ኮሮናቫይረስ፡ በአማራ ክልል የትምህርት ቤቶች መዘጋትን ተከትሎ ያለዕድሜ ጋብቻዎች መጨመራቸው ተገለፀ

ያለ ዕድሜ ጋብቻ

የፎቶው ባለመብት, Eric Lafforgue/Art in All of Us

በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ ያለ እድሜ የሚደረጉ ጋብቻዎች እየጨመረ መሆኑ ተገልጿል።

ያለ እድሜ ጋብቻ እየጨመረ ስለመሆኑ መረጃው አለን ያሉት የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሠላማዊት አለማየሁ በተለይም በአንዳንድ ዞኖች ላይ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን አስረድተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም መረጃዎች ይሰበሰቡ የነበረው በዋነኝነት በትምህርት ቤቶች እና ድግሶች ቢሆንም፤ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ተማሪዎች እና መመህራኖች ስለማይገናኙ እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድግሶች እንዳይከናወኑ በመከልከሉ ምክንያት መረጃ ለማግኘት እንደተቸገሩ አስታውቀዋል።

ስለዚህ የተሻለ አማራጭ በመጠቀም ከኮሮናቫይረስ ግብረ ኃይል ጋር በመጣመር ቤት ለቤት በሚደረጉ አሰሳዎች ጥቆማዎች እየደረሷቸው መሆኑንም ምክትል ኃላፊዋ ገልፀዋል።

በጥቆማዎቹ መሠረት መሠርት በደቡብ ጎንደር እና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች የተንሰራፋ ችግር እንዳለም መረዳታቸውን ገልፀዋል።

"በደቡብ ጎንደር ስማዳ፣ ታች ጋይንት እና ፎገራ ወረዳዎች ላይ ሰፊ የልጅነት ጋብቻን እየተካሄደ እንደሆነ መረጃዎች አሉ። ምስራቅ ጎጃምም በተመሳሳይ ሸበል በረንታ ደባይ ጥላት እና ጎዛምን ወረዳዎች ላይ ሰፊ እንቅስቀሴ አለ" ብለዋል።

በደባይ ጥላት ወረዳ የሚገኘው የአጋምና የ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት መምህር ደሣለኝ ቢተው ቀደም ሲል አልፎ አልፎ የነበረው የልጅነት ጋብቻ ትምህርት ቤት በመዘጋቱ በከፍተኛ ደረጃ እየተካሄደ ነው ሲሉ ለቢቢሲ አስታውቀዋል።

"ቀደም ሲል በተማሪዎች በኩል መረጃ ይሰባሰብና ከህጻናት እና ወጣቶች ቢሮ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን ጋብቻዎቹ ይቋረጡ ነበር። አሁን ግን መረጃ ማግኘት ባለመቻላችን የልጅነት ጋብቻ እየተካሄደ ነው ያለው። አሁን መረጃ ብዙም አናገኝም ህጻናት እና ተማሪዎች ነበሩ የሚነግሩን አሁን ግን አናገኝም" ብለዋል መመህር ደሣለኝ።

በደባይ ጥላት ወረዳ የልጅነት ጋብቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው ያለው ያሉት ወረዳው የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ነጻነት ዘለቀ ለቁጥሩ መጨመር አንደናው ምክንያት ህብረተሰቡ ውስጥ ያለው "የአመለካከት ክፍተት" መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የትምህርት ቤቶች መዘጋትን ተከትሎ በልጅነት ጋብቻ ዙሪያ መረጃ ማግኘት አለመቻል ሌላው ተጽዕኖ የፈጠረ ጉዳይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በየትኛዎቹ የወረዳው አካባቢዎች የልጅነት ጋብቻ እንደሚበዛ ተጠይቀው ሲመልሱም በደባይ ጥላ ወረዳ በሚገኙ "ደጋማ ቀጠናዎች አካባቢ" መሆኑን አስረድተዋል።

በአማራ ክልል ከሶስት አመታት በላይ ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቀረት እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ሠላማዊት በበኩላቸው በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2019 ብቻ ከ5800 በላይ የልጅነት ጋብቻ የተሰረዘው ብለዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን የተሠማራው ግብረ ሃይል በዞኑ ከ1280 ሠርጎች መታቀዳቸውን አስታውቋል። ከእነዚህ መካከል "541 የልጅነት ጋብቻን ብለን የምንጠራቸው ናቸው" ብለዋል።

እነዚህ ለማስቆም ጥረት መደረጉን አስታውቀው በ46 ግለሰቦች ላይም ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

"በዞኑ ውስጥ ከፍተኛውን የሚይዘው የደባይ ጥላት ወረዳ ነው። 255 የልጅነት ጋብቻን ያላነሱ ሊፈጸሙ የነበረው። 221 ተቋርጧል 34 እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተደርጓል። ሌሎችም ዞኖች ላይ ተመሳሳይ ነገር እንዳለ ለመገምገም ሞክረናል። ሰፊ ግን እነዚህ ሁለት ዞኖች [ በደቡብ ጎንደር እና ምስራቅ ጎጃም] ላይ ነው እያየን ያለነው" ብለዋል።

ጋብቻው በስነልቦና እና በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር መምህር ደሣለኝ ገልፀው "ስነልቦና ተጽዕኖ በህጻናት ላይ ያደርሳል። በእኛም የመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ በትዳራቸው መዝለቅ እና የተማሪዎች ቁጥር መቀነስ እና ተማሪዎች የትምህርት ማቆራረጥ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በልጆች ላይም ፊስቱላ ሊከሰት ይችላል" ሲሉ አስረድተዋል።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው እና የሰዎች መሰብሰብ መከልከሉ የልጅነት ጋብቻውን ለመቆጣጠርም እንቅፋት ሆኗል።

ለዚህ መፍትሔ የሚሆነው ግንዛቤ መፍጠር መሆኑን የሚገልጹት ወይዘሮ ነጻነት የተገኙትን አጋጣሚዎችን በሙሉ እንደሚጠቀሙ አስታውቀዋል።

ወይዘሮ ሠላማዊት በበኩላቸው "የመጀመሪያው ቤተሰቦችን ትክክል አለመሆናቸውን ማሳየትና ማረም ነው። ከዚያ ሲያልፉ በህግ እርምጃ ይወሰዳል። በህግ የተቀመጠ ቅጣት አለ። 3-25 ዓመት ቅጣት አለ። ከፍትህ አካላት ጋር እርምጃ እየተወሰደ ነው" ብለዋል።

ኮሮና
Banner