አዲስ አበባ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ማዕከል ለምን ሆነች?

አዲስ አበባ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Andia

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ሁለት ወራት አልፈውታል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ሐሙስ ማምሻውን የተገለፀውን የሐረሪ ክልልን ጨምሮ በስምንት ክልሎችና በሁለት የከተማ መስተዳደሮች የቫይረሱ ስርጭት ይገኛል።

በአገሪቱ ቫይረሱ ከተገኘባቸው 494 ሰዎች ውስጥ 304 ሰዎች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ ፣ በተለይ በልደታ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች የቫይረሱ ስርጭት ይበልጥ መስፋፋቱ ተገልጿል፡፡

ከጤና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ከልደታ ክ/ከተማ 104 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ፣ ከአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ደግሞ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 28 ደርሷል።

ከዚህም በተጨማሪ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ምንም አይነት ንክኪ ያልነበራቸው እንዲሁም የጉዞ ታሪክ ሌላቸው ሰዎች ነገር ግን በከፍተኛ ሁኔታ በቫይረሱ ተይዘው የሚገኙት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እና በልደታ መሆኑም ተገልጿል።

አዲስ አበባ የቫይረሱ ማዕከል ለምን ሆነች? የሚሉ የተለያዩ መላምቶች እየተሰጡ ሲሆን በአብዛኛውም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንዲሁም የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት መገኛ ከመሆኗ አንፃር ቫይረሱ ከተነሳበት እለት ጀምሮ በርካታ የውጭ መንገደኞችን ማስተናገዷ የሚጠቀስ ነው።

መንገደኞቹም ኢትዮጵያ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ መመሪያን ከማሳለፏ በፊት በቫይረሱ ተይዘው ከነበረና በከተማዋ በሚያደርጉትም እንቅስቃሴ ከማህበረሰቡ ጋር ግንኙነት ፈጥረው ከሆነ ድንገት በዛ መንገድ ተላልፎ ይሆናል በማለት አስተያየታቸውን የሚሰጡ በርካቶች ናቸው። መንገደኞቹ ወደ ሃገር ውስጥ ሲገቡ የሙቀት ልኬት ተደርጎላቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል በርካታዎቹ የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ ከነዚህም የምትጠቀሰው ዱባይ አንዷ ናት። ከዱባይ የሚመጡ በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖሪያቸውም ሆነ ንግዳቸው አዲስ አበባ በመሆኑ ንክኪ ሳይፈጠር አይቀርም የሚሉም አሉ።

ሆኖም ዋና ከተማዋ የቫይረሱ ማዕከል መሆኗን ተከትሎ በተለይም በተጠቀሱት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች በእጅጉ በተጠጋጋ ስፍራ መኖራቸው ቫይረሱ ስርጭት እንዳይስፋፋ እንደሚያሳስብ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በአፍሪካ ትልቁ የገበያ ማዕከል፣ መርካቶ የሚገኝበት መሆኑና፤ ከዚህ የገበያ ስፍራ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በርካታ መሆናቸው ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ እስካሁን ድረስ በመጀመሪያ ዙር የቤት ለቤት ልየታ ከ900 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶችን፣ 3.1 ሚሊየን የከተማዋ ነዋሪን፣ በማዳረስ ስለኮቪድ-19 ግንዛቤ የመስጠትና ልየታ መሰራቱን ተገልፏል። አሁንም ሁለተኛ ዙር እየተሰራ መሆኑን ቢሮው ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ሐሙስ ማምሻውን በሐረሪ ክልል አንድ ሰው በኮቪድ-19 መያዙን ተከትሎ በመላው አገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ወደ 399 አድጓል። በክልል ደረጃም ካየነው በአሁን ሰዓት ከጋምቤላ ክልል በስተቀር በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ይገኛሉ።

እስካሁን ድረስ ላይ በአገሪቱ ካሉ ወደ 80 የሚጠጉ ዞኖች በ40ዎቹ የኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች እንደሚገኙ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

በሁለት ወራት ውስጥ በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ከተመዘገበው ሰዎች ቁጥር ግን ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተመዘገቡት ከፍ ያለ ሆኖ መታየቱን የጤና ሚኒስትርና የኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዚህ ሳምንት በሰጡት መግለጫ ላይ ገልፀዋል።

እንደ መግለጫው ከሆነ በመጀመሪያ ሁለት ወራት 135 ሰዎች ተይዘው የነበረ ቢሆንም በባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ የ230 ሰዎች ጭማሬ አሳይቷል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, 20 ሺህ የፊት ጭምብሎችን ለአረጋዊያያን ለማከፋፈል እየሰራች ያለችው ጀነት ለማ

117ሰው በአምስት ቀን የተያዘበት ሳምንት

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ዕለት 35 ሰዎች በኮሮና መያዛቸው በምርመራ መታወቁ የተጠቀሰበት ሪፖርት በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 352 አድርሶት ነበር።

ይህ ቁጥር እስካሁን በቫይረሱ ተይዘው በአንድ ቀን ከተመዘገቡ ሁሉ ትልቁ መሆኑ ይታወቃል። በማግስቱ 14 ሰዎች መያዛቸውን ተከትሎ በአንድ ላይ በሁለት ቀን ብቻ 49 ሰዎች መያዛቸው ተመዝግቧል።

ረቡዕ ላይም ለ3460 የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 24 ሰዎች የኮሮና ይረስ እንደተገኘባቸው ተገልጿል። በዚህም በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ሶስት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ (389) ደርሷል። በሳምንቱ ሶስት ቀናት ብቻ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 73 አድርሶታል።

ሐሙስ ዕለት በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 10 መሆናቸውም የአገሪቱን አጠቃላይ ቁጥር 399 ሲያደርሰው አርብ ዕለት በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠውን 34 ሰዎች ጨምሮ በዚህ ሳምንት ብቻ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 117 ደርሷል።

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች በተገኘበት ወቅት የውጪ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሰዎች ላይ ሰፋ ብሎ ይታይ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው እንዲሁም ምንም አይነት ንክኪም ሆነ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ሰዎች እየበረከቱ መምጣታቸውን የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መግለጫ አመላክቷል።

ጤና ሚኒስትርና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት በተደጋጋሚ በሚሰጡት መግለጫዎች ላይ እንደሚያነሱት ኀብረተሰቡ መዘናጋትና ቸልተኝነት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

ጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስትትዩት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል አራቱ መ ዎችን ተግባራዊ እንዲያደር ይመክራሉ።

እነዚህም መራራቅ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ መታጠብ፣ እጅን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ መታጠብ፣ መቆየት፣ አስገዳጅ ካልሆነ በስተቀር ቤት ውስጥ መቆየት፤ መሸፈን ከቤት ውጪ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የሚሉ ናቸው።

ኮሮና
Banner