በኮሮናቫይረስ ምክንያት ኢትዮጵያውያን እየተፈተኑባት ያለችው ኢስሊ

የፎቶው ባለመብት, SOPA Images
ቡና ለኢትዮጵያውያን የምታነቃቃ መጠጥ ብቻ አይደለችም። ጎረቤት፣ ዘመድ፣ ወዳጅና ቤተሰብ ተሰባስቦ የሚወያይባት፤ የአብሮነት መገለጫ፣ እንዲሁም ከዘመን ወደ ዘመን ስትተላለፍ የመጣች የትውልድ አሻራ ናት።
ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ስደተኞች በየሄዱበት ቡናን ይዘዋት ተጉዘዋል፤ 'በባዕድ አገር' አገራቸውን ለመፍጠር ሞክረዋል። በተለያየ እድሜ ላይ ለሚገኙ ሴቶች ምስጋና ይግባቸውና በውጭ አገራትም ቢሆን ቡና ይቆላል፣ ፈንዲሻው ይፈካል፣ ዕጣኑ ይጨሳል የተገኘውም የቡና ቁርስ ይቀርባል።
ኢትዮጵያውያኑ ባህር አቋርጠው፣ በሺዎች ኪሎ ሜትር ርቀትም ባሉበት ሁሉ እንጀራ፣ ቅቤው፣ የወጡ ሽታ የመኖሪያ ህንጻዎችን ያውዳል፤ ዓመት በአል አከባበራቸው አገርን፣ ባህልን፣ ቤተሰብንና ትውልድን ተሸክሞ መምጣት ምን ማለት እንደሆነ ያሳያል። ከአገር ውጭ አገርን፤ ከቤት ውጭ ቤትን መፍጠር ያውቁበታል።
በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ውስጥ በምሥራቅ ሲቢዲ የምትገኘው ኢስሊም በፔርሙስ ቡና ከሚያዞሩ፣ ልክ እንደ ኢትዮጵያ የእማማ ቤቶች ተብለው በሚጠሩ ትንንሽ ምግብ ቤቶች ውስጥ ቡናው ይቆላል፣ ጭሱም ይጨሳል፣ አድባሯንም ይለማመኗታል።
ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ኢስሊ መሸጋገሪያ ናት፤ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ለሚደረጉ ጉዞዎች ለሌላ ስደት ጊዜን የሚጠብቁባት እንዲሁም የሚዘጋጁበት ቦታ ናት። ጉዳያቸው ተጠናቆ ምን ያህል ዓመታት እንደሚጨርስ ባይታወቅም ባሉበት በተለያዩ ንግዶች ተሰማርተው ይኖራሉ።
በተለይም ኢስሊ 10ኛ ተብላ የምትጠራው ሰፈር የኢትዮጵያውያንና የኤርትራውያን ስደተኞች መናኸሪያ ናት፤ የህልሞች መሰሪያ ስፍራ።
በኢስሊ ቅናሽ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የመጋረጃ ጨርቆች፣ ታዋቂ የዲዛይነር ምርቶች ከሚሸጡባቸው ትልልቅ ሞሎች በተቃራኒው የፕላስቲክ እና የማዳበሪያ ጣሪያ የለበሱ ሱቆች፤ የጡት ማስያዣ ሳይቀር ሰልባጅ ልብስ የሚሸጥባቸው ቦታዎች፣ ጉንጫቸው በጫት የተወጠረ ቃሚዎችና ጫት ሻጮች ሁሉ በየአይነቱ የተሞላባት ናት።
በኢስሊ አዳዲስ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች ይሰማሉ፣ ልክ ኢትዮጵያ ያሉ ይመስል በአማርኛ የተሰሩ ፊልሞች ድራማዎች በሲዲዎችም ኮፒ እየተደረጉ ይሸጣሉ። ምግብ ቢሆን የፍም ጥብስ፣ ቁርጥ፣ ክትፎ፣ በየአይነቱ፣ ሽሮ የሌለ የለም፤ ሬስቶራንቶቹ ውስጥ ውሃም ከሌለ እንደ ኢትዮጵያም በጆግ ሊታጠቡ ይችላሉ።
ኢስሊ፤ በርካታ ቋንቋዎች፣ ቀለሞች፣ ድምፆች፣ ማታቱና 'ጀብሎው' የሚነታረኩባት፣ መንገዶቿ ከመጨናነቃቸው የተነሳ የታክሲ አሽከርካሪዎች ከገቡ ለመውጣት እንደሚቸገሩ ስለሚያውቁ እንደ 'ቤርሙዳ ትሪያንግል የሚፈሯት' አዛኑ ቀጥታ ወደ ፈጣሪ የሚደርስ ይመስል ጎላ ብሎ የሚሰማባት ያች ደማቅ ስፍራ በአሁኑ ሰዓት ፀጥ ረጭ ብላለች።
