ፕሬዝደንት ኢሳያስ በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለምን አስፈለጋቸው?

የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች

የፎቶው ባለመብት, @PMAbiyAhmedAli

የኤርትራው ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ፤ አማካሪዎቻቸውን አስከትለው ባለፈው እሁድ ለሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይታወቃል።

ፕሬዝደንቱ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የዓለም አቀፍ ስጋት ስለሆነው ኮቪድ-19 እና የምስራቅ አፍሪካ አገራት ትልቅ ስጋት የሆነው የአንበጣ መንጋ ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመወያየት እንደሆነ ተገልጿል።

ፕሬዝደንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በመሆን በኦሮሚያ ክልል የባቱ ዱግዳ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት መርቀዋል።

ከሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነት በኋላ፤ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የልማት ፕሮጀክቶች ሲመርቁ እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምረቃ ላይ መታየታቸው፤ በአገራቸው በአደባባይ የልማት ፕሮጀክቶችን ሲያስመርቁ አሊያም ከተመራቂ ተማሪዎች ጋር ሲታደሙ ብዙ ባላስተዋሏቸው ዜጎቻቸው እንዲነቀፉ አድርጓቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የፕሬዝደንቱ ጉዞ የዓለም አገራት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ድንበራቸውን ዘግተው፣ የሰዎች እንቅስቃሴ ገድበው፣ በአየርም ሆነ በመንገድ ከቦታ ቦታ የሚደረግ ጉዞን በመሰረዝ አገራዊና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሚገናኙበት ወቅት መሆኑም፤ እውን የፕሬዝደንት ኢሳያስ ጉዳይ ኮቪድ-19 እና የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ነው? የሚል ጥያቄን አጭሯል።

ኤርትራዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አቶ ደስበለ መሃሪ ኑሯቸው በጣሊያን አገር ሚላን ከተማ ነው።

ጣልያንን እጅጉን የፈተነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፤ ህብረተሰቡ ላይ ያደረሰው ከባድ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና በቅርብ አይተው፤ ደንግጠዋል። በዚህ ወቅት ፕሬዝደንት ኢሳያስ ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉዞ "ታሪካዊ ስህተት" በማለት ይተቹታል።

አቶ ደስበለ "በእውነቱ ይህ ጉዞ አስገራሚ ነው፤ ሁሉም ነገር ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሚሰራበት ጊዜ ሁለቱም መሪዎች በአካል መገናኘት የመረጡበት ምክንያት፤ ጉዳያቸው ከኮቪድ-19 የዘለለ መሆኑን የሚያሳይ ነው" የሚል እምነት አላቸው።

ባለፈው ወር የፕሬዝደንቱ ጤና መቃወስን እና ህልፈተ ህይወት በማስመልከት በሰፊው ወሬ ሲናፈስ ነበር።

ሆኖም ከእለታት በአንዱ ቀን በቴሌቪዥን ቀርበው ኮሮናቫይረስ በዘመናዊ የአለም ታሪክ በብዙ መልኩ ያልተጠበቀ ድንገተኛ ጦርነት ነው በማለት፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር "ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣል አለበት" ብለው ነበር።

በዚህ መሠረት በኤርትራ ከሚያዚያ 2 ቀን 2020 ጀምሮ ህዝቡ ከቤቱ እንዳይወጣ ተነግሮታል። ኤርትራ በኮቪድ-19 የተያዙ 9 ሰዎች ብቻ ቢኖርዋትም የአገሪቷ ፕሬዝደንት ቁጥሩ እየጨመረ ወደ ሚታይባት ኢትዮጵያ መሄዳቸው ትልቅ ስጋት እንደፈጠረባቸው አቶ ደስበለ ይናገራሉ።

"የጉዞው ምክንያት በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ለመወያየት እንዳልሆነ መገመት እንችላለን። ምናልባት ፕሬዝደንቱ ታመዋል፣ ሞተዋል ሲባል ስለነበር ይህ እውነት እንዳልሆነ ለአካባቢው መልዕክት ለማስተላለፈ የተደረገ ፖለቲካዊ ጉዞ ሊሆን ይችላል። ስለ ኮቪድ-19 ለመወያየት ነው የተገናኙት ተብሏል፤ ኤርትራ እኮ ከዚህ በፊት ከቻይናዊው ባለሃብት (ጃክ ማ) የተላኩ የክህክምና እቃዎችን መልሳለች፤ ታዲያ እንዴት በዚህ ጉዳይ ይወያያሉ ተብሎ የሚጠበቀው? ለእኔ እጅግ የሚያሰጋኝ እና አሁን ያለው ዓለም አቀፋዊ ፕሮቶኮል የጣሰ ግንኙነት ነው።" ብለዋል።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝታቸው ጨርሰው ከትናንት በስቲያ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። እንደሚባለው ከጉዞ በኋላ እንደ ማንኛውም ሰው ለ14 ቀናት እራሳቸው ለይተው ያቆዩ ይሆን? የሚለው ደግሞ ሌላው ኤርትራውያን እያነጋገረ ያለው ጉዳይ ሆኗል።

