አፍሪካዊቷ ቢሊየነርና የብሩስሊ ፊርማ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሰሞኑ የሃገሯን ሃብት አራቁታለች የምትባለው የቀድሞው የአንጎላ ፕሬዚዳንት ልጅና ቢሊየነር ኢዛቤል ዶስ ሳንቶስና የቻይናው ዕውቅ የኩንግፉ ስፖርተኛ፣ ፊልም ሰሪና የማርሻል ጥበብ ፈላስፋ ብሩስሊ በአንድ ላይ ስማቸው እየተነሳ ነው።
እንዴት ነው ጄት ኩንዱን የፈጠረ፣ እንዲሁም የአልበገር ባይ ምሳሌ የሆነው ብሩስሊና አንጎላዊቷ ቢሊዮነር ዶስ ሳንቶስ ምን አገናኛቸው?
አንጎላዊቷ ቢሊዮነር ዶስ ሳንቶስ ከሰሞኑ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሃገር ውስጥም ሆነ በፖርቹጋል ያለው ንብረቷ የታገደው ይነሳልኝ ብላለች።
ለዚህም የሉዋንዳ ፍርድ ቤትና ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመመሳጠር ሃሰተኛ ማስረጃዎችን አቅርበውብኛል ብላለች።
ቢሊየነሯ እንደምትለው የሷ ያልሆነ ፓስፖርት አመሳስለው በመስራት የተፈበረኩ ማስረጃዎችን አቅርበውብኛል በሚል ፍርድ ቤቶቹን ወንጅላቸዋለች።
ለዚህም ማስረጃ እንዳላት የተናገረችው ኤዛቤል ዶስ ሳንቶስ ፓስፖርቱ ላይ የተቀመጠው ፊርማ የሷ ሳይሆን እንዲያውም የኩንግፉው ንጉስ ብሩስሊ ነው ብላለች።
ፓስፖርቱ ላይ የተቀመጠው ፊርማ የብሩስሊ መሆኑን ማረጋገጧን በፅሁፍ ለፍርድ ቤቱ ብታስገባም ፍርድ ቤቶቹ ያሉት ነገር የለም።
በአፍሪካ ውስጥ አሉ ከሚባሉ የናጠጡ ቱጃሮች አንዷ የሆነችው ዶስ ሳንቶስ የተጣራ አንጡራ ሃብቷም ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።
አባቷ ጆሴ ኤድዋርድ ዶስ ሳንቶስ አንጎላን ለ38 አመታት ያህል ቀጥ ለጥ አድር በመግዛት፣ በጨቋኝ ክንዳቸው እንዲሁም የሃገሪቷን ሃብት በመመዝበር ይተቻሉ። ልጃቸውምን በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2016 የሃገሪቱ የነዳጅ ማጣሪያ ድርጅት ሃላፊ አድርገው ሾመዋት ነበር።
በአመቱ አባቷ ከስልጣን መውረዳቸውንም ተከትሎ ተተኪያቸው ጆዋ ሎውሬንሶ ዝም አሏሏትም። ከነበራት ድርጀቱ ሃላፊነት ከማንሳት በተጨማሪ የሃገሪቱን አንድ ቢሊዮን ዶላር ሃብት ከተባባሪዎቿ ጋር በመመዝበር ወንጀል ከሰሷት።
በፍርድ ቤት ውሳኔም በአንጎላ እንዲሁም በፖርቹጋል ያለው ሃብት እንዲታገድ ተወሰነ። በአፍሪካ ሴት ቢሊየነሮች ደረጃ ቀዳሚ የሆነችው ዶስ ሳንቶስ ይህን ሁሉ ውንጀላ በማጣጣል አልፈፀምኩም ብላ ክዳለች።
ከሰሞኑም ያቀረበችው ማስረጃ "ንፁህነቴን" የሚያረጋግጥ ነው በማለት የተፈበረከ የተባለውንም ፓስፖርት በህዝብ ግንኙነቷ በኩል ይፋ እንዲሆን አድርጋለች። በትዊተር ገጿም አጋርታለች።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ዶስ ሳንቶስ እንዴት ልትከሰስ ቻለች?
