በእግር ኳስ በፌዴሬሽኑ ውሳኔ ላይ የክለብ አመራሮች ምን ይላሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የ2012 ዓ.ም ሁሉም የሊግ ውድድሮች መሰረዙን ትላንት አስታውቋል። ውድድሩ በመሰረዙም አሸናፊ እና ወራጅ ቡድን አለመኖሩን አስታውቆ፤ ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ እና የኮንፌደሬሽን ካፕ ላይ እንደማትሳተፍ ገልጿል።
የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በተከናወነበት ሊግ ቀሪ 13 መርሃ ግብሮች መካሄድ ይጠበቅባቸው ነበር። ይህም 45 በመቶ የሚሆነውን ውድድር ይሸፍናል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኘን ምክንያት በማድረግ የተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ የሊጉ ክለቦች ምን ይላሉ?
የባህር ዳር ከነማ ስፖርት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ፍቃዱ፤ የፌደሬሽኑን ውሳኔ የሰሙት ከመገናኛ ብዙሃን መሆኑን ጠቅሰው "የተወሰደው እርምጃ ጥሩ እና ወቅታዊ ነው" ሲሉ ይገልጻሉ።
በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት የፋሲል ከነማ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዮት ብርሃኑ ናቸው። እንደ አቶ አብዮት ከሆነ "ከየትኛውም ነገር በላይ የሰው ልጅ ህይወት ስለሚበልጥ" ውድድሩ በመቋረጡ ላይ ቅሬታ የላቸውም።
የመቀሌ 70 አንድርታ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽፈራው ተክለሃይማኖት ግን "የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ውሳኔ ወቅታዊ ነው። ቢሆንም እንደግለሰብ የውሳኔው ሂደት ላይ ቅሬታ አለኝ። አሰልጣኞችን በማነጋገር ብቻ ነው ጥናት ያደረጉት። የክለብ ኃላፊዎችን አላነጋገሩም። ከባለቤቱ መረጃ ማግኘት ነበረባቸው። ውሳኔው ላይ ቁንጽል መረጃ ነው የወሰዱት" ይላሉ።
የባህር ዳር ከነማ ስፖርት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑልም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ። "ክለቦች የራሳቸውን ሃሳብ ያቀረቡበት ነገር ያለ አይመስለኝም፤ እንደክለብ ምንም አስተያት አላችሁ በሚል የቀረበ ነገር የለም። እንዲህ ቢሆን? ያለው ነገር የለም" ብለዋል።
"የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ተነጋግረዋል" የሚሉት የፌደሬሽኑ ጊዜያዊ ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ ባህሩ ጥላሁን ናቸው። "የሊጉ አብይ ኮሚቴ ወይም ሼር ካምፓኒ ከሚመለከታቸው ክለቦች እና ከውድድርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ጋር እንዲወያይ አቅጣጫ ተሰጥቶት ነበር" ይላሉ።
"እነዚህን ሂደቶች ተከትለናል። ሼር ካምፓኒው ከአብይ ኮሚቴ እና ከውድድርና ስነ-ርዓት ኮሚቴ ጋር በመሆን ምክረ ሃሳብ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አቀረበ። ፌደሬሽኑ ደግሞ ከመንግስትም የተቀመጠውን አቅጣጫ በመመልከት ውሳኔ አስተላለፈ" ባይ ናቸው።
