በአንድ ቀን 1 ቢሊዮን ዶላር ያተረፈው ጆርጅ ሶሮስ ማን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ የደበተው ሰኞ ከሰዓት፤ በ2019 ኅዳር ወር ላይ መሆኑ ነው፣ ምንነቱ ያልታወቀ የፖስታ ጥቅል በኒውዮርክ የባለጸጎች መንደር በሚገኝ አንድ ግዙፍ ቤት ተቀመጠ፤ ደጅ የፖስታ ሰንዱቅ ውስጥ።
ጥቅሉ አጠራጣሪ ነገሮች ነበሩት። አንደኛ የተመላሽ ስም በትክክል አልተጻበትም። ሁለተኛ በተላከበት ቀን ነው የደረሰው። ፖሊስ ተጠራጠረ፤ ኤፍቢአይ ተጠራ። የጆርጅ ሶሮስ ቪላ ተወረረ።
በዚያ ጥቅል ውስጥ የሶሮስ ፎቶ ነበር፤ ከፊት ለፊት የይገደል ምልክት ተጽፎበታል። 6 ኢንች የሚረዝም የፕላስቲክ ጎማ፣ ቁልቁል የሚቆጥር ሰዓት፣ ባትሪና የኤሌክትሪክ ሽቦዎች ነበሩበት፤ በጥቅሉ ፖስታ።
ተመሳሳይ ጥቅል ወደ ኦባማና ሂላሪ ቤት ተልኳል። ደግነቱ አንዱም አልፈነዳም፤ ፖሊስ አክሽፎታል።
እነዚህን ጥቅሎች የላከው ማን ነበር?
ቀኝ ዘመም የአሜሪካ ሚዲያ ቶሎ ጣቱን የቀሰረው ወደ ሶሮስ ነበር። ራሱ ሶሮስ የሸረበው ሸር ነው በሚል። ሶሮስ እንዴት አድርጎ ወደ ራሱ ቦምብ ይልካል?
ጥሩ ጥያቄ ነው። ነገር ግን የትራምፕ አክራሪ ደጋፊዎች በአመዛኙ ለርትዕ ፊት አይሰጡም ይባላል፤ ለፖለቲካ ተዋስኦ ክፍት አይደሉም፤ አመክንዮ ይቀፋቸዋል። የትራምፕ ደጋፊዎች የሚቀናቸው ሴራ ነው። የአሻጥር ፖለቲካ የነጭ አክራሪዎች ኦፒየም ነው።
ስለዚህም አደባባይ ወጡ። ጆርጅ ሶሮስን ሊያወግዙ።
"ትራምፓችን ሆይ! ሶሮስን እሰር! ሶሮስን ዘብጥያ አውርድልን" የሚል ድምጽ በዋይት ሃውስ ደጅ ላይ አስተጋባ።
ደግነቱ ፖሊስ ቦምቦቹን በጥቅል የላከውን ሰው ደረሰበት። የ56 ዓመቱ የፍሎሪዳ ነዋሪ ሲዛር ሳዮክ ነበር።
ሰውየው እንዲያውም ብዙዎች እንደገመቱት ሪፐብሊካን አልነበረም። ቤት ለቤት ፒዛ አዳይ እንጂ።
ሆኖም አእምሮው በሴራ ፖለቲካ ናውዞ ነበር። እንደ ብዙዎቹ ቀኝ አክራሪዎች። ከሁሉም ፖለቲካ ጀርባ ጆርጅ ሶሮስ የሚባል ሰው አለ ብሎ ያምን ነበር፤ ሶሮስ የነጭ የበላይነትን ሊያጠፋ የተነሳ ጠላት ነው ብሎ ያስብ ነበር፤ የትራምፕ ጠላት ነው ብሎ ያምን ነበር፤ ስለዚህ መገደል አለበት በሚል ነው ቦምቡን በፖስታ የላከው።
የዚህ ወንጀለኛ ፌስቡክ ሲበረበር ደግሞ ሌላ ጉድ ተገኘ።
"ዓለም ከእንቅልፉ ሲነቃ የሶሮስን አሳዛኝ ዜና ይሰማል!"
