"ለሃያ አመታት ያህል ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስዘጋጅ ነበር" የንፅህና ሱሰኛው

በሳሙና እጅ መታጠብ የሚያሳይ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Emma Russell

የመፍራት ደረጃችን ቢለያይም፤ ብዙዎቻችን ጀርምን እንፈራለን። የቢቢሲው ጋዜጠኛ ፒተር ጎፊን ጀርሞችን በመፍራት፣ ጀርሞችን ከቤቱም ሆነ ከአካባቢው ሙሉ በሙሉ እንዲወገዱ ለሁለት አስርት አመታት ጥሯል።

ህይወቱ በሙሉ አካባቢውን በንፅህና ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ ነው። ንፁህ ካልመሰለው ያስጨንቀዋል፤ ይሸበራል። ዓለም የምትገለበጥና መጥፎም ነገር የሚከሰት ይመስለዋል።

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ መታጠብ፣ ፀረ ተህዋሲያን (ዲስኢንፌክታንት) መጠቀም በሚመከርበትና ብዙዎች ብዙዎች ድግሞ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ በሚጥሩበት በዚህ ወቅት ነገሩ ለፒተር ግን የህይወቱ አካል ነው።

ከሰሞኑ በማዕድ ቤት ቁጭ ብዬ የገዛኋቸውን የታሸጉ ጥራጥሬዎችን በፀረ-ተህዋሲያን እያፀዳሁ ነበር፤ እናም ለብዙዎች ይህ ምናልባት አዲስ ሊሆን ይችላል። ለእኔ ግን በባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያደረግኩት ነው። ድንገት አንድ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ ፤ እሱም ላለፉት ሃያ ዓመታት ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስዘጋጅ እንደነበር።

ገና በአስራዎቹ እድሜ ነው ኦሲዲ (ኦብሰሲቭ ኮምፐልሲቭ ዲስኦርደር) እንዳለብኝ የተረዳሁት። (ኦሲዲ የማይፈለግና ለመቆጣጠር የሚያስቸግር ሃሳብ በሰዎች እዝነ ህሊና እየተመላለሰ የሚያስጨንቅና፤ አንድን ነገርም ሱስ በሚባል ሁኔታ በተደጋጋሚ ከማድረግ ጋር ይገናኛል።)

ሁለት ሦስተኛውንም የህይወት እድሜዬን ያሳለፍኩት ስለጀርሞች በመጨነቅ ነው፤ እንዴት ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ይተላለፋሉ? እንዴትስ ማጥፋት ይቻላል? የሚለው የዘወትር ጭንቀቴ ነበር።

በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ስጋት የሆነውን የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመከላከል የሚደረጉ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ስሰማ ምን ያህል ቀድሜ እንደሄድኩም እረዳለሁ።

በዘመናት የዳበረ ልምድ

ከቤት ውጭ ያሉ ሰዎች ጋር አካላዊ ንክኪን ማስወገድ፣ ሌላ ሰው የነካውን ማንኛውንም ነገር ድንገት ብነካ መታጠብ፣ ከሱፐር ማርኬት የገዛኋቸውን ማንኛውንም እቃዎች በፀረ ተህዋሲያን (ዲስኢንፌክታንት) ማፅዳት አሁን በዚህ ወቅት ሳይሆን የህይወቴ አካል የሆኑ ተግባራት ናቸው።

በዘመናትም በዚህ ረገድ ጠቢብ ሆኛለሁ ብል ማጋነን አይሆንም። በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮናቫይረስ በፈጠረው የአኗኗር ዘይቤና ባህልም የራሴን ባህርይ አይበታለሁ። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በቫይረሱ ልጠቃ እችላለሁ ከሚል የመነጨ ፍራቻ የሚፈጥረው የፅዳት ሱስ ሙሉ በሙሉ አጥጋቢ ስለማይሆንም ጭንቀት ይፈጥራል።

ሺህዎች ሳይሆኑ ሚሊዮኖች በአሁኑ ወቅት ከኮሮናቫይረስ ጋር በተገናኘ "ሱፐርማርኬት ስገበያይ ያ ግለሰብ ተጠግቶኝ ይሆን?" እጄን በተገቢው መልኩ ታጥቤ ይሆን? ሳሙናው ጀርሞችን ይገላል? እናም በሌሎች ጥያቄዎች እየተረበሹ ነው።

በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ስለ ኦሲዲ የምርምር ፅሁፋቸውን ያበረከቱ ዶክተሮች ይህንን ችግር "የጥርጣሬ እብደት" ብለውታል።

እውነትም በጥርጣሬ ማበድ፤ በተለይም ጭንቀቴን መቆጣጠር ሲያቅተኝ ፤ መቼም ቢሆን እርግጠኛ አለመሆኔን ሳውቅ እውነትም ዶክተሮቹ እንዳሉት ነው።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ደግሞ አሁን ብዙዎች ይሄ ስሜት እየተሰማቸው ነው።

አካላዊ ርቀታችንን መጠበቅ ከቻልን፣ በተደጋጋሚ እጃችንን ከታጠብን፣ አገራት ያሳለፏቸውን ቤት የመቀመጥ መሪያዎችን ከተከተልን በቫይረሱ እንደማንያዝ እርግጠኛ ነን።

ነገር ግን አእምሯችንን የሚነዘንዘን ጥርጣሬና እርግጠኛ አለመሆን፤ ከዚያም ጋር ተያይዞ የሚመጣው ጭንቀት ህይወታችንን ሞልቶታል።

የሚመላለሱት ሃሳቦች መጥፎ ስሜቶች ናቸው። ምናልባት ጭንቀቱ በትንሹም ቢሆን እንድንጠነቀቅ ያደርገን ነበር፤ ችግሩ ግን ከቁጥጥራችን ውጪ ይሆናሉ።

በህይወቴ እንደማውቀው ጥርጣሬው የሚጀምረው "ንፁህ ነኝ" ከሚል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ትንሽ ቆይቶ "ወደ ቀደመው ህይወቴ መመለስ እንዲሁም ኖርማል ልሆን እችል ይሆን" ወደሚለው ያመራል።

ከዚያም በተደጋጋሚ መሞከሩ አድካሚ ያደርገዋል።

መቼ ጀመረ?

ያደግኩት ካናዳ ነው። ገና በአምስት ወይም ስድስት ዓመቴ ነው ጭንቀቴንና ፍርሃቴን መቆጣጠር የተሳነኝ።

አስራ ሁለት ዓመቴ ሲሆን በአጠቃላይ ፍርሃቴ ከንፅህና ጋርና በጀርሞች መጠቃት ጋር የተያያዘ ሆነ። በተለይም ሰዎች ሲናገሩ ምራቃቸው መፈናጠሩና ሽንት ቤት ተፀዳድተው የማይታጠቡ ሰዎች መኖራቸውን ሳስብ ገዳይ የሆኑ ባክቴሪያዎች በሙሉ በሰውነቴ ላይ እየተርመሰመሱ እንደሆነ አስባለሁ።

በር መዝጋት ስፈራ፣ መብራት ማጥፋትም ሆነ ማብራት ስጋት ሲሆንብኝ፤ እጄ እሲከቀላ ኧረ እንዳውም እስኪላጥ ስታጠብ ቤተሰቦቼ መመልከት ጀመሩ።

እድለኛም ሆኜ ደጋፊና ችግሬን የሚቀበሉ ቤተሰቦች አሉኝ። ችግሬን ለመስማትም ሆነ ግራ ያጋባ በነበረው የጤና ሥርዓትም ውስጥ ህክምና እንዳገኝ ጥረት አድርገዋል።

እናም ጭንቀቴን መቆጣጠር እንድችልም መድኃኒቶች ታዘዙልኝ። ከህክምናውም ጋር ሆነ ከንፅህና ሱስ ጋር መኖርን ተለማመድኩት።

ሆኖም የንፅህና ሱሴ ታዳጊም ሆነ በ20ዎቹ እድሜዬ ላይ ህይወቴን አመሳቅሎታል። ሁለተኛ ደረጃም ሆነ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለሁ ከጥናት በላይ ትኩረቴም ሆነ የሚያስጨንቀኝ ጀርሞችና ንፅህና ናቸው።

አንዳንድ ጊዜም ሙሉ ሌሊት ልብሴን ሳጥብ፣ በደንብ ንፁህ ነኝ ብዬም ስለማስብ ሁለት ሦስት ጊዜ ገላዬን እታጠባለሁ። ጓደኞቼም ጋር የነበረኝ ግንኙነት የተገደበ ነበር፤ ይበክሉኛል ብዬም ስለማስብ ብቻ አይደለም። የተለየሁ መሆኑን ካወቁ ያገሉኛል የሚለው ሌላ ጭንቀቴ ነበር።

