መጨባበጥ ቀረ? ከመጨባበጥ ውጪ ስላሉ ሰላምታዎችስ ያውቃሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኮቪድ-19 ማኅበራዊ መስተጋብርን እየቀየረ ነው። ለምሳሌ ከሰዎች ጋር ሰላምታ የምንለዋወጥበት መንገድ ተለውጧል።
አሁን ላይ መጨባበጥ፣ መተቃቀፍ አይታሰብምና በርካቶች ወደ ሌላ አማራጭ ፊታቸውን አዙረዋል።
ሰላምታ የምንለዋወጥበት መንገድ ከሰው ሰው ይለያያል። ሰላም ከምንለው ሰው ጋር እንዳለን ቅርርብም ይወሰናል። ስለ ሰብዕናችንም የሚጠቁመው ነገር አለ።
የባህል አጥኚው አሌሳንድሮ ዱራንቲ፤ ሰላምታ መለዋወጥ ትርጉም አዘል መስተጋብር ነው ይላሉ።
ለመሆኑ በተለያዩ አገሮች የተለመዱ ሰላምታ አሰጣጦች ምን ይመስላሉ? ስንል ሰባት አገሮችን ቃኝተናል። ከቻይና እንጀምር. . .
ቻይና
ኮሮናቫይረስ መጀመሪያ የተገኘባት የቻይናዋ ውሃን ግዛት ውስጥ ‘ውሃን ሼክ’ የተሰኘ ሰላምታ ተፈጥሯል። ሰዎች አንድ እግራቸውን ከሌላ ሰው እግር ጋር በማነካካት ሰላምታ የሚለዋወጡበት መንገድ ነው።
የታንዛንያው ፕሬዘዳንት ጆን ማጉፉሊን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ባለሥልጣኖች ‘ውሃን ሼክ’ን ወርሰው፣ በአደባባይ በዚህ መንገድ ሰላም ሲባባሉ ታይቷል።
የባህል አጥኚው ቹዋን ካንግ ሺህ “ሰዎች ውሃን ሼክን በመጠቀም በዚህ አስከፊ ወቅት አብሮነት እንዳልተሸረሸረ ያሳያሉ። ቀለል ያለ፣ አዝናኝም ሰላምታ ነው” ይላሉ።
‘ውሃን ሼክ’ ምናልባትም ለዘመናት የሚቆይ ዓለም አቀፍ ሰላምታ ይሆን?
በእርግጥ ቻይና ውስጥ 3,000 ዓመታት ያስቆጠረ ሰላምታ አለ። መዳፍን አገናኝቶ፣ ወደ ደረት አስጠግቶ፣ ከወገብ ጎንበስ በማለት ይከናወናል። በተለይም በቻይናውያን አዲስ ዓመትና ሠርግ ላይ ይዘወተራል።
ኒው ዚላንድ
የኒው ዚላንድ ቀደምት ማኅበረሰብ ‘ሆንጊ’ የተባለ ሰላምታ አላቸው። አንድ ሰው አፍንጫውንና ግንባሩን ከሌላ ሰው አፍንጫና ግንባር ጋር አነካክቶ ሰላም ይላል።
የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መሆኑን ከማወጁ ከሳምንታት በፊት ማኅበረሰቡ ይህንን ሰላምታ ያቁም ተብሎ ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትር ጀሲንዳ አርደንም ‘ሆንጊ’ ይቁም፤ መጨባበጥና መተቃቀፍም ይቅር ብለው ነበር።
ዜጎች አሁን በአይን ወይም አገጭ ከፍ በማድረግ ሰላምታ ይሰጣጣሉ የሚሉት ፕሮፌሰር ራንጊ ማታሙና ናቸው።
