ኮሮናቫይረስ በባህረ ሰላጤው ያለውን ውጥረት ሊያረግብ ይችላል ተባለ

ወርቅ ሻጩ ጭምብል እና ጓንት አድርጎ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ኢራንን ጨምሮ ስድስቱ የባህረ ሰላጤው አገራት ከኮሮናቫይረስ ስርጭት በኋላ "ተዳክመው፣ ተጎድተው እና ደህይተው" ይገኛሉ ሲሉ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዶ/ር አንዋር ጋርጋሽ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ሚንስትሩ ለዚህ ሁሉ ምላሽ በቀጠናው ያለውን ውጥረት ማርገብ ነው ብለዋል። ቫይረሱ የሁሉም ጠላት ነው ያሉት ሚንስትሩ፤ የቫይረሱ ስርጭት በቀጠናው ያለውን ግጭት እና ውጥረት ለማብረድ አቅም እንዳለው ተስፋ አድርገዋል።

'ዎርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው፤ ባህሬን፣ ኢራቅ፣ ኩዌት፣ ኦማን፣ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችን የባህረ ሰላጤው አገራት ናቸው ሲል ይዘረዝራል።

በየመን እየተካሄድ ባለው ጦርነት የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች (ዩኤኢ) እና ኢራን በሁለት ጎራ ተከፋፍለው ይፋለማሉ። ዩኤኢ በየመን ያሰማራቻቸው ወታደሮቿ በኢራን የሚደገፉትን የሁቲ አማጺያንን ይወጋሉ።

በሊቢያ እየተካሄደ ባለው ጦርነትም ቢሆን ሳኡዲ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራውን ኃይል ሲደግፉ ሌላኛው የባህረ ሰላጤው አገር ኳታር በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ለተሰጠው የትሪፖሊ መንግሥት ድጋፍ ታደርጋለች።

ባህሬን፣ ሳኡዲ እና ዩኤኢ በሌላ በኩል ከኳታር አለመግባባት ውስጥ ይገኛሉ። የመን በበኩሏ ለአምስት ዓመታት በዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቃ ትገኛለች።

ይህ ጦርነት የጤና ስርዓቷን እጅጉን ያዳከመ ሲሆን የኮሮናቫይረስ ስርጭት የሚከፋ ከሆነ ደካማውን የጤና ስርዓቷን ሙሉ በሙሉ ሊያንኮታኩት ይችላል የሚል ስጋት በሁሉም ዘንድ አለ።

የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችንም ቢሆንም ቫይረሱ ሳይፈትን አላለፈም። በርካታ የደቡብ ኢሲያ አገራት ዜጎች በሚኖሩበት የንግድ ከተማዋ ዱባይ አንድ አካባቢ ቫይረሱ በስፋት ተሰራጭቶ ነበር። ይህ አካባቢ ዝግ እንዲሆን ተደርጎ ከቆየ በኋላ ዳግም ከመከፈቱ በፊት የጸረ-ተዋሲያን ርጭት ተከናውኗል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ጠንካራ እርምጃ በምትወስደው እና በቀን እስከ 40ሺህ ሰዎችን በምትመረምረው ዩኤኢ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ ነው።

ዶ/ር አንዋር ጋርጋሽ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ወደ በፊት በህክምና ዘረፉ ብዙ መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ እንዲደረግ እንደሚያደርግ ቅድመ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

"ትልቁ ፈተና የሚሆነው የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ነው። የነዳጅ ዋጋም እየቀነሰ ነው" ያሉ ሲሆን፤ የቀጠናው መንግሥታት የሚፈተኑት ከቫይረሱ ስርጭት በኋላ በሚኖራቸው የአመራር አቅም ነው ብለዋል።

ኮሮና
Banner