የውሃ እጥረት ዋነኛው የዓለማችን ስጋት

ውሀ የተሸከሙ ህንዳውያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም ሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የሥጋ ተመጋቢዎች አሃዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ መሄድ እንዲሁም እያደገ የመጣው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የዓለማችን የውሃ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው።

ተለይተው በታወቁ 400 የዓለማችን ክልሎች ውስጥ ሰዎች ከፍተኛ በሚባል የውሃ እጥረት ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፤ ሁኔታው ይሻሻላል ተብሎ እንደማይጠበቅ መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው የዓለም ተፈጥሯዊ ሃብቶች ኢንስቲቲዩት የጥናት ውጤት ያሳያል።

በጥናቱ መሰረት የውሃ እጥረት ከግጭቶችና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ጋር ሲደመር በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያ መንደራቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ይሆናል።

ከሜክሲኮ እስከ ቺሊ፣ ከአፍሪካ በከፍተኛ የቱሪስት ፍሰታቸው እስከሚታወቁት ደቡባዊ አውሮፓና ሜዲትራኒያን ክልሎች ድረስ በተደረገው ጥናት ምን ያክል ውሃ ከከርሰ ምድር እንደሚወሰድና ምን ያክሉ ደግሞ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተመልክቷል።

ግኝቱም የዓለማችን የውሃ አቅርቦት አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያሳያል።

ዓለም አቀፋዊ ስጋት

አንድ ሦስተኛ የሚሆነው 2.6 ቢሊዮን የዓለማችን ህዝብ ከፍተኛ የውሃ እጥረት የሚያጋጥመው ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1.7 ቢሊዮን የሚሆኑትና በ17 ሃገራት ውስጥ የሚገኙት ደግሞ እጅግ የከፋ የውሃ እጥረት ይጋረጥባቸዋል ተብሎ ተሰግቷል።

በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ሞቃታማ ሃገራት ለውሃ እጥረት የተጋለጡ የተባሉ ሲሆን ህንድ በምትከተለው የተዛባ የውሃ አጠቃቀም ምክንያት የከፋ የውሃ እጥረት እያጋጠማት እንደሆነ ተገልጿል።

የውሃ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎችን የሚያሳይ ካርታ

ፓኪስታን፣ ኤርትራ፣ ቱርክሜንስታን እና ቦትስዋና ደግሞ እጅግ የከፋ የውሃ እጥረት ውስጥ እንደሆኑ ጥናቱ ጠቁሟል።

ይህ መረጃ የመጣው የዓለማቀፉ ተፈጥሯዊ ሃብቶች ኢንስቲቲዩት ሃገራት ካላቸው የውሃ ሀብት አንጻር ምን ያክሉን እንደሚጠቀሙ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

ሃገራት የሚጠቀሙት የውሃ መጠን ከ80 በመቶ ከፍ ካለ እጅግ የከፋ ውሃ ችግር እንደሚያጋጥማቸው የሚያሳይ ሲሆን ብዙ ሃገራት የሚገኙበትና አሳሳቢ የተባለው ከ40 እስከ 80 በመቶ ያለው ነው።

የጥናቱ ዋነኛ ተሳታፊ የሆኑት ሩትገር ሆፍስት ለቢቢሲ እንደተናገሩት በህንድ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ የሚባል ነው። በመረጃው መሰረትም ህንድ በውሃ እትረት ከዓለም 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ አሳሳቢ የሚባል ችግር ባይኖርም ሜክሲኮ የውሃ አጠቃቀሟን ካላስተካከለች ከህንድ የባሰ የውሃ እጥረት እንደሚያጋጥማት ጥናቱ ጠቁሟል።

ከዚህ በተጨማሪም ምንም እንኳን ቻይና እና ሩሲያ እንደ ሃገር ከውሃ እጥረት ነጻ ናቸው ቢባሉም ዋና ከተሞቻቸው ቤዢንግ እና ሞስኮ እጅግ ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንዳለባቸው ተገልጿል።

ከፍተኛ ውሃን የሚጠቀሙ ዘርፎችን የሚያሳይ ቻርት

ጣልያን እና ስፔንን ጨምሮ ደቡባዊ የአውሮፓ ሃገራት በሚያስተናግዱት ከፍተኛ የጎብኚ ቁጥር ምክንያት የውሃ ሃብታቸው ላይ ጫና እያሳደሩ ነው። በተለይ ደግሞ ደረቅ የሚባለው የዓመቱ ወቅት ሲመጣ ችግሩ በእጅጉ እንደሚባባስም ተጠቁሟል።

ምዕራባዊ የደቡብ አፍሪካ ክፍሎች፣ 10 የቦትስዋና ክልሎች፣ አንዳንድ የናሚቢያ አካባቢዎችና አንጎላ ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንደሚያጋጥማቸውም መረጃው ያሳያል።

ከአውሮፓውያኑ 1961 እስከ 2014 ድረስ በዓለማችን ያለው የከርሰ ምድር ውሃ እና የገጸ ምድር ውሃ የመጠቀም ዝንባሌ በ2.5 እጥፍ ጨምሯል። ተክሎችን ለማብቀል የምንጠቀመው ውሃ መጠንም ባለፉት 50 ዓመታት ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።

በመስኖ የሚለሙ ተክሎችና የተለያዩ ምርቶች ደግሞ በየዓመቱ 67 በመቶ የሚሆነውን የውሃ ፍጆታ ድርሻ ይወስዳሉ። በ2014 የተለያዩ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች የተጠቀሙት የውሃ መጠን በ1961 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በሦስት እጥፍ ጨምሯል።

በሌላ በኩል የዓለማችን ህዝብ በቤት ውስጥ የሚጠቀመው ውሃ መጠን ባለፉት አርባ ዓመታት በስድስት እጥፍ ጨምሯል።

የውሃ እጥረትን የሚያሳይ ግራፍ

ነገር ግን ተክሎችን ለማብቀል ጥቅም ላይ የሚውለው ውሃ ሁሌም ቢሆን ለሰው ልጆች ብቻ በቀጥታ እንደማይውል ሩትገር ሆፍስት ያስረዳሉ። እንደ ማሳያም ከብቶችን ለመመገብ የሚውለውን 12 በመቶ ውሃ ፍጆታ ያነሳሉ።

''ስለዚህ የዓለም ህዝብ የሥጋ ፍጆታውን መቀነስ ወይም መቆጣጠር ከቻለ በተዘዋዋሪ የውሃ ፍጆታውን ቀነሰ ማለት ነው'' ይላሉ።

በረሃማነትን የሚዋጋው ተባበሩት መንግሥታት ድርጀት አካል እንደሚለው አሁን ያሉትን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት በበረሃማና በከፊል በረሃማ አካባቢዎች የሚኖሩ እስከ 200 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በፈረንጆቹ 2030 ይፈናቀላሉ።

ነገር ግን ይላሉ ሩትገር ሆፍስት እንደ ሲንጋፖርና እስራኤል ያሉ ሃገራት የውሃ እጥረትን ለመከላከል ብዙ ሥራዎችን እየሰሩ ነው። መላው ዓለምም የእነሱን ፈለግ መከተል አለበት ሲሉ አሳስበዋል።