ይህ ግለሰብ ለጊዜው 20 ዓመት እስር ተከናንቧል። ጆርጅ ሶሮስ ግን አሁንም የሴራ ፖለቲካ ገፈት ቀማሽ እንደሆነ አለ። ከሁሉም የዓለም ፖለቲካ ለውጥ ጀርባ የሶሮስ እጅ አለ የሚል አስተሳሰብ ናኝቷል።
ለመሆኑ ሶሮስ እንደሚገመተው የዓለም የአሻጥር ፖለቲካ ሾፌር ነው?
የጆርጅ ሶሮስ አጭር የሕይወት ታሪክ
ጆርጅ ሶሮስ ከፖለቲከኞች አፍ የሚጠፋ ስም አይደለም። አምባገነኖች በተለይ ይፈሩታል።
የእነዚህ አምባገነኖች መቀመጫ እሲያም ይሁን አፍሪካ፣ ምሥራቅ አውሮፓም ይሁን ደቡብ አሜሪካ ወይም መካከለኛው ምሥራቅ... ብቻ መንግሥታቱ ከሚነሳባቸው ተቃውሞ ጀርባ የቢሊየነሩ ጆርጅ ሶሮስ እጅ እንዳለበት ይገምታሉ። እውነት አላቸው?
ለመሆኑ ይሄ ለግራ ዘመም ፖለቲከኞች ብር ይረጫል የሚባለውና በልግስናው ስመ ገናናው ጆርጅ ሶሮስ ማን ነው?
ትውልደ ሀንጋሪያዊ-አሜሪካዊው ሶሮስ የተወለደው በቡዳፔስት በ1930 ዎቹ መጀመርያ ከአይሁድ ቤተሰብ ነበር።
እንዲያውም "ጆርጂዮ ሽዋትዝ" ነበር የቀድሞ ስሙ።
በጊዜው በአውሮፓ በአይሁዳዊያን ላይ በነበረው ሥር የሰደደ ጥላቻ ምክንያት አባቱ ከግድያ ለማምለጥ፣ ቤተሰባቸውንም ለመታደተግ እንዲረዳቸው ሲሉ ነው የቤተሰባቸውን ስም ከሽዋትዝ ወደ "ሶሮስ" የቀየሩት።
ስሙን መቀየር ብቻም ሳይሆን በተለይ ለጆርጅ አዲስ ማንነትና መታወቂያ ተዘጋጅቶለት ልክ አይሁድ ያልሆነ ሌላ አንድ ተራ የቤተሰብ አባል ተደርጎ እንዲኖር ተደረገ። በዚህም ያንን አስቸጋሪ ዘመን መሻገር ቻለ።
ሶሮስ በ14 ዓመቱ የአንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ልጅ እንደሆነ ተደርጎ መታወቂያ ወጥቶለት ለጥቂት ሳይገደል ቀርቷል።
ሶሮስ ከግድያዎች ያምልጥ እንጂ በዚህ ወቅት የአይሁዶች ንብረት ሲዘረፍ፣ ክብራቸው ሲገፈፍ ዓይኑ በብረቱ ተመልክቷል።
በዚያ ዘመን፣ በተለይም በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ግማሽ ሚሊዮን የሀንጋሪ አይሁዶች እንዲገደሉ የሆነው 8 ሳምንታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነበር። እንዲያውም በመላው ዓለም ካሉ አገራት እንደ ሀንጋሪ አይሁዶች በአጭር ጊዜ በስፋት የተረሸኑበት አገር የለም ይባላል፤ ወላ በጀርመንም ቢሆን።
ሶሮስ ከናዚዎች ግድያ ተርፎ እፎይ ብሎ መኖር ሲጀምር ሀንጋሪ ወደ ኮምኒስት አገርነት ተለወጠች፤ ሌላ ፈተና። በዚህ ጊዜ ነበር ገና በ17 ዓመቱ ከቡዳፔስት ወደ ለንደን የሸሸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእንግሊዝን ባንክ ያንበረከከው ሶሮስ
ጎረምሳው ሶሮስ እንግሊዝ እንደገባ የሻይ ቤት አስተናጋጅ ሆነ። ከዚያም የባቡር አውራጅና ጫኝ ሆነ። ቀጥሎ ዩኒቨርስቲ ገባና ከዝነኛው የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ በምጣኔ ሀብት ዘርፍ ዲግሪ ያዘ።
እዚያ ዩኒቨርስቲ ሳለ ነበር አስተሳሰቡን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የለወጠለትን ሰው ያገኘው። ይህ ሰው ፈላስፋው ሰር ካርል ሬይመንድ ፖፐር ነበር።
ፈላስፋው ፖፐር ልክ እንደ ሶሮስ ሁሉ አይሁድ ስደተኛ ነው። ኦስትሪያዊ አይሁድ። ጆርጅ ሶሮስ አስተሳሰቡ የተጠረበው በዚህ መምህሩ እንደሆነ ይታመናል።
የዚህ መምህሩ በፖለቲካ ፍልስፍና ዓለም የናጠ ሥራው "The open society and its enemies" ይሰኛል። ከዚህ ከመምህሩ የጥናት ሥራ በተወሰደ ስም ነው ኋላ ጆርጅ ሶሮስ ዓለም ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ ድርጅቱን የመሠረተው፤ ስሙም "ኦፕንሶሳይቲ ፋውንዴሽን" ይባላል።
ብቻ ከዚህ በኋላ ጆርጅ ሶሮስ በ1970 የሶሮስ ፈንድን አቋቋመ።
እሱን ዓለም የሚያውቀው ግን በሁለት ነገር ነው፤ አንዱ እሱ አምጦ በወለደውና ቀደም ሲል በጠቀስነው "ኦፕን ሶሳይቲ" በሚባለው ድርጅቱ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእንግሊዝን ባንክ በእንብርክክ በማስኬዱ ነው። ከሁለተኛው እንጀምር...