ከነዳጅ ማጣሪያ ሃላፊነቷ መነሳቷን ተከትሎ እሷን ተክቶ የመጣው ካርሎስ ሳቱሪኖ የተባለው ግለሰብ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር እንዳለ ባለስልጣናቱን ማሳወቁን ተከትሎ ነው ምርመራ የተከፈተባት።
በጎርጎሳውያኑ 2019ም የአንጎላ ፍርድ ቤት በአንጎላ የሚገኘውን ባንኳ ውስጥ ያለው ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ እግድ ከመጣል በተጨማሪ የተለያዩ ኩባንያዎቿንም እንዳታንቀሳቅስ አድርጓታል።
በሷ ላይ ብቻ ሳይሆን በባለቤቷና ሲንዲቃ ዶኮሎና በስራ አስኪያጇም ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ ተላለፈ።
በወቅቱም ዶስ ሳንቶስ ሁኔታውን ከማውገዝ አልፋ "ፖለቲካዊ ብቀላ" ነውም ብላለች። ምንም እንኳን ቢሊየነሯ ፖለቲካዊ ኢላማ ተደርጌያለሁ ብትልም ከ700 ሺህ በላይ የሆኑ ሾልከው የወጡ መረጃዎች እሷም ሆነ የኮንጎ ዜግነት ያለው ባለቤቷ የሃገሪቷን ንብረት አግባብ በሌለው ሁኔታ ጥርጣሬ የተሞላባቸው ስምምነቶች ወጥተዋል።
ከነዳጅ ጋር በተያያዘ
አንድ የለንደን የነዳጅ አውጭ ኩባንያ በአገሯ እንዲሰራ በተጭበረበረ መንገድ ሲገባ ዶስ ሳንቶስ የትወናው አካል ነበረች። በኋላ አባቷ ከስልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ ኩባንያው ሲታገድ 58 ሚሊዮን ዶላር የከፈለችበት ደረሰኝ ተገኝቷል። ይህ ለምን እንደተፈጸመና ድርሻዋስ ምን ነበር የሚለው ያልተመለሰ ጥያቄ ነው።
የኢዛቤል ዶ ሳንቶስ ጉዳይ በዚህ አያበቃም። አንድ ዱባይ ከሚገኝ ኩባንያ ጋርም በተመሳሳይ ተመሳጥራ ሁለት የክፍያ ሰነዶች እንደተላኩላት ማግኘት ተችሏል። ይህ ሕጋዊነት ይጎድለዋል የተባለው የክፍያ ሰነድም ለምን ክፍያው እንደተፈፀመ የሚያትተው ነገር የለም።
በዚህ የሂሳብ መጠየቂያም በአንደኛው 472,196 ዩሮ ሁለተኛው ደግሞ 928,517 የአሜሪካን ዶላር ተጠይቆበታል።
ይህም ሰነድ ህጋዊነቱ ያልተረጋገጠ ቢሆንም ቢሊየነሯ ግን ሕጋዊ መንገድን ተከትዬ የፈጸምኩት ነው ብላለች።
ሌላኛው ከነዳጅና ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ለኢዛቤል የቀረበው ክስ በጎርጎሮሳውያኑ 2006 የአንጎላ የኃይል አቅርቦት ለመሥራት ስትስማማ በወቅቱ 15% ብቻ ከፍላ ቀሪው ዝቅተኛ ወለድ ተደርጎላት በተራዘመ ጊዜ እንድትከፍል ነበር።
ላለፉት 11 ዓመታት ግን መክፈል የነበረባትን 70 ሚሊዮን ዶላር አልከፈለችም። አሁን ኢዛቤል በባለድርሻነት የምትመራው ኩባንያ አጠቃላይ ዋጋው 750 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል።
ተቋሟ እዳውን በ2017 ለመክፈል ተስማምቶ ነበር፤ ነገር ግን ቢያንስ ወለድ ተብሎ የታሰበውን 9% ማካተት ስላልቻለ ክፍያው እንዳይፈጸም ተደርጓል።
ከአልማዝ ጋር በተያያዘ
በሙስና ሥራው ኢዛቤል ብቻዋን እንዳልተሳተፈች መረጃ የቀረበባት ሲሆን የሃገሪቷ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባሏም በአሻጥሩ ተሳትፏል ይላል። በጎርጎሳውያኑ 2012 ባለቤቷ መንግሥት ከሚቆጣጠረው ሶዳየም ከሚባለው የአልማዝ ኩባንያ ጋር የአንድ ወገን ፊርማ ፈርሟል።
