ኮሮናቫይረስ፡ በአዲስ አበባ በተለምዶ ኮካና አብነት የሚባሉት አካባቢዎች የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት ቁጥጥር እየተደረገ ነው

በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ አፋቸውን የሸፈኑ እናት

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩ ከተገለጸ ወዲህ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር (88 ሰዎች) ይፋ የተደረገው ትናንት ነበር።

የጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሚሰጧቸው ዕለታዊ መግለጫዎች ላይ በበሽታው የተያዙት በርካታ ሰዎች የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ነው።

በአምስት ተከታታይ ቀናት ብቻ አንድ መቶ አምሳ አንድ ሰዎች በአዲስ አበባ በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል። ግንቦት 12፣ 2012 ዓ. ም. ዘጠኝ ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በተከታታይ ባሉት ቀናት 3፣ 18፣ 48 ከዛም 73 ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸው ይፋ ተደርጓል።

ከአዲስ አበባ በዋነኛነት በልደታ ክፍለ ከተማና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። በልደታ ክፍለ ከተማ እስካሁን 104 ሰዎች በበሽታው እንደተያዙና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ደግሞ 28 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተገልጿል።

የጤና ጥበቃ ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፤ የቫይረሱ ሥርጭት በተስፋፋባቸው ክፍለ ከተሞች የእንቅስቃሴ እገዳ ሊደረግ እንደሚችል መናጋራቸውም ይታወሳል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ከቫይረሱ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ቅኝት የማድረግ ስራ ዋነኛ ተግባር መሆኑን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ገልፀዋል።በወቅቱ በአዲስ አበባ ከተማ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተደረገ ቅኝት ከቫይረሱ ጋር ንክኪ ከነበረው አንድ ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸው 32 ግለሰቦች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋልም ብለዋል፡፡

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ በወረዳው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በተደረገ ድንገተኛ ምርመራ አርባ (40) 'የህግ ታራሚዎች' እንደሚገኙበት በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

በእነዚህ አካባቢዎች ምን እርምጃ ወሰደ?

ልደታ ክፍለ ከተማ

በልደታ ክፍለ ከተማ በሽታው በስፋት የተሰራጨበት ወረዳ ሦስት በተለምዶ ኮካና አብነት የሚባሉት አካባቢ፣ እንቅስቃሴ መገታቱን አንድ ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁ የክፍለ ከተማው ባልደረባ ለቢቢሲ ተናግረዋል። የክፍለ ከተማው ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ተሬሳ ግን ምንም ዓይነት የተጣለ ገደብ የለም ሲሉ አስተባብለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከቤት እንዳይወጡ ተደርጎ፣ ምግብ እየቀረበላቸው መሆኑንን ለቢቢሲ የተናገሩት እኚህ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የክፍለ ከተማው ሠራተኛ ናቸው።

በልደታ ክፍለ ከተማ በኮቪድ-19 ተይዘው የነበሩ ሴት ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ በበሽታው መያዛቸው ስለተረጋገጠ ከሟቿ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች የመለየት ሥራ እንደተሠራ ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የአካባቢውን ነዋሪዎች በስፋት መመርመር (ማስ ቴስቲንግ) የጸረ ተዋህሲያን ርጭትም ተካሂዷል።

የልደታ ክፍለ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ተሬሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በክፍለ ከተማውም ሆነ በተጠቀሱት ስፍራዎች እስካሁን ድረስ ምንም የተጣለ እንቅስቃሴ ገደብ የለም ብለዋል።

የክፍለከተማው ጤና ቢሮ ወረርሽኙ በዓለም ላይ ከተከሰተ ጀምሮ በዓለም ጤና ድርጅትና በጤና ሚኒስቴር የሚሰጡትን የመከላከል ምክሮች ለነዋሪዎች በማስተማር ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ሲስራ እንደነበር ገልፀዋል። በአሁኑ ሰዓትም ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልፀው፣ በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮች ተግባራዊ እንዲደረግ እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ግን በአስሩም ወረዳዎች እንቅስቃሴ እንዳልተገታ፤ የክፍለ ከተማው በሽታ የመከላከልና የመቆጣጠር ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ለበን ጸጋዬ ተናግረዋል።