አንድ ቢሊዮን በአንድ ቀን
በ1992 እንግሊዞች "ጥቁሩ ረቡዕ" (ብላክ ወይንስዴይ) ብለው የሚያውቁት ታሪክ አለ። ብሪታኒያ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ የገባችበት አስገራሚ ቀን ነው። ይህ ቀን ለብሪታኒያ ጥቁር ነበር ካልን ለጆርጅ ሶሮስ ግን ነጭ ነበር፤ የእርሱ የብልጽግና በር የተከፈተው በዚች ቀን ነበር ማለት ይቻላል።
ነገሩን በአጭሩ ለማስረዳት፡ ብዙዎቹ የአውሮፓ አገራት ዩሮን ወይም እሱን የሚመስል የጋራ ገንዘብ ለመፍጠር እያለሙ ነበር።ይህን መንገድ የሚጠርግ The European Exchange Rate Mechanism (ERM) የሚባል ህብረት ነበራቸው።
ይህንን ለማሳካት ደግሞ አባል አገራት የገንዘባቸው ጥንካሬ ከተወሰነ መጠን ዝቅ እንዳይል ይጠበቅባቸው ነበር።
የብሪታኒያ መንግሥት የሚገበያይበት ፖውንድ ስተርሊንግ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል የወለድ ምጣኔን ከፍ በማድረግ ጭምር ሞከረ። ሆኖም አልተሳካም።
በዚህ ታሪካዊ ቀን እንግሊዝ ገንዘቧን ፓውንድን ከመውደቅ ማዳን አቃታት፤ ስላቃታትም ከአውሮፓ አገራት የውጭ ምንዛሬ መወሰኛ ኅብረት (ERM) ለመውጣት ተገደደች።
ይህ "ጥቁሩ ረቡዕ" ብሪታኒያ ብሔራዊ ኪሳራን በአገር ደረጃ ያወጀችበት ዕለት ነበር።
ጆርጅ ሶሮስ ከዚህ ቀን ቀደም ብሎ የፓውንድ መውደቅ አይቀሬ እንደሆነ በመተንበይ ፓውንድ አብዝቶ ከባንኮች ይበደር ነበር። በርካታ ፓውንድ እየተበደረ መልሶ ከባንክ ውጭ በርካሽ ይሸጠዋል።
በተከታታይ ፓውንድ ዝቅ ባለ ዋጋ በመሸጥ ሌላ የገንዘብ ኖት በማከማቸቱ (በተለይም የጀርመን ማርክን) ብቻ በትንሹ በአንድ ቀን 1 ቢሊየን ዶላር ማትረፍ ችሏል። በዚህም የተነሳ ጆርጅ ሶሮስ "የእንግሊዝን ባንክ የያንበረከከው ሰው" በመባል ይታወቃል።
ጆርጅ ሶሮስ በዚያ ዓመት እንግሊዝን 3.3 ቢሊዮን ፓውንድ አክስሯታል፤ በሌላ አነጋገር እያንዳንዱ እንግሊዛዊ በተናጥል 15 ፓውንድ ለሶሮስ ከፍሏል ማለት ነው።
በእንዲህ ዓይነት አስቀድሞ የገንዘብ ጥንካሬን በመተንበይ በዓመታት ውስጥ በበርካታ አገራት ውስጥ ቢሊዮን ዶላር ማጋበስ እንደቻለ ይነገርለታል፤ ሶሮስ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኦፕን ሶሳይቲና ሶሮስ
እንደ ፈረንጆቹ በ1979 የተመሠረተው ኦፕን ሶሳይቲ በአሁኑ ጊዜ በ120 አገራት እየሠራ ነው። በኢትዮጵያም ቢሮ ለመክፈት በሂደት ላይ እንደነበር አንድ ሰሞን መዘገቡ ይታወሳል።
