በጥሬ ገንዘብ ዝውውር ላይ የተጣለው ገደብ ለምን አስፈለገ?

የፎቶው ባለመብት, Elias Meseret
በኢትዮጵያ ከባንኮችና ከማክሮ ፋይናንስ ተቋማት በሚወጣ የጥሬ ገንዘብ ላይ የተጣለው እገዳ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል። ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመሪያ ተቋማትና ግለሰቦች ከባንኮች በቀንና በወር ውስጥ በሚያወጡት የጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ ገደብ ጥሏል።
በዚህም መሰረት አንድ ግለሰብ በቀን እስከ 200 ሺህ ብር እንዲሁም በወር እስከ 1 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ከባንኮች ማውጣት የሚችል ሲሆን፤ ተቋማት ደግሞ በቀን እስከ 300 ሺህ ብር እና በወር እስከ 2.5 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንደሚችሉ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶክተር) ይህንን እርምጃ መውሰድ ያስፈለገው "የገንዘብ ዝውውርን ሥርዓት በማስያዝ ወንጀልንና የግብር ስወራን ለመከላከል ይረዳል" በሚል ነው ብለዋል።
ይህን የብሔራዊ ባንክ እርምጃን በተመለከተ የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች አሉ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዋሲሁን በላይ አንድ አገር ላይ የኢኮኖሚ ፖሊስ ሲወጣ፣ ምጣኔ ሃብቱ እንዲረጋጋ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚው ባለበት ሁኔታ እንዲቀጥል ሲፈለግ ሁለት ዓይነት ኃይለ ፖሊሲዎችን እንደሚከተሉ ያስረዳሉ።
በጀት ምን መምሰል አለበት፣ ሰዎችና የንግድ ተቋማቶች መክፈል ያለባቸው ግብር ምን ይመስላል ተብሎ የሚወሰንበትን እና የገቢዎች ሚኒስቴርና የገንዘብ ሚኒስቴር የሚቆጣጠሩት ፊሲካል ፖሊሲ አንዱ ሲሆን፣ ሞኒተሪ ፖሊሲ ደግሞ የብሔራዊ ባንክ የሚቆጠጣረው መሆኑን ያስረዳሉ።
ብሔራዊ ባንክ ሲቋቋም ጀምሮ የአገሪቱ የገንዘብ አቅርቦት ምን መምሰል አለበት? ምን ያህል ገንዘብ ታትሞ በገበያ ውስጥ መሰራጨት አለባቸው? የሚለውን የመቆጣጠር የሥራ ድርሻው እንዳለው ያብራራሉ።
በተጨማሪ ደግሞ በባንኮች በኩል ያለውን የወለድ መጠን፣ የሚቆጣጠረው ብሔራዊ ባንክ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዋሲሁን፣ ብሔራዊ ባንክ በትናንትናው ዕለት ካሉት ሁለት ትልልቅ ስልጣኖች መካከል በመጠቀም የገንዘብ አቅርቦት በገበያው ምን መምሰል እንዳለበት ወስኗል ሲሉ ያስረዳሉ።
የመንግሥት ውሳኔ መነሻ ምክንያቶች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
እንደ ምጣኔ ሃብቱ ባለሙያ አስተያየት ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የገንዘብ መጠን ላለፉት ብዙ ዓመታት በእርግጠኝነት ማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው።
"በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከ700 እስከ 800 ቢሊየን ብር ድረስ በገበያው መሰራጨቱ ይታወቃል የሚሉት የምጣኔ ሃብቱ ባለሙያ እርሱንም ቢሆን በእርግጠኝነት ለማወቅ አስቸጋሪ ነው" ሲሉ ያለውን ፈተና ያብራራሉ።
ስለዚህ እዚህ ገበያ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ማወቅ እንደሚያስፈልግ በማንሳት "የገንዘብ መጠኑ የማይታወቅ ከሆነ የተለያዩ ሕጋዊ ያልሆኑ የንግድ ሥርዓቶች ሊበራከቱ ስለሚችሉ ብሔራዊ ባንክ ያንን ለማወቅ አስቦ እንደወሰነው እገምታለሁ" ይላሉ።