ኬንያ እንደ ሌሎች አገራት አስገዳጅ የቤት መቀመጥ መመሪያ ባታስተላልፍም የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው በርካታ ህሙማን በመዲናዋ ናይሮቢ ኢስሊና በባህር ዳርቻዋ ከተማ ሞምባሰ ኦልድ ታውን መገኘታቸውን ተከትሎ ሰፈሮቹ ከምንም አይነት እንቅስቃሴ ተገድበዋል።
በተለይም በኢስሊ በአንድ ቀን ውስጥ 29 የኮሮናቫይረስ ማግኘታቸውን ተከትሎ ነበር የአገሪቱ የጤና ባለስልጣናት ወደ ኢስሊ መግባትም ሆነ መውጣት የከለከሉት።
ባለስልጣናቱ አስፈላጊ የሚባሉት እንደ መድኃኒትና ምግብ ለማድረስ ካልሆነ በስተቀር በአቅራቢያው መድረስ አይቻልም ብለው መወሰናቸውን ተከትሎም ፖሊሶችና ፀጥታ አስከባሪዎች አካባቢውን ወረውታል። ይህ የዋና ከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ዋነኛ ስፍራ ከእንቅስቃሴ ውጪ መሆኑ አስከዛሬ [ግንቦት 12/2012 ዓ.ም] የሚቆይ እንደሆነ የተነገረ ቢሆንም ሁኔታዎች ካልተቀየሩ ግን ሊቀጥል ይችላል።
"የባሰ አያምጣ"
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የእንቅስቃሴ ገደቡን በተወሰነ መልኩ ላልቶ የንግድ ቦታቸውን እንዲከፍቱ ቢወሰንም፤ አሁንም ቢሆን ከኢስሊ ውጪ ያሉ ደንበኞች ወደ አካባቢው አለመግባታቸው መክፈታቸውን ትርጉም አልባ እንዳደረገው በኤምፔሳ ንግድ የሚተዳደረው ኢትዮጵያዊው ዮናስ ይናገራል።
ኢስሊ ሙሉ በሙሉ ከመዘጋቱ በፊት በተቻለ መጠን ኦካላዊ ርቀታቸውን እየጠበቁ ይሰሩ የነበረ ሲሆን በመሆኑ እንደነ ዮናስ ላሉት ጉሮሮ መድፈኛቸውን አላሳጣቸውም ነበር።
በአሁኑ ሰዓት ግን የሚከፍለው የቤት ኪራይ 12 ሺህ ሺልንግ፣ ለሱቅ ኪራይ ደግሞ የሚከፍለው 20 ሺህ ሺልንግ በየወሩ አለበት። ከዚያ በተጨማሪ ምግብ እንዲሁም ሌሎች ወጪዎች ሲደማመሩ ገቢው ለተቋረጠበት ሰው እንዴት ፈታኝ እንደሆነ ለማሰብ አያዳግትም።
ዮናስ ምንም እንኳን "ማማረር አልወድም" ቢልም በጣም ከባድ ወቅት እያሳለፉ እንደሆነም ይገልፃል። በአካባቢው የሚሰሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚበሉት አጥተዋል፤ ትንሽ ሻል ያሉትም ቁርስ በልተው ምሳ መድገም ከብዷቸዋል። የቤት ኪራይ ሳይከፍሉ ትንሽ አቅም ካላቸው ጋር ተጠግተው የሚኖሩም አሉ።
ዮናስም የቤት ኪራዩ በርካታ ቀናት ቢያልፍም የንግድ እንቅስቃሴው ቀጥ በማለቱ የሚከፍለው የለውም፤ ነገም እንዴት እንደሚከፍል አያውቅም።
"አሁንም መስሪያዬን ነው እየበላሁት፤ ግን ቢሆንም አላማርርም። እናቴ እንደምትለው "የባሰ አያምጣ ነው" የሚባለው" ይላል።
ሁኔታዎች ደህና በነበሩበት ወቅት በቀን ከአርባ እስከ አምሳ ሰው ያስተናግድ ነበር እሱም ሆኖ ለኑሮው በቂ አልነበረም። የሚኖርበትም ቦታ በኢስሊ 11ኛ ተብሎ የሚጠራው ሰፈር ሲሆን ከሚሰራበትም ቦታ የጥቂት ደቂቃዎች መንገድ መሆኑ ቢያንስ የትራንስፖርት ወጪን ቀንሷል።