የአገር ቤቱ ሪፖርተር ጋዜጣ የእንግሊዝኛው ቅጂ በፈረንጆች ኅዳር 30 እትሙ እንደዘገበው ደግሞ ኦፕን ሶሳይቲ እገዛ ሊያደርግላቸው ካሰባቸው ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች መሀል አዲስ ስታንዳርድ የድረገጽ ጋዜጣና አዲስ ፎርቹን የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ይገኙበታል። ሁለቱ ሚዲያዎች ከ160 እስከ 200ሺህ ዶላር እንደሚለገሳቸውም ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።
ሪፖርተር በዚሁ ዘገባው የድርጅቱን ኃላፊ ሩት ኦሜንዲን ጠቅሶ እንዳለው ከሆነ ኦፕንሶሳይቲ በቅርብ ጊዜ ቢሮውን አዲስ አበባ ይከፍታል። እስከዛሬ እውን አልሆነም።
ሊበራል ዲሞክራሲን በማስፋፋት የተጠመደው ኦፕን ሶሳይቲ ፋውንዴሽን የብዙ አገሮች ራስ ምታት መሆኑ አልቀረም።
በተለይ አገራት ወደ ዲሞክራሲ እንዲሸጋገሩ "አመጾችን ለማቀጣጠል የሚውል ገንዘብ ይረጫል" የሚባለው ኦፕን ሶሳይቲ በሰብአዊ መብትና በትምህርት ላይ ያሳደረው የላቀ አስተዋጽኦ የሚካድ አይደለም።
ጆርጅ ሶሮስና የሴራ ፖለቲካ
ሚስተር ጆርጅ ሶሮስ ለሴራ ፖለቲካ ለመጀርመያ ጊዜ የተጋለጠው በ1990ዎቹ መጀመርያ ቢሆንም በተለይ በ2003 የኢራቅ ጦርነትን መቃወሙ በሪፐብሊካኖች ዘንድ ጥርስ እንዲነከስበት ሆኗል።
"ያለኝን ሀብት በሙሉ ጆርጅ ቡሽን ለማስወገድ ብጠቀምበት አይቆጨኝም" ማለቱ ብዙ ሲያነጋግር ነበር፤ በዚያ ዘመን።
ሶሮስ በ2018ቱ የአሜሪካ ምርጫም በተመሳሳይ ገንዘቡን ረጭቷል ተብሎ ይነገራል። ከባራክ ኦባማ መመረጥ ጀርባ ትልቁ ገንዘብ የሶሮስ ነው ተብሎም ይታመናል። እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት ፍቺ እንዳትፈጽም ለሚተጋ ቡድን ወደ 800 ሚሊዮን ዶላር ለግሷል።
የጆርጅ ሶሮስ ስምን ገናና ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ የቅርቡ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የነበረው ፍጥጫ ነው።
ዶናልድ ትራምፕን የሚያወግዙ ማናቸውም ሰልፎችን በከፍተኛ ገንዘብ ይደግፋል የሚባለው ሶሮስ፤ ከሆንዱራስ ተነስተው በሜክሲኮ አድርገው ወደ አሜሪካ በእግር የዘመቱ ሥራ አጦችን ያዘመተብን እሱ ነው የሚል ክስ ይቀርብበታል።
ውግንናው ለትራምፕ እንደሆነ የሚነገርለት ፎክስ ኒውስ በተከታታይ በሰራቸው ዘገባዎች ጆርጅ ሶሮስ ሁሉም የአገራት ድንበሮች እንዲከፈቱና በሕዝቦች መካከል ያልተገደበ ዝውውር እንዲኖር ይሻል ሲል ከሶታል።