ሌላው መንግሥት ባይጠቅሰውም የገንዘብ እጥረት የአገሪቱ አንዱ ችግር መሆኑን ይጠቅሳሉ። "ጥሬ ገንዘብ አቅርቦት በጣም እያነሰ ነው። የኮሮናቫይረስ ክስተትን ተከትሎና በሌሎችም ምክንያቶች ሰዎች ያላቸውን ገንዘብ በእጃቸው መያዝ ይፈልጋሉ" የሚሉት ባለሙያው ለመንግሥት የገንዘብ እጥረት ገጥሞኛል ብሎ መናገር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ ከባድ መሆኑን ይናገራሉ።
"ወረርሽኙን ተከትሎ ሰዎች ለመድኃኒት፣ ለሕክምናና ለምግብ የሚሆኑ ወጪዎችን ብቻ ነው እያወጡ የሚገኙት" የሚሉት ባለሙያው በተጨማሪም ነገ በሚሆነው ነገር ላይ ተስፈኛ መሆን አለመቻል ገንዘብን በባንክ ለማስቀመጥ ፍላጎት እንደሚያሳጣ ይጠቅሳሉ።
"አሁን በከፍተኛ ሁኔታ ገንዘብ ከባንክ ቤቶች እየወጣ መሆኑ ግልጽ ነው" በማለትም ከበሽታው በፊትም ቢሆን የልማት ባንክ ያልተመለሱ የተበላሹ ብድሮች እንዳሉት ሲናገር በርካታ ባለሃብቶች ብድር ወስደው መክፈል አልቻሉም ማለት እንደሆነም ያስረዳሉ።
ኢንቨስትመንት ላይ ያሉ ሰዎች ራሳቸው ብድራቸውን መክፈል እንዲችሉ ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ ሰዎች ያስቀመጡት ገንዘብ ባንክ ቤት ውስጥ የለም ማለት መሆኑን በማስረዳት ለገንዘብ እጥረቱ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ያብራራሉ።
"መንግሥት ግን ይህንን ውሳኔ የወሰንኩት እጥረት ስለገጠመኝ ነው ብሎ ሊል አይችልም" በማለትም የገንዘብ እጥረቱ እየገጠመ ነው ወደፊት ደግሞ በፍጥነት ሊገጥም መቻሉ ገሃድ መሆኑን ያስረዳሉ። "ምክንያቱም ወደ በሽታው [ኮሮናቫይረስ] ገና እየገባንበት ነው ይላሉ።
ወረርሽኙ እየተስፋፋ ሲመጣ፣ የሰዎች እንቅስቃሴ ሲገደብ፣ አሁን ገበያ ላይ ያሉት ነጋዴዎች አቅማቸው ሲዳከም፣ ገንዘባቸውን በእጃቸው ይዘው መጠቀም ሲመርጡና ለአስፈላጊ ነገሮች ብቻ ሲያወጡ፣ የባንክ ቤት ሰልፍ ጠልተው እያወጡ ሲያስቀምጡ ወደፊትም ቢሆን እጥረት መፈጠሩ አይቀርም ይላሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዋሲሁን በላይ።
"ዜጎች በመጪው ጊዜ ላይ እርግጠኛ መሆን የማይችሉ ከሆነ ብራቸውን ስለሚይዙ የመቆጠብ አቅማቸው ደካማ ስለሚሆን የገንዘብ አቅርቦት እያነሰ ስለመጣ እርሱንም አስታኮ የወሰነው ይመስለኛል።"
በተጨማሪነት ግን ኢንቨስትመንት እንዲያድግ ቁጠባን ለማበረታታት አስቦ መንግሥት የወሰነው እንደሚመስላቸው ባሙያው ጠቅሰው "ገንዘብ ከባንክና ከፋይናንስ ሥርዓት ውጪ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ አይፈቀድም።"
ብዙ አገራቶች ይህንን ነገር እያስቀሩ መምጣታቸውን ገልጸው "ስለዚህ ብሔራዊ ባንክም የሆነ ቦታ ላይ ለጥሬ ገንዘብ ዝውውሮች ሥርዓት ማበጀት ነበረበት" ብለዋል።

"ተጻራሪ የምጣኔ ሃብት ፖሊስ"
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እርምጃ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ሲሉ እርምጃውን አጥብቀው ይተቻሉ።
"ይሄ ይዞት የሚመጣው ነገር በጣም አደገኛ ነው። ከዚህ በኋላ ባለሃብቱ የሚከፈለውን ክፍያ በጥሬ ገንዘብ ይቀበልና ወስዶ ቤቱ ያስቀምጣል። ይህ ደግሞ ገንዘብ ወደ ባንክ ገብቶ እንቅስቃሴ እንዳይፈጠር ያደርጋል። ይሄ እርምጃ ከሚያመጣው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል" ይላሉ።
ግብር ስወራን በተመለከተ ጉቱ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ የሚጠበቅባቸውን ግብር ላለመክፈል 'ኪሳራ ደርሶብኛል' እያሉ ሪፖርት በማድረግ ግብር የሚያሸሹ በርካታ ነጋዴዎች መኖራቸው አይካድም ይላሉ።
"ነገር ግን በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ሰዎችን አሳደን የሚጠበቅባቸውን ግብር እንዲከፍሉ ማድረግ እንችላለን ወይ? ይህ ዘላቂ መፍትሄ ያመጣል ወይ?" ሲሉ ይጠይቃሉ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው እንደሚሉት ከሆነ ይህ ዓይነት የመንግሥት ውሳኔ፤ "ከባንክ ውጪ ሊደረግ ወደ የሚችለው ልውውጥ ስለሚወስድ ምጣኔ ሃብቱን በአፍጢሙ ሊደፋ ይችላል" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