ሆኖም እነ ዮናስ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ራሳቸውን ከአዲሱ ሁኔታ ጋር ማለማመድ ግዴታቸው ሆኗል። "በኢስሊ ኑሮን ቀለል ታደርጊዋለሽ። የተገኘውን ነገር አበሳስሎ መብላት ይቻላል። 'እግዚአብሔር አይነ ስውር አሞራን ይቀልባል' አይደል የሚባለው። ሆኖም ከእኔ የባሱ ጓደኞቼም፣ ወንድሞቼም አሉ" ይላል ዮናስ።
በተለይም ወደ ሞያሌ የሚጓዙ መንገደኞች መናኸሪያ የሆነችው ኢስሊ ገንዘብ የሚቀይሩት፣ የሚያስፈልጓቸውን እቃዎች የሚሸምቱባት ከመሆኗ ጋር ተያይዞ በአሁኑ ወቅት የአውቶብሶቹ እንቅስቃሴ መቆሙ ሰፈሯን ሽባ አድርጓታል። የአውቶብሶቹ መከልከል የተጀመረው ዮናስ እንደሚለው አሁን ሳይሆን ኢስሊ የመዘጋት ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ነው።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት "ሰብአዊነት ቢኖር" የሚለው ዮናስ ለተቸገሩት የቤት ኪራይ ቢቀንስ፣ የቻሉት ደግሞ የቤት ኪራይ ሙሉ በሙሉ መተው ቢችሉ በተቻለ መጠን ችግሩን እንደሚያቀለው ያምናል።
በአሁኑ ወቅት በርካቶች ያላቸውን ገንዘብ አሟጠው እየተጠቀሙ ሲሆን ይህም ሁኔታ ለወደፊቱ የሚፈጥረውን ጫና ማሰብ ለዮናስ ከባድ ነው። "ሰርተሽ ሳይሞላልሽ የምትከፍይው የቤት ኪራይ ያናድዳል። ምንም ሳትሰሪ ሲሆን ደግሞ በጣም ያበሳጫልም" ይላል።
ሆኖም ወቅቱን ተረዳድተው ለማለፍ ምግብ ቤቶች ባይከፈቱም ያልተከፈተ አንድ ሱቅ አለ። እዚያች ገባ ብለው፣ ሽሮውንም፣ አቮካዶና ድንችም ቀላቅለው ያገኙትን ምሳ ይቀማምሳሉ። ። እዚያች ገባ ብለው፣ ሽሮውንም፣ አቮካዶና ድንችም ቀላቅለው ያገኙትን ምሳ ይቀማምሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, SIMON MAINA
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእለት ገቢያቸው የሚተዳደሩባቸውን አካባቢዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመዘጋታቸው በርካታ ሰዎች ለረሃብና ለእንግልት መዳረጋቸውን ተከትሎ አገራት የወሰዷቸውን እርምጃዎች ከኢኮኖሚያዊ ፍትህና፣ የማኅበረሰብን ደኅንነትን ከመጠበቅ አንፃር በርካቶች ተችተውታል።
አስገዳጅ ቤት ውስጥ የመቀመጥ ውሳኔ አብዛኛውን ደሃ ሕዝብ ያላማከለ፣ በተለይ በኢ-መደበኛ ዘርፎች ተሰማርተው የሚኖሩ አፍሪካውያንን የዘነጋ፣ ለጥቂቶች የተሰጠ ቅንጦት ብለውታል።
በኢስሊ በተለይም ክፉኛ የተጎዱት በምግብ ቤቶች፣ በሱቆች እንዲሁም በተለያዩ የንግድ ቦታዎች ተቀጥረው በቀን ሥራ የሚተዳደሩት ናቸው። በቀን ለፍተው የሚያገኙት ገቢ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።
ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ እንደመሆኑ መጠን እንኳን መቆጠብ የእለት ጉርስና ማደሪያም መሸፈን በትግል ነው። አሰሪዎቻቸውም ባለው የኮሮናቫይረስ ቀውስ እንኳን ለመክፈል ለራሳቸውም ኪሳራ ላይ ናቸው።