ዶናልድ ትራምፕም በትዊተር ሰሌዳቸው ገንዘብ ለስደተኞች ሲታደል የሚያሳይ ቪዲዮ በመለጠፍ የገንዘቡ ምንጭ ሶሮስ እንደሆነ ለማመላከት ሞክረዋል። "ዱርዬዎች የአሜሪካንን ድንበር እንዲሰብሩ እየተከፈላቸው ነው" በሚል።
በኋላ ጋዜጠኞች እንዳጣሩት ከሆነ ግን ትራምፕ ያጋሩት ቪዲዮ በጭራሽ በሆንዱራስ እንዳልተቀረጸና የቪዲዮው ምንጭም ጓቲማላ እንደሆነች ማረጋገጥ ችለዋል። ትራምፕ ግን ይህ ግድ አልሰጣቸውም።
ከዚህ ትራምፕ ካራገቡት የሴራ ፖለቲካ በኋላም በአይሁዳዊያን ላይ የደረሰውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ የሶሮስ ስም በድጋሚ አንሰራራ። በዚህ ጥቃት አንድ ነጭ የአይሁዶች ምኩራብ ውስጥ ገብቶ 11ዱን ከፈጀ በኋላ ግለሰቡ ጆርጅ ሶሮስ የላከው ተደርጎ ሲዘገብ ነበር።
ኋላ ላይ ሲጣራ ግን እንዲያውም ወንጀለኛው የጆርጅ ሶሮስ ቀንደኛ ጠላት እንደሆነ ተደርሶበታል።
ይህ አክራሪ ነጭ ሽብርተኛ ጽፎታል በተባለ ምሥጢራዊ ሰነድ ማወቅ እንደተቻለው "ጆርጅ ሶሮስ ቀስ በቀስ የነጮችን የበላይነት በአሜሪካና በአውሮፓ ለማጥፋት የሚሰራ ጠላት ነው" ብሎ ያምን ነበር።
ይህ አክራሪ ነጭ ሽብርተኛ የታወረበት የሴራ ፖለቲካ እንደሚያትተው ዓለም ላይ ከመጋረጃ ጀርባ ነጮችን የማዳከምና የነጮችን አገር በጥቁር ስደተኞች ቀስ በቀስ የመሙላት ሐሳብ አለ፤ ይህን ሐሳብ በገንዘብ የሚደግፈው ሰው ደግሞ ጆርጅ ሶሮስ ይባላል። ያንን ጥቃት እንዲያደርስ የተገፋፋውም ይህንን የጆርጅ ሶሮን እንቅስቃሴ ለመግታት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዶናልድ ትራምፕ ሰዎች እጅግ ከማይወዷቸው ቢሊየነሮች ግንባር ቀደሙ ጆርጅ ሶሮስ ነው። በትራምፕ ወዳጆች ዘንድም ሶሮስ ላይ ከባድ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶበት ነበር።
"ሶሮስ ናዚ ነው"፤ "ኦባማና ሂላሪ የሶሮስ አሻንጉሊቶች ናቸው"፤ "አሜሪካን ለማፍረስ የሚተጋው አይሁድ ጠሉ ጆርጅ ሶሮስ ነው" የሚሉ ወሬዎች ኢንተርኔቱን ሞልተውት ነበር አንድ ሰሞን።
የጦር መሣሪያ ቁጥጥር እንዲጠብቅ፤ ጸረ ትራምፕ ሰልፎች እንዲፋፋሙ እንዲሁም የፍሎሪዳ ጥቃትን ተከትሎ የተደረገው "ማርች ፎር አወር ላይቭስ ሙቭመንት" በሶሮስ ገንዘብ የተቀነባበሩ እንደሆነ ይታመናል።
የትራምፕ ተቺዎችን ለመግደል ያለመ የጥቅል ፖስታ ቦምብ እደላ በተደረገበት ወቅትም በቁጥር አንድ የትራምፕ ጠላትነት የተፈረጀው ሶሮስ ነበር።
ሶሮስ ድንበር ይጠላል?