በምሽት ልብሱን ለማጠብ እየተዘጋጀ ያለ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Emma Russell

ነገሮችን ለማሻሻል ጥረት

በባለፉት አምስት ዓመታት ከኦሲዲ ጋር የተገናኘ ፍራቻዬን በተወሰነ ደረጃ መቆጣጠር ችያለሁ። ፍራቻዬንም መጋፈጥ መረጥኩኝ። በተቻለም መጠን ሊረዱኝ የሚችሉ ነገሮችን ማድረግ እንዲሁም አላስፈላጊ የሚባሉና ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮችንም ላለማሰብ እሞክራለሁ።

የትዳር አጋሬም ትዕግስተኛና የምትረዳኝ መሆኗ ህይወቴን አቅልሎታል።

በሚገርም ሁኔታ ጀርምን ይፈሩና ጭንቀት የነበረባቸው ሰዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ መረጋጋት ታይቶባቸዋል። ምናልባትም የእነሱን የህይወት ዘይቤ ዓለም ስለተቀበለው፤ ዓለምን የሚመለከቱበት መነፅርን ብዙዎች መረዳት መቻላቸው እንዲሁም በርካቶች አስፈላጊ የሚባሉ ጥንቃቄዎች ከማድረጋቸው ጋር ተያይዞ ነው።

ለእኔም ይህ ጉዳይ በተወሰነ መልኩ እውነታ አለው። ሆኖም ወረርሽኙም ደግሞ ፍንትው አድርጎ ያሳየኝም ጉዳይ አለ። በጎዳናዎች ላይ እንኳን ስንተላለፍ በቀላሉ ጀርሞች ከሰው ወደ ሰው መተላለለፍ መቻላቸው በተደጋጋሚ መነገሩ የምጨነቅበት ጉዳይ ምን ያህል እውነት እንደሆነም አሳይቶኛል።

ድሮም ቢሆን ሱፐርማርኬት ሄጄ ስገዛ የሰው ንክኪን በመፍራት የታሸጉ ነገሮችን እመርጥ ነበር። ሆኖም ምግቦች ላይ የከፋ ስጋት አልነበረኝም። አሁን ግን በወረርሽኙ ምክንያት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ጀምሬያለሁ። አዕምሮዬ ታሞ ወደ ነበረበትና ከአስር ዓመት በፊት ወደነበረው ጥንቃቄም በተወሰነ መልኩ ተመልሻለሁ።

የኮሮናቫይረስ ያጠናከረው ስጋት

ከሱፐርማርኬት ስመለስ የገዛኋቸውን እቃዎች በሙሉ ቤቴ ውስጥ ገለል አድርጌ አስቀምጣቸዋለሁ። ጫማዬንም አውልቄ በሩ ላይ በጥንቃቄ አስቀምጣለሁ።

እጄንም በደንብ እታጠባለሁ። የገዛኋቸውንም ነገሮች በሙሉ በውሃ፣ በፀረ ተህዋሲያን አፀዳለሁ። በተደጋጋሚም እጄን አታጠባለሁ።

ከዚያም መደርደሪያ ወይም ፍሪጅ ውስጥ እከታለሁ። ይሄ አዲስ ልምድም ሆነ ባህርይ አይደለም ነገር ግን ለዓመታት ላስወግደው ያልቻልኩት የንፅህና ሱስ ነው። ምናልባት ብዙዎች እነዚህን ተግባራት ሊያከናውኑ ይችላሉ ሆኖም የእኔ ከባዱ ጭንቀትና የአዕምሮዬም ጤና እክልም እየገጠመኝ ነው።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት የአዕምሮ ጤና መቃወስም ችግሮች እየተፈጠሩ ነው። እርዳታን የሚሹ በርካታ ግለሰቦችም በየአገራቸው ያሉ የጥሪ ማዕከላትን እያጨናነቁ ነው።

በአለም ላይ ያሉ የስልክ ጥሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Emma Russell