ሁለቱም መሪዎቹ የተወያዩባቸው ዝርዝር ጉዳዮች በውል ባይታወቅም፤ በሁለቱም አገራት መካከል እያደገ ካለው ፖለቲካዊ ሁኔታ አንጻር ግን ፕሬዝደንቱ ለሌሎች ሁለት ምክንያቶች እንደመጡ መገመት ይቻላል ይላሉ የፖለቲካ ተንታኝና የሰብአዊ መብት ተሟጓች ዶክተር ሃይለ ሃጎስ።

ከዚህ በፊት ፕሬዝደንት ኢሳያስ "በኢትዮጵያ የሚመጣው የፖለቲካ ለውጥ ዝም ብለን አንመለከተውም፤ ያገባናል" ማለታቸው ይታወሳል። ይሄ ንግግር ብዙ ኢትዮጵያውያን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እጃቸውን እያስገቡ ነው የሚል ትችት እና ስጋታቸው ገልጸው ነበር። ፕሬዝደንት ኢሳያስ ደግሞ በሌሎች አገሮች ፖለቲካ ጣልቃ እየገባ ለራሱ በሚመቸው መንገድ መቃኘት ላይ ወደ ኋላ እንደማይል የታወቀ ነው።

"በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትልቁ የፖለቲካ ጉዳይ ደግሞ ምርጫ የተመለከተ ስለሆነ ኢሳያስ በዚህ ጉዳይ ኤርትራ ውስጥ ከነበሩ ሃይሎች በመነጋገር ለማግባባት መጥቷል ማለት እንችላለን። በሌላው ጉዳይ ብዙ ኢትዮጵያውያን ኢሳያስ መሞቱን ሲናገሩና ምኞታቸው ሲገልጹ ስለነበር ይህ ምኞት ብቻ ነው ለማለትም ይሆናል ብዬ እገምታለው" ይላሉ።

በዚህ ምክንያት፤ ሁለቱም መሪዎች በዚህ ጊዜ በሰዎች ህይወትና የእርሻ ምርቶች ትልቅ ስጋት በሆኑት የጤና ጉዳዮች ላይ ሊወያዩ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው በኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር ትዊተር በኩል የተሰጠው ምክንያት አሳማኝ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተደጋጋሚ በሚነገርበት ወቅት ለረጅም ቀናት ለህዝብ መግለጫ አልሰጡም ተብለው የታሙት ፕሬዝደንት ኢሳይያስ፤ ቆይተው "ወረርሽኙ የእኛን ትኩረት በመበጥበጥ ሊያሰንፈን አይገባም፤ የጀመርናቸውን የልማት ስራዎች ተግተን መቀጠል አለብን" ስላሉ ደጋፊዎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉት ጉዞ "የማይበገር" መንፈስ እንዳላቸው ማሳያ ነው ይላሉ።

ተቺዎቻቸው ደግሞ፤ ጊዜው መሪዎች የፖለቲካ ስራም፤ ሴራም የሚሰሩበት ሳይሆን፤ የአለም መንግስታትን የመምራት አቅም የተፈታተነውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት መግታትና መከላከል ላይ ያማከለ መሆን አለበት ይላሉ።

"አካሄዳቸው በጣም አደገኛ ነው፤ ያደጉ አገሮች መቆጣጠር ያልቻሉት ወረሽኝ ባለበት ወቅት ወደ ሌላ አገር ተጉዞ ፕሮጀክቶች መመረቅ አስፈላጊ ሆኖ አይታየኝም፤ የህዝቦች የጤና ጉዳይ ላይ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ጊዜው ያልጠበቀ ነገር መስራት ምን ፋይዳ አለው? በተለይ በቂ የውሃና መብራት አቅርቦት ለሌው የኤርትራ ህዝብ ቤት ውስጥ ተቀመጥ ብለህ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ ሌላ ፖለቲካ መፍጠር በታሪክ የሚያስጠይቅ ነገር ሊሆን ይችላል" ይላሉ ዶክተር ሃይለ ሃጎስ።

የአለም የጤና ድርጅት ቀጣዩ የኮቪድ-19 መዳረሻ አፍሪካ መሆንዋ በመግለጽ፤ መሪዎች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ለመመርመር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው እያስጠነቀቀ ይገኛል።

ኮሮና