ከመካከለኛው አሜሪካ ኑሮ መረረን ያሉ ስደተኞች ወደ አሜሪካ የእግር ጉዞ ሲጀምሩ ትራምፕ የግምብ አጥሩን ቶሎ እንገንባው በሚሉበት ወቅት ይህንን የሕዝቦች ስደትን የሚደግፈው ጆርጅ ሶሮስ ነው የሚሉ ወሬዎች መነዛት ጀምሩ። ትራምፕም ይህንኑ እንደሚጠረጥሩ ተናግረዋል።
"እሱ ነው ቢሉኝ አልደነቅም፤ እሱ ስለመሆኑ አላውቅም፤ እሱ እንደሚሆን ግን እገምታለሁ፤ አያስደንቀኝም" ብለው ነበር ዶናልድ ትራምፕ ለጋዜጠኞች።
የትራምፕ ልጅ በተዋናይት ሮሰን ባር የትዊተር ሰሌዳ ስለ ሶሮስ የተጻፈውን መራር ጥላቻ ማጋራቱም ምን ያህል ሶሮስ በነ ትራምፕ ቤተሰብ የማይወደድ ቢሊየነር እንደሆነ መገመት አስችሏል። ተዋናይት ባር የጻፈችውና የትራምፕ ልጅ ያጋራው ጽሑፍ እንዲህ ይላል።
"በነገራችሁ ላይ ጆርጅ ሶሮስ ናዚ ነው። የገዛ አይሁድ ጓደኛውን በጀርመን ማጎርያ ካምፕ ውስጥ አስገድሎ ገንዘቡን የዘረፈ ናዚ"
ይህን ተከትሎ የሶሮስ ቃል አቀባይ "እንዲህ ዓይነት መሠረተ ቢስ ክሶች በሶሮስ ሳይሆን በመላው አይሁድ ሕዝብ ላይ የተቃጡ ስድቦች ናቸው፤ በተለይም በጅምላ ፍጅቱ ተጠቂዎች ላይ..." ብሏል።
እርግጥ ነው ሶሮስ አገሮች ነጻ እንዲሆኑ፤ የሕዝቦች ነጻ እንቅስቃሴ እንዲኖር ይተጋል። ይህ ግን አገሮች ድንበር አይኑራቸው ከሚል ጽንሰ ሐሳብ የሚመነጭ አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"የነጮች አህጉር የሆነችውን አውሮፓን በስደተኛ ልታጥለቀልቃት ነው ሀሳብህ"
የጆርጅ ሶሮስ ተቺዎች ሶሮስ በአገራት የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ ይገባል፤ እጁም ረዥም ነው ይሉታል። እርግጥ ነው ለሂላሪና ለኦባማ የምርጫ ዘመቻ ትልቁን ገንዘብ ስለመስጠቱ የሚካድ አይደለም። ይህ ተግባሩ ግን በአሜሪካ ብቻ የሚወሰን አልሆነም።
ሶሮስ በ1980ዎቹ የሀንጋሪ ኮምኒስቶችን ለማዳከም ገንዘቡን አውሎታል። ኦፕን ሶሳይቲ ፋውንዴሽን ለዲሞክራሲ እሴቶች የሚተጋ ነው። በዓመታት ውስጥ ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር ለዚህ ድርጅቱ ፈሰስ አድርጓል ሶሮስ። ይህ ገንዘብ በምንም መለኪያ ትንሽ አይደለም።
"ይህን ድርጅት ያቆምኩት አስተማማኝ ዲሞክራሲን በመላው ዓለም ለመዘርጋት ነው" ይላል፤ እሱም ቢሆን።
ሶሮስ በትውልድ አገሩ ሀንጋሪ ቢሊዮን ዶላሮችን በማፍሰስ የሰብአዊ መብት ፕሮጀክቶችንና በትምህርት ቤቶች ነጻ የምግብ እደላዎች እንዲኖሩ አስችሏል።
ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ጭምር ዝነኛ የሆነውና የውጭ የትምህርት ዕድል በመስጠት የሚታወቀው የሴንትራል ዩሮፒያን ዩኒቨርስቲን (CEU) የመሠረተው ጆርጅ ሶሮስ ነው።
"አንዳንድ ጊዜ ትልቅ ለማይመስሉ ነገር ግን ለምናምንባቸው ነገሮች መቆም አለብን" ይላል ሶሮስ።
ከእነዚህ መሀል አንዱ በስደተኞች ላይ ያለው አቋሙ ነው። በአውሮፓ የሚገኙ ስደተኞችን ለማገዝ የሚተጋው ሶሮስ ከበርካታ አገራት መንግሥታት ጥላቻን አትርፏል። "የነጮች አህጉር የሆነችውን አውሮፓን በስደተኛ ልታጥለቀልቃት ነው ሀሳብህ" የሚል ክስ ይነሳበታል።