ጉቱ (ዶ/ር) ይህ የመንግሥት ውሳኔ አገሪቱ ኮሮናቫይረስ ከሚያስከትለው የምጣኔ ሃብት ቀውስ በኋላ ለማንሰራራት በምታደርገው ጥርት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችልም ያነሳሉ።
"ከኮሮናቫይረስ ስርጭት በፊት የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች የሚያበድሩት በቂ ገንዘብ አልነበራቸውም። ብሔራዊ ባንክ ራሱ ከተቀማጭ ገንዘቡ ማሻሻያ እያደረገ ለባንኮች ገንዘብ የሚለቅበት አጋጣሚዎች ነበሩ" ይላሉ ባለሙያው።
አክለውም ከወረርሽኙ በኋላ ደግሞ እንደሚስተዋለው የዓለም ምጣኔ ሃብት እጅጉን ተጎድቷል፤ በኢትዮጵያም የፋይናንስ ተቋማት ለመደገፍ መንግሥት በብሔራዊ ባንክ በኩል 15 ቢሊዮን ብር እንዲቀርብ ማድረጉን አስታውሰዋል።
"መንግሥት ይህን ያደረገው አበዳሪዎች ለተበዳሪዎች ጊዜ እንዲያራዝሙ፣ የወለድ መጠን እንዲቀንስ፣ ተጨማሪ ብድር የሚፈልጉ ብድር እንዲያገኙ፣ አምራቾች ምርታቸውን እንዲያስፋፉ ነው።
"ለዚህ ደግሞ ጥሩ የገንዘብ አቅርቦ ወደ ኢኮኖሚው መፍሰስ አለበት እያልን አያሰብን ባለንበት ሰዓት ላይ የገንዘብ ዝውውር ላይ ገደብ መጣል ከተባለው ነገር ጋር የሚቃረን የምጣኔ ሃብት እርምጃ ነው የሚሆነው" ይላሉ።
መልካም ጎኑ?
መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከተገደደብ ምክንያት አንዱ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት በማሰብ ነው።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጉቱም (ዶ/ር) አሁን ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ወጪ በሚደረግ የገንዘብ መጠን ላይ ገደብ መጣል የሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት ጠቀሜታ አለው በማለት ይስማማሉ።
ይህንንም ሲያስረዱ "ከወረርሽኙ በፊት የሰው እንቅስቃሴ እንደልብ ነበር። ሰዎች ገንዘብ በማዳበሪያ ጭነው ሃርጌሳ ይወስዳሉ፤ ወደ መተማ ይሄዳሉ። አሁን ግን በቫይረሱ ምክንያት ሰዎች እንደፈለጉት መንቀሳቀስ አይችሉም። ስለዚህ ባንክ ለመጠቀም ይገደዳሉ" ይላሉ።
ይህንንም በምሳሌ ሲያስረዱ "አንድ ሰው ወደ ባንክ ገቢ የተደረገውን ገንዘብ ላውጣ ቢል፤ ወጪ የተጠየቀው ቅርንጫፋ ብዙ ገንዘብ ስለተጠየቀ ሥራ መስራት አቆመ ማለት። ግለሰቡም ይህን ያክል ገንዘብ ከየት አመጣህ ተብሎ ይጠየቃል። በዚህ መልኩ መቆጣጠር ይችላል" በማለት እርምጃው ሊኖረው የሚችለውን ጠቀሜታ ያስረዳሉ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዋሲሁን በላይበበኩላቸው የመንግሥት ውሳኔ መጥፎ አለመሆኑን ያስረዳሉ። "የገንዘብ አቅርቦቱን በጣም በጣም መቆጣጠር አለበት። ምክንያቱም የዋጋ ንረት ከሚቀጣጠልባቸው ነገሮች አንዱ ከፍተኛ ብር በገበያው ሲሰራጭ ነው። ሐሰተኛውን በር ከትክክለኛው መለየትም በጣም አስቸጋሪ ነው" በማለት መንግሥት እነዚህን ለመቆጣጠር አስቦ እንደሆነ ያምናሉ።
"ውሳኔው ጥሬ ገንዘብ የመያዝ እንጂ ሰዎች ገንዘብ ማንቀሳቀስ የለባቸውም" የሚል አይደለም የሚሉት ባለሙያው፣ ከጥሬ ገንዘብ ውጪ ዲጂታላይዝ በሆነ ገንዘብ ግብይት ማከናወን የሚቻልበት ሥርዓት ካለ በሞባይል መገበያየት፣ በኤቲኤም፣ በቼክ፣ በፖስ ማሽን መገበያየት የሚችሉ ከሆነ ግብይቶች እንዲቆሙ አልተደረገም ይላሉ።
ስለዚህም የመሸመት መጠኑን የሚገደብ ምክንያት አለ ብለው እንደማያስቡ የሚናገሩት አቶ ዋሲሁን፤ ከፍተኛ ገንዘብ ገበያ ላይ ተረጭቶ ገንዘቦቹ ምርትና ምርታማነት ላይ የማያርፉ፣ ፍላጎትን የሚያሳድጉ ከሆነ የዋጋ ግሽበትን የማቀጣጠላቸው እድል በጣም ከፍተኛ መሆኑን ያሰምሩበታል።












