“በከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ተሳትፈናል” የአሜሪካውያኖቹ ኑዛዜ በቬንዙዌላ ቴሌቪዥን

ፕሬዚደንት ኒኮላስ ማዱሮ( በስተግራ) እና ሉኬ ደንማን እና ኤራን ቤሪ (በስተቀኝ)

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዚደንት ኒኮላስ ማዱሮ( በስተግራ) እና ሉኬ ደንማን እና ኤራን ቤሪ (በስተቀኝ)

አሜሪካውያኖቹ የቬንዙዌላውን ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ለመጣል መፈንቅለ መንግሥት የማካሄዳቸውን ኑዛዜ የቬንዙዌላው ቴሌቪዥን አሳይቷል።

ፕሬዚዳንት ኒኮላስን መገልበጥ ብቻ ሳይሆን ይዘውም አሜሪካ እንዲያመጧቸው ትዕዛዝ መተላለፉንም ተናዘዋል።

በባለፈው ሳምንት ቬንዙዌላ ከሽፏል ያለችው መፈንቅለ መንግሥትን ተከትሎ አስራ ሶስት ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውላለች።

ከነዚህም ውስጥ አንዱ አሜሪካዊው ሉክ ዴንማን ነው። ቬንዙዌላ “ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች” ስትል የጠራቻቸውን ሲሆን “እቅዳቸውም አልተሳካም” ብላለች።

ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በተደጋጋሚ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ከስልጣን ሊገለብጧቸው እንደሚያሴሩና ሃገራቸውንም ለመውረር እንደሚያቅዱ ሲናገሩ ይሰማሉ።

በዚህም ሳምንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ አልተሳተፈችም ሲሉ ውንጀላውን ውድቅ አድርገውታል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ በበኩላቸው መንግሥታቸው ዜጎቹን ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ እንዲመለሱ “የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም” ብለዋል።

የቬንዙዌላ ቴሌቪዥን ምን አለ?

በትናንትናው ዕለት የ34 አመቱ ሉክ ደንማን ለመፈንቅለ መንግሥቱ የሚሆኑ ቬንዙዌላውያንን እንዲመለምልና ወደ ኮሎምቢያ ወስዶ ስልጠና እንዲሰጣቸው ትእዛዝ ተሰጥቶኛል ብሏል።

በመቀጠልም የሃገሪቱን አየር መንገድ በቁጥጥራቸው ስር እንዲያውሉና ፕሬዚዳንቱም ተይዘው ከሃገር እንዲወጡ አቅጣጫ መሰጠቱን ጠቁሟል።

“ቬንዙዌላውያን ሃገራቸውን መልሰው እንዲቆጣጠሩ እየረዳሁ ነበር” ያለው ሉክ ደንማን የቀድሞ የልዩ ኃይል ተልእኮ አባል ነበር።

ሉክና የ41 አመቱ አሪያን ቤሪ የተባለው ሌላ አሜሪካዊ ሲልቨርኮፕ በተባለ ኩባንያ መቀጠራቸውንም ግለሰቡ አጋልጧል። ኩባንያውን መቀመጫውን ፍሎሪዳ ያደረገ ሲሆን፤ ተልዕኮውንም የሚመሩት ጆርዳን ጎድሩ የተባሉ የአሜሪካ የጦር ኃይል አባል የነበሩ ግለሰብ ናቸው ብሏል።

ቬንዙዌላ ጆርዳን ጎድሩ ተላልፈው እንዲደሰጡ እጠይቃለሁ ያለች ሲሆን፤ ግለሰቡም በመፈንቅለ መንግሥት ተልዕኮው ላይ ተሳትፎ እንደነበራቸው አምነዋል።

ሲልቨርኮፕ የተባለው ኩባንያ በበቬንዙዌላ ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑትና በአውሮፓውያንና በአሜሪካውያን ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ጁዋን ጉዋይዶ ጋር ስምምነት እንዳላቸው ፕሬዚዳንቱ ኒኮላስ ማዱሮ ገልፀዋል።

“የወረራው ጠንሳሽ ዶናልድ ትራምፕ ናቸው” በማለት ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ከአሜሪካዊው ኑዛዜ በኋላ በሰጡት መግለጫ ወርፈዋቸዋል።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም አሜሪካውያኖቹ ፍትሃዊ ፍርድ ይጠብቃቸዋል ከማለት ውጭ ግለሰቦቹ የት እንደታሰሩ፣ ጠበቃ አግኝተው እንደሆነና ሌሎች መረጃዎች ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ስለ አሜሪካውያኖቹ የቀደመ ታሪክ ዝርዝር መረጃ ባይገኝም ቬንዙዌላ የአሜሪካ የፀጥታ ኃይል አባላት ናቸው ስትል፤ የአሜሪካ ሚዲያዎች በበኩላቸው የቀድሞ አባላት ናቸው ብለዋል። ከአሜሪካ መንግሥት ግን ስለማንነታቸው የተሰጠ መረጃ የለም።

ጆርዳን ጎድሩ ከዚህ ቀደምም ከቬንዙዌላው ፖለቲከኛ ጁዋን ጉዋይዶ ጋር ግንኙነት አለኝ ሲሉ በተደጋጋሚ ተሰምተዋል።

ፖለቲከኛው በበኩላቸው በመግለጫቸው የጦር ኃይል አባሉን እንደማያውቋቸውና “ከተፈፀሙት ነገሮችም ጋር ምንም አይነት ንክኪም ሆነ ኃላፊነት የለኝም” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዚዳንቱን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የመጡ ግድያዎችና ግጭቶችን ለማዘናጋት የፈጠሩት ዘዴ ነው በሚልም ፖለቲከኛው ተችተዋቸዋል።

የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥትን ተከትሎ 11 ሰዎች ሲታሰሩ፣ ስምንት ሰዎች ደግሞ ተገድለዋል።