እሱም "በስደተኛ ላይ ያለኝ አቋም ብዙ ጠላት አፍርቶልኛል" ይላል።
ለምሳሌ የገዛ ትውልድ አገሩ ሀንጋሪ ለሶሮስ ያላትን ጥላቻ በጎዳና ላይ ቢልቦርድ ጭምር ሰቅላዋለች። አሁን ያለው የሀንጋሪያዊያን መንግሥት በአመዛኙ ጥቁር ጠል የሚባል ነው።
በሀንጋሪ ለስደተኞቸ ድጋፍ የሰጠ ዜጋ በእስር ይቀጣል። የሚደንቀው ታዲያ የዚህን የቅጣት ሕግ ስም ሳይቀር የሃንጋሪ መንግሥት "ስቶፕ ሶሮስ" ብሎ ነው የሚጠራው። ያው ስደተኞችን እያጋዘ የሚያመጣብን ጆርጅ ሶሮስ ነው በሚል።
የሀንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን የሶሮስ ቀንደኛ ጠላት ናቸው።
በስሎቫኪያ የጋዜጠኛ መገደልን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ የተደናገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር፡ "ይሄ የጆርጅ ሶሮስ እጅ ነው። በስሎቫኪያ የተነሳው ነውጥ የሶሮስ ሥራ ነው። እሱ ስደተኛ እንዳይመጣባቸው ለሚፈልጉ አገራት አይራራም። የጎዳና ላይ ነውጥ እያስነሳ ይገለብጣቸዋል" ብለው ነበር።
ሶሮስ ስለሱ ስለሚባለው ምን ይላል?
ጆርጅ ሶሮስ ከአፍሪካ እስከ ምሥራቅ አውሮፓ፣ ከትራምፕ እስከ ሞዲ ስለሱ የሚባለውን ሲሰማ ምን ይላል? በእርግጥ የዓለም ፖለቲካን የሚዘውረው ሰው ጆርጅ ሳሮስ ነው?
"የእኔ እጅ ረዥም እንደሆነ የሚነገረው የተጋነነ ነው። እንደሚባለው የእንግሊዝ ባንክን አላንኮታኮትኩትም። ገበያው ነው ያንኮታኮተው። እንደሚባለው ስደተኛን እያጋዝኩ ወደ አውሮፓና አሜሪካ አላስኮበልልም። ኦፕን ሶሳይቲን የመሠረትኩት ዲሞክራሲንና የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማጎልበት ነው" ይላል።
ጆርጅ ሶሮስ እና ዶናልድ ትራምፕ
ጆርጅ ሳሮስ እንደ ትራምፕ የሚንቀው ሰው ያለ አይመስልም። "ትራምፕ አታላይና በራሱ ፍቅር የናወዘ ሰው ነው" ይላል። ትራምፕን ብሔራዊ ጥቅምን ሳይቀር ለግል ስምና ዝናው አሳልፎ ለመስጠት የማይሳሳ ነው ይለዋል።
የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ዠን ፒንግን ደግሞ በቴክኖሎጂ መላ ሕዝቡን ለመቆጣጠር የሚሞክር አምባገነን ይለዋል።
ዓለማችን ሁለቱን መሪዎች ብታስወግድ የተሻለ እንኖር ነበር ይላል ሶሮስ።
ሶሮስ መጪው ጊዜ አስፈሪ ነው ይላል
ሶሮስ በስዊዘርላንድ ዳቮስ በቅርቡ ባደረገው ንግግር ዘረኝነት በአገራት እየተስፋፋ መምጣቱ እንደሚያሳስበው ተናግሯል። ጥላቻ እንዳይነግስ ለሚሰሩ፣ የመቻቻል ፕሮጀክቶችን ለማጎልበት ደግሞ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 1 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ቃል ገብቷል።
በዘረኞችና በሀሰት ወሬ አራጋቢዎች የምትሾረው ዓለም ለሶሮስ ታሳስበዋለች። ክሪቲካል ቲንኪንግ ወይም ምክንያታዊነትን ቶሎ ካላስፋፋን መጪው ጊዜ አስፈሪ ነው ይላል ሶሮስ። ከመሞቴ በፊት ማድረግ ይመፍልገውም ይህንን ነው።