በአሁኑ ወቅት ሃገራት ጥለዋቸው የነበሩ አስገዳጅ የቤት መቀመጥም ሆነ የእንቅስቃሴ ገደቧችን መለላት አለባቸው የሚሉ ውይይቶች መበርታታቸውን ተከትሎ ብዙዎች መረጋጋት አልቻሉም።

ትልልቅ መደብሮች፣ ቢሮዎችም ሆኑ ትምህርት ቤቶች የመከፈት እቅድና ሁኔታዎች ወደ ቀደመው ሁኔታ እንዲመለሱ እቅዶች ቢኖሩም ዓለም በኮሮናቫይረስ ከመጣባት ፍራቻና ጭንቀትም በቀላሉ አታገግምም። ለወራትም የሚቀጥል ይሆናል።

በልምድ የዳበረ መፍትሔ

ራሴን ከመፈተሽ እንዲሁም በዓመታት ውስጥ ካደረግኳቸው ህክምናዎች [ቴራፒዎች] የተማርኩት ነገር ቢሆን ፍራቻን መቆጣጠር እንደሚቻል ነው።

ልምዴንም ለማካፈል ያህል፤ ከባለሙያዎች ወይም ከማምናቸውና ከምወዳቸው ሰዎች ጋር ጭንቀቴንና ስሜቴን በተረጋጋ ስሜት ማጋራቴ ብዙ ረድቶኛል።

በህፃንነቴም ካናዳ እንዲሁም ትልቅ ሆኜ በእንግሊዝ የወሰድኩት ቴራፒ ብዙ ረድቶኛል፤ ምናልባት ባለሙያ እንኳን ማግኘት ካልተቻለ በራሳችሁ ማከናወን የምትችሏቸው ጉዳዮች አሉ። ለማንኛውም ሰው ሊጠቅሙም ይችላሉ።

ለምሳሌም ያህል የሚያስጨንቋችሁን ጉዳዮች መዘርዘር፣ ለምን እንዳስጨነቃችሁና ምን እንደሚሰማችሁ መፃፍ። ከዚያም ዝርዝሮቹን በመመልከት ምክንያቶቹን መረጃዎችን በመጠቀም ማጤን፤ እናም ጭንቀታችሁ የተጋነነ፣ መሰረት የሌለው ወይም መፍትሄ ያለው መሆኑንም ትረዳላችሁ።

በተለይም በአስገዳጅ ሁኔታ ቤት የተቀመጡ ሰዎች የጤና ስጋቶች፣ ሥራ ማጣት፣ ሥራዬን ላጣ እችላለሁ የሚል ስጋት፣ ብቸኝነት፣ መገለልና እንዲሁም ደስታ ማጣት ሊያጋጥም ይችላል።

እናም እነዚህን ጭንቀቶች በደንብ በመርመር የተወሰነ ማቅለል ይቻል ይሆናል። ለምሳሌ ብቸኛ ላለመሆን በኣካል እንኳን ማግኘት ባትችሉ ከቤተሰብ ወይም ከጓደኞች ጋር በቪዲዮ ማውራት ሊሆን ይችላል።

ሁኔታዎች ሲረጋጋጉ ደስ የሚል ስፍራ ለመሄድ ማቀድ፤ የባለሙያ ምክርም መስማት ይረዳል። በቫይረሱ የተጠቁ በርካታ ሰዎች አገግመዋል።

እጅን በተደጋጋሚ መታጠብም ሆነ ልብስን ማጠብ ቫይረሱን እንደሚያስወግድ ሳይንሳዊ መረጃዎች መረዳት። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በወረርሽኙ ብቻችንን አለመሆናችንን ልናውቅ ይገባል። ከዓለም ህዝብ ጋር አብረን እየተጋፈጥን ነው።

ጭንቀቴና ፍርሃቴ በሚጨምርበት አንዳንዱ መጥፎ ቀን ለራሴ ያለኝ ስሜት ያሽቆለቁላል። ራሴን እንደ እንግዳና ሞኝ እንደሆንኩ እቆጥራለሁ።

በዓለም ላይም እንደእኔ የሚሰማው ሰው እንደሌለም አስባለሁ። አሁን ግን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የኮሮናቫይረስ ጫና ሁላችንም ጫንቃ ላይ ነው።

በዚህ ቀውስ ወቅት ራሳችንን ብናገልም፤ አንድ ላይ በሕብረት ነው የቆምነው።

ኮሮና
Banner