በኢትዮጵያ ከባንኮች በሚወጣ የገንዘብ መጠን ላይ ገደብ ተጣለ

ብር የሚቆጥር ሰው

ኢትዮጵያ ከባንኮችና ከማክሮ ፋይናንስ ተቋማት በሚወጣ የጥሬ ገንዘብ ላይ ገደብ መጣሏን አስታወቀች።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ዛሬ ይፋ ባደረገውና ተግባራዊ በሚሆነው መመሪያው መሰረት ተቋማትና ግለሰቦች ከባንኮች በቀንና በወር ውስጥ ከባንኮች በሚያወጡት የጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ ገደብ ተጥሏል።

በዚህም መሰረት አንድ ግለሰብ በቀን እስከ 200 ሺህ ብር እንዲሁም በወር እስከ 1 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ከባንኮች ማውጣት የሚችል ሲሆን፤ ተቋማት ደግሞ በቀን እስከ 300 ሺህ ብር እና በወር እስከ 2.5 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንደሚችሉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ይህንን እርምጃ በተመለከተ እንደተናገሩት "የገንዘብ ዝውውርን ሥርዓት በማስያዝ ወንጀልንና የግብር ስወራን ለመከላከል ይረዳል" ማለታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በጥሬ ገንዘብ ዝውውር ላይ የተጣለውን የመጠን ገደብ በተመለከተ የወጣው መመሪያ እንዳመለከተው ግን ከተቀመጠው መጠን በላይ ለማንቀሳቀስ ለሚፈልጉ በገንዘብ ተቋማቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች በኩል የሚያቀርቡት ምክንያት ተመርምሮ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም የመጠን ገደብ ከተጣለበት በላይ ጥሬ ገንዘብ ለሚያንቀሳቅሱ ግለሰቦችና ተቋማት ከአንድ ሒሳብ ወደ ሒሳብ፣ በቼክ፣ወይም በሲፒኦ ተጨማሪ ገንዘብ ማዘዋወር እንደሚችሉም ተመልክቷል።

ከዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 11/2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን የተነገረው መመሪያን ተግባራዊነትን በተመለከተ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ ክትትል እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን፤ ባንኮችም በየሳምንቱ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴያቸውን ለማዕከላዊው ባንክ ሪፖርት እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል።

ይህ መመሪያም በአገሪቱ ያሉትን ሁሉንም ባንኮችና አነስተኛና ጥቃቅን የገንዘብ ተቋማትንም የሚመለከት መሆኑ ተገልጿል።

ይህንን የብሔራዊ ባንኩን መመሪያ ተላልፈው የተገኙ የገንዘብ ተቋማት ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልባቸውም ተመልክቷል።