በፊርማው መሰረት ሁለቱ ፈራሚዎች የፕሮጀክቱን ወጪ ግማሽ ግማሽ መቻል ነበረባቸው።
ነገር ግን ሙሉ ወጭው የተሸፈነው በመንግሥት ነው። ሰሞኑን የሚዲያዎች እጅ ላይ የገባው ዶክመንት እንደሚያሳየው ከ18 ወራት በኋላ ባለቤቷ 79 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ሲገባው የከፈለው የገንዘብ መጠን ግን 4 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።
ይባስ ብሎ ደግሞ ጉዳዩን ስለደለልኩ ሽልማት ይገባኛል ብሎ ከዚሁ ፕሮጀክት ውስጥ የኢዛቤል ባለቤት ዶኮሎ ተጨማሪ 5 ሚሊዮን ዶላር ራሱን ሸልሟልም ተብሏል።
ከዚህ ስምምነት የአንጎላ ሕዝብ የሚያገኘው ጥቅም ምንም ሲሆን በአንጻሩ ለኩባንያው መሥሪያ ተብሎ ከግል ባንክ ለተበደሩት 200 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ይከፍላሉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የአንጎላ መንግሥት አልማዝ በዝቅተኛ ዋጋ መሽጡን ቢያምንም ምንጮች እንደሚሉት ግን እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ከስሯል።
ከመሬት ጋር በተያያዘ
ዶሰስ ሳንቶስ መሬት ላይም ሁነኛ ተሳታፊ ናት። መረጃው እንደሚያሳየው ቢሊየነሯ ዶ ሳንቶስ በ2017 በዝቅተኛ ዋጋ መሬት እንድትገዛ መንግሥት አመቻችቶላታል። ይህንን በመዲናዋ ሉዋንዳ የባህር ዳርቻ የሚገኘውን ጋሻ መሬት የገዛችውም በአባቷ ረጅም እጅ በመታገዝ ነበር።
ኮንትራቱ የሚለው መሬቱ 96 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል ነው።ዶስ ሳንቶስ ያወጣችው ግን 5 በመቶ ብቻ ነው። ቦታው ላይ የነበሩ አንጎላዊያን ግን ይዞታቸው ለዶስ ሳንቶስ በመሰጠቱ ከነበሩበት ዋና ከተማዋ ሉዋንዳ 50 ኪሎ ሜተር ርቀው ሄደዋል። ከመሬት ጋር በተያያዘ በሌላ የኢዛቤል ዶ ሳንቶስ ፕሮጀክት ከ500 በላይ ቤተሰብ በእርሷ ምክንያት ተፈናቅሏል።
ከቴሌኮም ዘርፍ ጋር በተያያዘ
ቢሊየነሯ ከቴሌኮም ዘርፍም አንጎላ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ አግበስብሳለች፤ በአገሪቱ ከፍተኛው የሞባይል ስልክ አቅራቢ ኩባንያ ውስጥ 25 በመቶ ድርሻ አላት።
ዩኒቴል የተባለው ይህ ኩባንያ በቀቅርቡ ለኢዛቤል 1 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ የሰጣት ሲሆን ቀሪ ኃብቷም ሌላ 1 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሏል። ይሁንና ሴትዮዋ ከዘርፉ ገንዘብ የምታገኝበት ይህ ብቸኛ መንገድ አይደለምም ተብሏል።
በእንግሊዝ ተቀማጭነቷን ያደረገችው ቢሊየነሯ በነዳጅ፣ ቴሌኮምና ባንክ ዘርፎች በመሰማራት በሃገሯ አንጎላና በፖርቹጋል የተትረፈረፈ ሃብትን ማትረፍ ችላለች።












