የቀድሞው የአንጎላ መሪ ልጅ የ15 ሚሊዮን ዶላር ቤቷን አፍርሳ ልትገነባ ነው

ለበርካታ አስርት ዓመታት አንጎላን የመሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ልጅ ለንደን ውስጥ ያላትን ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ቅንጡ መኖሪያ ቤቷን አፍርሳ ልትገነባ መሆኑ ተነገረ።
ኢዛቤላ ዶስ ሳንቶስ ከዓለማችን ውድ ከተሞች መካከል በምትጠቀሰው ለንደን ውስጥ ያላትን ግዙፍ ቅንጡ መኖሪያ ቤቷን አፍርሳ እንደገና ልታስገነባው መሆኑን የእንግሊዙ ታይምስ ጋዜጣ ዘገበ።
የናጠጡ ሃብታም ከሚባሉት አፍሪካዊያን ሴት መካከል እንደሆነች የሚነገርላት ቢለየነሯ የቀድሞው የአንጎላ ፕሬዝዳንት ልጅ ኢዛቤላ የቤቱ ባለቤት መሆኗ የታወቀው ፈርሶ በሚገነባው ውድ ቤት ዕቅድ ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ሳቢያ እንደሆነ ተዘግቧል።
የተትረፈረፋቸው ባለጸጎች ይኖሩበታል ተብሎ በሚነገርለት ኬንሲንግተን በተባለው የለንደን ክፍል ውስጥ የሚገኘው ፈርሶ የሚገነባው የኢዛቤላ ዶስ ሳንቶስ መኖሪያ ቤት ዕቅድ በጎረቤቶቿ ዘንድ ቁጣን እንደቀሰቀሰ ተገልጿል።
እንደ ጋዜጣው ዘገባ ግን ኢዛቤላ መልሳ ልትገነባው ያሰበችውና ድንቅ የሥነ ህንጻ ምኞቷን እውን ለማድረግ ያሰበችውን የቤቷን ግንባታ ዕቅድ በዙሪያዋ ባሉ ነዋሪዎች ተቃውሞ ቢቀርብበትም ግንባታውን ለማከናወን ከሚመለከተው አካል ፈቃድ አግኝታለች።
በእንግሊዝ ጋዜጦች ላይ የወጡ ዘገባዎች የግዙፉን ቤት ፎቶ ግራፎች ይዘው የወጡ ሲሆን ኤዛቤላ ዶስ ሳንቶስ ቤቱን ከ12 ዓመት በፊት መግዛቷን ጠቅሰዋል።