‘ሆንጊ’ ከማኅበረሰቡ ጋር የተቆራኘ ባህል ነው። የደን አምላክ ታኔ በመጀመሪያዋ ሴት ሕይወትን ከዘራበት መንገድ ጋር የተሳሰረ ነው እብለው ያምናሉ።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1918 ‘ኢንፍሉዌንዛ’ ወረርሽኝ ሲሰራጭ ሰላምታው እንዲቆም ተደርጎ ነበር። ፕሮፌሰሩ “የጥንት ልማዶቻችን ለአሁኑ ማኅበረሰብ ካልሠሩ እንለውጣቸዋለን” የሚሉትም ለዚህ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፈረንሳይ
ፈረንሳውያን ጉንጭ ለጉንጭ ይሳሳማሉ። ‘ቢስስ’ ይባላል።
ልክ እንደ ኒው ዚላንዱ ‘ሆንጊ’ ሰላምታ የፈረንሳይ ሰላምታም በ ‘ኢንፍሉዌንዛ’ ወረርሽኝ ጊዜ ታግዶ ነበር።
ፈረንሳይ እንቅስቃሴ ከማቆሟ በፊት 60 በመቶ ዜጎቿ ጉንጭ ለጉንጭ ይሳሳሙ ነበር። ከዛ ግን ወደ ስድስት በመቶ ወርዷል።
የፈረንሳይ መንግሥት ‘ቢስስ’ ቢቆምም፤ ጉንጭ ለጉንጭ ስትሳሳሙ የምታወጡትን ድምፅ በመጠቀም በሩቁ ሰላም ተባባሉ ብሏል።
የባህል አጥኚዋ ክላውዲ ጋውተው፤ ‘ቢስስ’ በቶሎ ማቆም አልተቻለም ነበር ይላሉ። በተለይ በሴቶች ዘንድ የሚዘወተረውን ሰላምታ መተው ከባድ ነበር።
እስከ 1960ዎቹ ድረስ በጣም በሚቀራረቡ የቤተሰብ አባላት መካከል የሚሰጥ ሰላምታ እንደነበርም ያስታውሳሉ።
“ሰላምታው የባህሉ አካል ነው” የሚሉት አጥኚዋ፤ አካላዊ ርቀት መጠበቅ ከመታወጁ በፊት ይህን ሰላምታ እምቢ ማለት ከደንብ መውጣት እንደነበር ያስረዳሉ።
ጉንጭ ለጉንጭ የመሳሳም ድምፅን ተጠቅሞ ሰላምታ መለዋወጥ ይቀጥል ይሆን?
አጥኚዋ እንደሚሉት ከሆነ፤ ማኅበረሰቡ ዘንድ ስለ ጤና የሚኖረው አመለካከት ይህ ሰላምታ እንዲቀጥል ወይም እንዲቆም ያደርጋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታንዛንያ
የታንዛንያ ባህል አንድ ሰው በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ቦታ መሠረት ያደረገ ነው ሲሉ ባህል አጥኚው አሌክሳንደር ሙጃጌ ይናገራሉ።
ታዳጊዎች ከወገባቸው ጎንበስ ብለው ለአዛውንቶች ሰላምታ ይሰጣሉ። በምላሹ አዛውንቶች የታዳጊዎችን ጭንቅላት ይዳብሳሉ። በሌላ በኩል አንድ ሰው በማኅበሰቡ ባለው ሥፍራ መሠረት፣ ዘለግ ላለ ጊዜ በመጨበጥ፣ በማቀፍ ወይም ጉንጭ በመሳም ሰላም ሊል ይችላል።
አሁን ላይ ሰላምታ የሚሰጠው በእግር ሆኗል። የቻይናው ‘ውሃን ሼክ’ ታንዛንያ ደርሷል።
በሩቁ ከወገብ ጎንበስ ብሎ ሰላም መባባልም እየተለመደ መጥቷል።
“ኮቪድ-19 እንድንራራቅ አድርጓል። እግር የተፈጠረው ለመራመድ ነው። በእገር ሰላም መባባል ፍቅርን፣ መተሳሰብን፣ መከባበርን ያሳያል?” ሲሉ አጥኚው ሐሳባቸውን ገልጸዋል።