"ከሊጉ ጋር የተያያዘውን ሼር ካምፓኒው ኃላፊነት እንዲወስድ የተደረገ ሲሆን አብይ ኮሚቴው ደግሞ ከክልቦች የተወጣጡ ስለሆኑ ተሳትፈዋል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ክለቦቹን የሚወክለውን ሼር ካምፓኒ አናግሬያለሁ ቢልም ክለቦቹ ግን በዚህ ተቃራኒ ቆመዋል።
"ሼር ካምፓኒ ተቋቁሟል እኛም አባል ነን። ካምፓኒው እና ፌደሬሽኑ ተነጋግረው ሊሆን ይችላል። ካምፓኒው ግን ክለቦቹን አላናገረም" ያሉት አቶ ልዑል ናቸው።
አቶ ሽፈራውም ተመሳሳይ አቋም አላቸው። "ለግብር ይውጣ ሼር ካምፓኒ ቢያናግሩም እኛን ካማፓኒው ማናገሩን ማወቅ ነበረባቸው። ዓለም አቀፉ የእግርኳስ አስተዳዳሪ /ፊፋ/ ፍኖተ ካርታ ክለቦችን አናግራችሁ ለሃገር ተስማሚ የሆነ ውሳኔ ላይ እንድትደርሱ ብሏል። እኛ አስተዳዳሪ አካላችን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ነው። አወዳዳሪ አካላችን ደግሞ ሼር ካምፓኒው ነው። በቴክኖሎጂም ቢሆን ሃሰባችንን ማድመጥ ነበረበት" ብለዋል።
ሌላው የውሳኔው ወቅታዊነት ላይ የሚቀርብ ጥያቄ ነው። የስፖርት ጋዜጠኛው መኳንንነት በርሄ እንደሚለው ያነጋገራቸው አብዛኛዎቹ ክለቦች በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዳላደረጉ እንደገለጹለት አስታውቋል። ለዚህም "ክለቦችን ያላማከለ የሊግ ካምፓኒውንም የፈጠነ ይመስለኛል። አንዳንድ ክለቦችን ሳነጋግር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ሆነ ሊግ ካምፓኒው አላነጋገረንም የሚል ሃሳብ አንስተዋል። ክለቦች ሊግ መስርተዋል። ሊጉ ያለ ክለቦች ምንም ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ውሳኔው ትንሽ የፈጠነ ይመስለኛል።"
የፌደሬሽኑ ጊዜያዊ ዋና ጸሐፊ አቶ ባህሩ "ካፍ እስከ ሜይ 5 [ሚያዚያ 27] ባለው የኢትዮጵያን የሊግ ሁኔታ አሳውቁን ብሎ ነበር" በማለት ያስረዳሉ።
በሃገሪቱ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለአምስት ወራት የሚቆይ መሆኑ እና በሽታው መቼ በቁጥጥር ስር ማዋል እንደሚቻል አለመታወቁም ሌላው ጉዳይ ነው።
አቶ ሽፈራው "የሚጠበቁ የተወሰኑ ውሳኔዎች ተካተዋል። የሊጉ ጨዋታዎች መሰረዝ ካለው ሃገራዊ ችግር አንጻር እሱ ላይ ብዙም አልተከፋሁም" ይላሉ።
እንደ አቶ ሽፈራው፤ "ሰኔ ላይ ወረርሽኙ አለቀ ተብሎ ጨዋታዎች ይቀጥሉ ቢባል እንኳን ብዙ ፈተናዎች ሊጉን ይፈትኑታል። ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ እና የሃገሪቱ የመጫወቻ ሜዳዎች ለክረምት የሚሆኑ አለመሆናቸው፤ የብዙ እግር ኳስ ተጫዋቾች ውል ሰኔ 30 መጠናቀቁ፤ ጨዋታዎች ወደ መስከረም እና ጥቅምት እንዲተላለፉ ከተደረገ ደግሞ ብዙዎች በበጀት ምክንያት የሚሳካላቸው አይመስልም።
"ጨዋታ መሰረዝ አንዱ አማራጭ ነው። በውድድሩ እስካሁን የማይናቅ ገንዘብ ቢወጣበትም። ወራጅም ወጪም የለም። በተለይ ወደ ላይ ለሚወጡት ክለቦች ብዙ በጀት አፍስሰው ተስፋ ቢያደርጉም መሰረዙን አልቃወምም። እስከዚህ ድረስ እስማማለሁ" ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልፃሉ።