በኢስሊ ውስጥ ምጣድ፣ ሽሮ፣ በረበሬ፣ ቅቤ፣ ጤፍ፣ ባቄላ በአጠቃላይ ማንኛውንም የኢትዮጵያ ምርቶችን የሚቸረችረው ተስፋዬ በስሩ የሚያስተዳድራቸው ሠራተኞች በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሆኑ ይናገራል።
ምንም እንኳን ከሰሞኑ ሱቁ ቢከፈትም ዝር የሚል ደንበኛ የለም፤ ለዚህም በርካታ ደንበኞቹ ከኢስሊ ውጭ በመሆናቸው ነው። በመኪናም ሆነ በሞተር እንኳን እንዳይልክ መንገዶች በመዘጋታቸው መውጫ የለም።
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በርካታዎቹ ሸቀጦች የሚበላሹ ከመሆናቸው አንፃር በቅርብ ጊዜ መሸጥ ካልቻለ ለበለጠ ኪሳራ እንደሚጋለጥ ይናገራል።
ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያና በኬንያ ያለው ድንበርን መዘጋትን ተከትሎም ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ያመጣቸው የነበሩ ምርቶችንም ማስመጣት አይችልም። ለወደፊቱም መቼ እንደሚከፈት ግልፅ ካለመሆኑም ጋር ተያይዞ የወደፊቱን ሁኔታ አጨልሞበታል።
ምንም እንኳን የንግድ እንቅስቃሴው ቀጥ ቢልም ለሱቁ 40 ሺህ ሺልንግ፣ ለመጋዘኑ 30 ሺህ ሺልንግ፣ የቤት ኪራይ 50 ሺህ በአጠቃላይ 120 ሺህ ሺልንግ [ከ1100 ዶላር በላይ] ወጪ አለበት። ከዚህም በተጨማሪ የአራት ልጆቹ እንዲሁም በአጠቃላይ የቤተሰቡ ወጪ ሲደማመር ወጪውን ያንረዋል። ገቢ በሌለበት ሁኔታ ደግሞ ይሄ ሁሉ ወጪ "ኪሳራ ነው" ይላል።
ከዛሬ አስራ አንድ ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የመጣው ተስፋዬ በኢስሊ በንግድ ለ10 ዓመታት ያህል ሰርቷል። በሕግ ትምህርት የተመረቀው ተስፋዬ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረበት ወቅት በአቃቤ ሕግነትም ሰርቷል። ከነበረበት የሥራ ዘርፍ ወደ ስደት ስለመጣበት ሁኔታም መናገር የሚፈልገው ታሪክ አይደለም።
"ከበሽታው በላይ ድህነት ነው የሚገድለን"
ለአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ኢስሊ ከመዘጋቷ በፊት ንግዳቸው ቀጥ ብሏል። ከእነዚህም መካከል በኢስሊ 10ኛ ሰፈር የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ባለቤት የሆነው በረከት አንደኛው ነው።
ኬንያ የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመግታት ስትል ሬስቶራንቶችን መዝጋቷን ተከትሎ እሱም ከሥራ ውጪ ከሆነ ሁለት ወራትን ያህል አስቆጥሯል።
በየወሩ ለሬስቶራንቱ ኪራይ የሚከፍለውን 66 ሺህ 300 ሺልንግ ሥራ ባቆመበት ሁኔታ መክፈል የማይቻል ትግል ሆኖበታል።
ለሁለት ወራት ያህልም የሱቅ ኪራይ እንዳልከፈለ አልደበቀም። እንዲያው ይኼ ቀውስ እስኪያልፍ ድረስ ሌላ ቦታ ተቀጥሮ ለመስራትም አስቦ የነበረ ቢሆንም የብዙ ንግድ እንቅስቃሴዎች በመዳከሙ ተስፋዬ ያገኘው ነገር የለም።
