ደቡብ ኮርያ ኪም የልብ ቀዶ ህክምና ስለማድረጋቸው 'ምንም ምልክት የለም' አለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የደቡብ ኮርያ ደህንነት አጄንሲ የኪም ጆንግ-ኡን ጤና መቃወስን በማስመልክት ሲወጡ የነበሩ ዘገባዎች መሰረተ ቢስ ናቸው አለ።
ኤጀንሲው ጨምሮም ኪም የልብ ቀዶ ህክምና ስለማድረጋቸው የሚያሳይ ምንም አይነት ምልክት የለም ብሏል።
የሰሜን ኮርያ መሪ በቅርቡ በአደባባይ ሳይታዩ ለ20 ቀናት ቆይተው ነበር። በአገሪቱ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የአያታቸው ልደት በዓል ላይ አለመገኘታቸው በርካቶች የጤና ሁኔታቸውን እንዲጠራጠሩ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።
አንዳንድ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ኪም በጠና መታመማቸውን የዘገቡ ሲሆን፤ ኪም ህይወታቸው አልፏል ያሉም በርካት መገናኛ ብዙሃን ነበሩ።
በቅርቡ ግን ኪም የምርጥ ዘር ፋብሪክ ምርቃት ላይ ታይተዋል። ሙሉ ጤነኛም ይመስላሉ።
የደቡብ ኮሪያ ደህንነት ኤጀንሲ ያለው ምንድነው?
የደቡብ ኮርያ ደህንነት ኤጀንሲ አለቃ ሱን ሁን ለአገሪቱ የህዝብ እንደራሴዎች ኮሚቴ ሲናገሩ የኪም ጆንግ-ኡንን ጤና በማስመልከት ሲወጡ የነበሩ ዘገባዎች ስህተት ናቸው ብለዋል።
ለፓርላማ አባለቱ የሰሜን ኮርያው መሪ በዚህ ዓመት ለ17 ጊዜ በአደባባይ እንደታዩ የተነገራቸው ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በነበሩ ዓመታት በተመሳሳይ ወቅት 50 ጊዜ በአደባባይ ታይተው ነበር።
ምንም እንኳ ሰሜን ኮርያ በይፋ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ስለመኖሩ በይፋ ባታሳውቅም፤ ኪም በአደባባይ ያልታዩት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሳይሆን አይቀርም ያሉ አልጠፉም።
የኪም የጤና መቃወስ ዜና መናፈስ እንዴት ጀመረ?
በሚያዚያ ወር የመጀመሪያ ሳምንት መጨረሻ አካከባቢ ኪም ጆንግ ኡን የአያታቸውን የልደት ዝግጅት ሳይታደሙ ቀርተዋል። ይህ በዓል የአገሪቱ መስራች እንደሆኑ የሚታሰቡ ግለሰብ ልደት እንደመሆኑ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ዝግጅት ነው።
ኪም ጆንግ-ኡን ከዚህ ቀደም ሳይታደሙ ቀርተው አያውቅም - ብርቱ ጉዳይ ካልገጠማቸው በቀር አይቀሩም።
ኪም በዝግጅቱ ሳይገኙ መቅረታቸው በበርካቶች ዘንድ እንዴት? ለምን? የሚሉ ጥያቄዎች እንዲነሱ አደረጉ።
ኪም ለመጨረሻ ጊዜ በብሔራዊ ጣቢያው የታዩት ሚያዚያ 4 ላይ ነበር። በቴሌቪዥን ሲታዩ እንደተለመደው ዘና ብለው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ኪም በአደባባይ ሳይታዩ ቀሩ።
ከዚያ በኋላም ሰሜን ኮርያ የሚሳኤል ሙከራ አድርጋ ነበር። የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ በዘገበበት ወቅት የኪም ጆንግ-ኡንን ስም አልጠቀሰም። ምስላቸውንም አላሳየም። ከዚህ ቀደም ሰሜን ኮርያ መሰል ወታደራዊ ሙከራዎችን ስታካሂድ ኪም በቴሌቪዥን መስኮት ይታዩ ነበር።












