያልፍም ከሞላ ጎደል ተዘንግቷል።

በዚያን ዘመን የአሜሪካ እና የእንግሊዝ መሪዎች በበሽታው ተይዘው ነበር። የብራዚል ፕሬዘዳንትም የሞቱት በወረርሽኙ ሳቢያ ነበር።

ሆኖም ግን የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወረርሽኙን ሸፍኖታል። የዓለም መንግሥታት መገናኛ ብዙሃን ስለ በሽታው እንዳይዘግቡ ማዕቀብ መጣላቸው ደግሞ በቂ ሽፋን ላለማግኘቱ ምክንያት ነው።

ስለወረርሽኙ በተለያዩ ባህሎች በስፋት ሲወራ በታሪክ መጻሕፍት ሲጠቀስም አይስተዋልም።

የህክምና ታሪክ አጥኚው ማርክ ሆንግስቡም እንደሚናገሩት፤ በወረርሽኙ ሕይወታቸውን ላጡ መታሰቢያ አይደረግም፤ መስዋዕትነት የከፈሉ ሐኪሞችና ነርሶች የሚታወሱትም በጥቂት መቃብር ስፍራዎች ነው።

“ስለ 1918ቱ ወረርሽኝ ብዙ ልብ ወለዶች፣ ዘፈኖች እና ሥዕሎችም የሉም” ይላሉ።

በ1924ቱ ‘ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ’ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተከሰቱ የማይረሱ ሁነቶች ዝርዝር ውስጥ ወረርሽኙን አልተካተተም።

‘ስፓኒሽ ፍሉ’ ወይም ‘የኅዳር በሽታ’ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወሳበት የታሪክ መጽሐፍ የወጣው በ1968 ሲሆን፤ የኮቪድ-19 ስርጭት ደግሞ የያኔው በሽታ አሁን እንዲታወስ ምክንያት ሆኗል።

ኮሮና
Banner