ምንም እንኳን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሬስቶራንቶች ይከፈቱ የሚል ፍቃድ ቢኖርም የእሱ ብዙዎቹ ደንበኞች ከሌላ ቦታ የሚመጡ በመሆናቸው እንዲሁም እሱ የሚሸጥበት የምግብ ዋጋ በአማካኝ 400 ሺልንግ በመሆኑ፤ እንኳን አሁን ከዚህ ቀደምም ለመብላት አቅሙ እንደሌላቸው በረከት ይገልፃል።
ለብዙዎች በአሁኑ ወቅት እንጀራ በወጥ መብላት የማይታሰብ በመሆኑ፣ በቀን ሶስት ጊዜ መብላት እንደ ቅንጦት እንደሚታይ የሚገልፀው ተስፋዬ፤ በርካቶች በቀን የሚያገኟትን ዳቦ በአቮካዶ ይበላሉ። "ከበሽታው በላይ ድህነት ነው የሚገድለን" ይላል።
ሆኖም "በህይወት መኖር ደግ ነው። ያው የተሻለ ጊዜ እግዚአብሔር ያምጣልን" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, YASUYOSHI CHIBA
ምንም እንኳን በኢስሊ በርካታ ሶማሌዎች ቢኖሩም ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከታንዛንያና ከኮንጎ የመጡ ስደተኞች አንድ ላይ የሚኖሩባት፣ የቀጠናውን ባህል፣ ሕዝብ እና እምነት አንድ ላይ የሚመጣባት ስፍራ ናት። ዮናስም ለዚህ ምስክር ነው።
"ቦታው ከብዙ ሰው ያገናኛል። ኬንያውም፣ ኢትዮጵያዊውም፣ ኤርትራዊውም እዚህ አለ። ደስ ይላል። አንዳንዴም 'ስደተኛ' በማለት ዝቅ ሊያረግሽ የሚሞክርም ይመጣል" በማለት ዮናስ መልካሙንና መጥፎውን ያወሳል።
መርካቶ ያደገው ዮናስ ወደ ናይሮቢ ከመጣ በኋላ አሁን የሚሰራውን የኤምፔሳ ንግዱን ከመጀመሩ በፊት ለስምንት ዓመታት ያህል ፎቶ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ ተሰርቷል። ኢስሊ በተወሰነ መልኩ መርካቶን ያስታውሰዋል። ግርግሩንም የሚያውቀው ነው።
"ኢስሊ ጥሩ ሰፈር ነው። እንደ ወንድም እህት ተፈቃቅረን፤ እንደ ቤተሰብ ቡና አፍልቶ በአብሮነት የምናሳልፍበት ነው" በኢትዮጵያ ያደርጉት የነበረውን ሁሉ በኢስሊም ያደርጉታል። የማርያምም ማኅበር አላቸው።
በተለይም ልክ እንደ አዲስ አበባ 'የእነ እማማ ቤቶች' ተብለው የሚጠሩ ምግብ ቤቶችም በኢስሊ አሉ። "ምግቡ ብቻ አይደለም። የእናትንም ፍቅር ታገኚበታለሽ" ቢልም ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ አይደለም።
የኢስሊ ነጋዴዎች እንዲሁም ሚዲያዎችና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እንዳሳወቁት፤ ስፍራው በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ስደተኞች በፖሊስ ከፍተኛ እንግልት፣ ያለምንም ጥፋት መታሰር እንዲሁም ገንዘብ የሚጠየቁበት ቦታ ነው።
ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል እንደሚሉት ኢስሊ የፍራቻ ቦታ ነው፤ ለስላሳ ፀጉር፣ ፈካ ያለ የቆዳ ቀለም ማለት የተለየ ማንነት ካለ የፖሊስ ኢላማ እንደሚኮን ይሰማሉ።