የአፍና የፊት መሸፈኛ ጭንብል፤ ሰዎች በፊት እንቅስቃሴ እንዳይግባቡም አድርጓል። ለምሳሌ ቀድሞ ከንፈር በማጠማዘዝ ‘በሐሳቡ ተስማምቻለሁ’ ማለት ይቻል ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቱርክ
የቱርክ ሰላምታ ከእስልምና ጋር የተቆራኘ ነው። ታዳጊዎች የጎልማሳ ዘመዳቸውን አይበሉባ ስመው ግንባራቸው ላይ ያሳርፉታል።
በበዓል ወቅት፤ ጓደኛሞች፣ የሥራ አጋሮችም ጉንጭ ለጉንጭ ሁለት ጊዜ ይሳሳማሉ።
ጋዜጠኛው ኬናን ሻርፕ “ጉንጭ ሁለት ጊዜ የሚሳምበት ምክንያት አለው፤ ሰው ሲሳም ጎዶሎ ቁጥር መሆን የለበትም” ይላል።
ለቱርኮች ሰላምታ መስጠት እንግዳ ተቀባይነት፣ ሰው ያለውን ዋጋ መሳያም ነው። የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ተከትሎ ለበሽታው የማያጋልጥ ሰላምታ ለማግኘት የእስልምና ታሪክን ፈትሸዋል።
‘ኢቫላህ’ ዘመናት ያስቆጠረ ሰላምታ ነው። አንድ ሰው ክንዱን ደረቱ ላይ አድርጎ ለሌላው ሰላምታ ይሰጣል። እርስ በእርስ መከባበርን የሚያንጸባርቅም ነው።
ቃሉ አረብኛ ሲሆን፤ በፈጣሪ እናምናለን ማለት ነው። በመላው ዓለም የእስልምና ተከታዮች ዘንድም ይዘወተራል።
ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ
የጤና ሚንስትር መሰባሰብን ማገዱን ተከትሎ፤ መተቃቀፍ ቀርቷል። ባህላዊው አፍንጫ መሳምም እንዲሁ ቀርቶ ክንድን ደረት ላይ አሳርፎ በሩቁ ሰላም በመባባል ተተክቷል።
ሰላምታው ድሮም በተቃራኒ ጾታ መካከል የተለመደ ነበር። በሌላ በኩል ሴቶች ጉንጭ ለጉንጭ ይሳሳሙ የነበረ ሲሆን፤ ኮሮናቫይረስ ይህ አይነቱን ሰላምታ አሰጣጥ አስቀርቷል።
ጸሐፊ ናታሻ አማር እንደምትለው፤ ኮቪድ-19 የአንድ ማኅበረሰብ አባል መሆንና ከሰው ጋር መቀራረብ ዋጋ እንዳለው እንድንረዳ አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አፍጋኒስታን
በአፍጋኒስታን ያሉ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ሰላም ሲባባሉ አክብሮትን እንዲሁም ፈጣሪና አገር መውደድን ያሳያሉ። መጨባበጥ፣ መተቃቀፍና መሳሳም ይዘወተራሉ።
በአንዳንድ ማኅበረሰቦች እስከ ስምንት ጊዜ መሳሳም የተለመደ ነው። ሰዎች ሲያወሩም በጣም ተጠጋግተው ነው።
ፕሮፌሰር ኮስሚን ኢቫንሲዩ እና ቪያና ፖፒካ እንደሚሉት፤ ጥሩ ጠረን ያለው ሰው ጥሩ ቀልብ እንዳለው ይታመናል።
በአፍጋኒስታን መተቃቀፍ፣ መሳሳም የፍቅር መግለጫ ነው። በርከት ያሉ ሰዎች ተሰባስበውም አክብሮታቸውን ያሳያሉ። ወታደራዊ ሰላምታ መስጠትም የአክብሮት ማሳያ ነው።
ሆኖም ግን ኮሮናቫይረስ ነገሮችን ለውጧል። ሩቅ ለሩቅ እጅ ማውለብለብ አዲሱ ሰላምታ ከሆነም ሰነባብቷል።