በውሳኔው ላይ ያላቸው ልዩነት ከዚህ ይጀምራል። "ሃገራችን የካፍ መስራች ሆና በአፍሪካ መድረክ አትሳተፍም ማለት ግን ስህተት ነው። 16 ክለቦች ማን ቢወክል ይሻላል በሚል በጥልቀት መወያየት ነው እንጂ ኢትዮጵያ አትሳተፈም ማለት ክለቦች የላትም የሚል ስለሆነ እሱ ላይ ተቃውሞ አለኝ" ብለዋል።
በውድድሩ እነማን መሳተፍ አለባቸው በሚለው ላይ "ህጋዊ መንገዶችን ትቼ በቀላሉ ጠንከር ያለ ኢኮኖሚ ያላቸውን መላክ፣ በስምምነት የባለፈው ዓመት ውጤት ይዞ እነሱን ማሳተፍ ወይም እስካሁን ባለው ደረጃ ወይም ደግሞ በዕጣ መስጠት ይቻላል። ብዙ አማራጮች አሉ። በዕጣ በማድረግ ኢትዮጵያን ማዳን ይችሉ ነበር" ሲሉ ያስረዳሉ።
ለስፖርት ጋዜጠኛው መኳንንት በርኼ ደግሞ የሌሎች ሃገራትን ተሞክሮ መመልክት አንዱ አማራጭ ነው። "ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ቡርኪና ፋሶ 1ኛ እና 2ኛ ሆነው የጨረሱትን ነው በሻምፒዮንስ ሊግ እና በኮንፈደሬሽን ካፕ እንዲሰለፉ ያደረጉት። ቡርኪናፋሶ አምና የተሳተፉትን ነው ያሳለፈችው። ክለቦቹ አቅም አለን እንጫወታለን ካሉ ተጫወቱ መባል ነው የነበረበት። ገዳቢ ይመስለኛል ውሳኔው" ይላል።
የባህር ዳር ከነማ ስፖርት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ፍቃዱ ግን የተለየ ሃሳብ ያነሳሉ። "በትክክል አፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ሆነ የኮንፈደሬሽን ካፕ ውድድሮች ይካሄዳሉ?" የሚል። ካልተካሄደ ውሳኔው ማስቀጠል ካልሆነ ግን ክለቦችን ባሳተፈ መልኩ የሌሎችን ሃገራት ልምድ ወስዶ መተግበርን ይመርጣሉ።
እስካሁን ባለው የሊጉ ውድድር በ17 ጨዋታ ፋሲል ከነማ በ30 ነጥብ ሊጉን ይመራል። ሥራ አስኪያጁ አቶ አብዮት ውሳኔውን "እስካሁን ለደረስንበት ተገቢው እውቅና ካለመስጠቱ በተጨማሪ በአፍሪካ መድረክ ተወዳዳሪ የለም በሚል ፋሲልን ከውድድር ውጭ ማድረጉ ተገቢ አይደለም። ውድድሩ መቋረጡ ላይ ልዩነት ባይኖረንም በአፍሪካ መድረክ ጉዳይ ላይ ቅሬታ አለን" ይላሉ።
በመጀመሪያ ሃገሪቱን ተሳትፎ በማቀጨጭ የተጫዋቾችንም እድገት የሚጎዳ ነው ብለውታል። "እንደ ካፍ መስራች እንደኬንያ እና ቡርኪና ፋሶ ካሉ ሃገራት የተለየ ውሳኔ መሰጠቱን የተሳሳተ መሆኑን ያሳያል። ሊጉን የሚመራው ፋሲል በዚህ ይጎዳል" ብለዋል።
የፋይናነስ ቀውስ
የሊግ ውድድሮች መሰረዙ ሌላው ያስከተለው ችግር የፋይናነስ ቀውስ ነው። በተለይ ደግሞ ከፍተኛ የስታዲየም ገቢ የነበራቸው ለዚህ ይጠቀሳሉ።
እንደ አቶ ባህሩ ከሆነ ፌደሬሽኑ ፋይናንስን በተመለከተ መንግስት ለክለቦች ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርቧል። "ኮቪድ በሊጉ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ላይ ፊፋ ጥናት አካሂዷል። ፊፋ ቀደም ሲል የለቀቀው የ500 ሺህ ዶላር ፈንድ ለሥራ ማስኬጃ ነው። የኢመርጀንሲ ፈንድ ለተወሰኑ ሃገራት ሊለቅ ይችላል። እኛም የዚህ አካል ልንሆን እንችላለን በሚል እየጠበቅን ነው። እንደዛ ከሆነ ለክለቦች ድጋፍ እናደርጋለን" ብለዋል።
ስለቀጣይ ውድድር ዓመትም ተጠይቀው "በሚቀጥለው ዓመት የወረርሽኙ ጉዳይ መጨረሻው ካልታወቀ የ2013 ውድድርም ላይጀምር ይችላል" ያሉት አቶ ባህሩ "ስለዚህ ውሳኔው የኮቪድ-19 በቁጥጠር ስር መዋል እና አለመዋል ጋር የተያያያዘ ነው" ሲሉ ያስረግጣሉ።