“በአካባቢው እንቅስቃሴ ይቁም ቢባል ምጣኔ ኃብቱ ይጎዳል። በከፍተኛ ኃላፊዎች ደረጃ የሚወሰን ነው። እንደ ጤና ዘርፍ ባለሙያ ግን በመርካቶ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ስላለ፣ የአገር አቋራጭ ትራንስፖርት ያለበት ቦታ በመሆኑም ለተወሰነ ጊዜ እንቅስቃሴ ቢቆም መልካም ነው እንላለን” ሲሉ ያስረዳሉ።

በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከመንቀሳቀሱ አንጻር በሽታው በስፋት ሊሰራጭ ይችላል የሚል ስጋት አለ።

አሁን ላይ የበሽታውን ምልክት ያሳዩ ሰዎች ሲገኙ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ይደረጋል። ከነዚህ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎችን የሚያስስ አምስት ቡድን እንዳለም አቶ ለበን ተናግረዋል።

በሽታው በስፋት የተሰራጨባቸው ወረዳ አንድ፣ ሰባትና ስምንት ውስጥ በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራች ሰዎች ተለይተው በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የማድረግ፣ ሙቀት የመለካትና ማኅበረሰቡን የማስተማር ሥራ እንደሚሠሩም አክለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ምን ይላሉ?

አቶ ንጉሤ ሰንበታ የሚኖሩት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነው። የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ በግል ሥር ዘርፍ ተሰማርተዋል።

ቤታቸው ለልደታ አካባቢ አዋሳኝ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ንጉሤ፤ በኮቪድ-19 ሳቢያ ሕይወታቸው ያለፈ ሴት ይኖሩበት በነበረ አካባቢ፤ “ሁለት ቅያሶች በፖሊስ ተከበው፤ መተላለፊያቸው በገመድ ታስሯል፤ ፖሊሶች ሰው እንዳይወጣ ይጠብቃሉ” ይላሉ።

የአካባቢው ማኅበረሰብ እምብዛም የእለት ከእለት እንቅስቃሴውን እንዳልተለወጠ አቶ ንጉሤ ያስረዳሉ።

“የመጀመሪያ ሰሞን ሰው የተሻለ ይጠነቀቅ ነበር። አሁን ግን ሰው እንደተለመደው ሥራ እየሠራ ነው፤ ይህም አስፈሪ ነው” ብለዋል።

በአካባቢው የእጅ ጓንት አድርገው የሚገበያዩት ዳቦ ቤቶች ብቻ እንደሆኑም ያክላሉ።

“እዚ አካባቢ የሚኖረው ሰው በድህነት አረንቋ ያለ በመሆኑ ገንዘብ ለማግኘት የግድ እለታዊ ተግባሩን ያከናውናል” ይላሉ።

በአብነት አካባቢ የሚሠራው መኮንን ለገሠም የአቶ ንጉሤን ሀሳብ ይጋራል። የአካባቢው ነዋሪዎች የዘወትር እንቅስቃሴያቸውን ማከናወናቸውን እንደገፉበትም ይናገራል።

መኮንን እንደሚናገረው፤ የልደታና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች በከፍተኛ ሁኔታ ለቫይረሱ ተጋላጭ መሆናቸው ከተገለጸ በኋላም ብዙም የሰው እንቅስቃሴ አልተለወጠም።

“ነዋሪው አቅመ ደካማ ስለሆነ ጠዋትም ከሰዓትም አስቤዛ ለመግዛት ደጋግሞ ከቤት ይወጣል” ይላል።

ዛሬ ጠዋት በአካባቢው የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ነዋሪዎች እንዲደግፉ የሚያሳስብ መልዕክት መሰቀሉን ገልጸዋል።

ኮሮና
Banner