ከሰሞኑም ዮናስ ከቤቱ በር ወጥቶ ማስክ ሊያደርግ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ፖሊስ ለምን ማስክ አላደረግክም በሚልም አስጠንቅቆታል።
ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሰለሞን ምንም እንኳን ስለ ንግዱም ሆነ ስለ ራሱ ህይወት መናገር ባይፈልግም በኮሮናቫይረስ ምክንያት የፖሊስ ዛቻና ማስፈራሪያ፣ የሙስናው ሁኔታ መንሰራፋቱን ይናገራል።
ከዚህ ቀደምም የነበሩት ሙስናዎች በአሁኑ ሰዓት መልኩን ቀይሮ ሕዝቡ እየተንገላታ ነው ይላል። በዚህም ኢስሊ በተለየ መንገድ ኢላማ ተደርጋለች ይላል።
ይህ ግን የሰለሞን ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ኢስሊ መዘጋቷን ተከትሎ በርካቶች ሰፈሯ የሶማሌዎች መኖሪያ በመሆኗ እነሱ ላይ ያነጣጠረ ነው የሚሉ ትችቶችም ተሰምተዋል።
በዚህም ምክንያት ባለፈው ሳምንት የኬንያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፍሬድ ማቲያንግ የኢስሊ ማኅበረሰብና የሙስሊም ማኅበረሰብ አመራሮችን ባናገሩበት ወቅት "ሰፈሩ መዘጋቱ ሕዝቡን ለመጠበቅ እንደሆነ ተናግረው፤ ብዙዎች ኢስሊ የተዘጋው አብዛኛው ማኅበረሰብ ሶማሌ ስለሆነ ነው የሚለውን ውንጀላ ነው" ብለው አጣጥለውታል።
"ይህ የሁላችንም ችግር ነው። ተባብረን ከሰራን እንወጣዋለን። እንዲህ አይነት አስተሳሰቦች መኖራቸው የሚያሳዝን ነው። እመኑኝ መንግሥት በብሔር እንዲሁም በእምነት ላይ አያነጣጥርም" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, SIMON MAINA
ቅድመ ታሪክ
በቅኝ ግዛት ወቅት እንግሊዞች በዘር እንዲሁም በብሔር የተለያዩ ማኅበረሰቦች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሲወሰን፤ የኢስሊ ሰፈር አመሰራረት ግን በመደብ ላይ ያተኮረ ነበር። ቀደምት ነዋሪዎቹም እስያውያንና የተማሩ አፍሪካውያን ፀሐፊዎች፣ የግንባታ ሠራተኞችና ጫማ ሰሪዎች የሚኖሩበት ነበር።
የኬንያውያንና እስያውያን መኖሪያ መሆኗ አስከ ጎርጎሳውያኑ 1963 ቢቀጥልም በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ሶማሌና ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የበርካታ ስደተኞች መኖሪያ ናት።
በአሁኑ ሰዓት የሶማሌዎች አሻራ ጎልቶ በሚታይባት ኢስሊ የግመል ሥጋ ወጥ፣ በግመል ሥጋ የተሰራ ፖስታ፣ የተለያዩ ቅመሞች የተቀላለቀሉበት የግመል ወተት፣ ሂና፣ ቀሲልና መፋቂያዋ ለየት ያደርጋታል።
የኢስሊው ኬኤፍሲ (የኬንተኪው ፍራይድ ቺክን አይደለም) ኪሊማንጃሮ ፉድ ኮርት ለፍየል ጥብስና ለግመል ጥብስ ተመራጭ ያደርገዋል። ከተለያዩ ቦታዎች የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየውም ኢስሊ ለናይሮቢ የከተማ ግብር ከ25 በመቶ በላይ አስተዋፅኦ የሚደረግባት ሰፈር ናት።
ማስታወሻ፦ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ስም ተቀይሯል














