ማሽተት የማይችሉ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ይመራሉ?

የፎቶው ባለመብት, Gabriella
መቼም የምንወደው ሽታ ይኖራል፤ የምግብ ወይንም የልብስ አሊያም የምንወደው ሰው ሸታ። ከአንድ ጥሩ ወይንም መጥፎ ትዝታ ጋር አጣምረነውም ይሆናል።
አምስቱ የስሜት ህዋሳት መካከል አንዱ ማሽተት ነው። ጋብሪዬላ ግን ከመወለዷ ጀምሮ ማሽተት አትችልም። እውን ማሽተት አለመቻል ምን ይመስላል?
«ምግብ ምን ምን እንደሚል አላውቅም። ትኩስ ነገርም ሆነ ጣፋጭ ወይም የሚያቃጥል ነገር ምን አይነት ሽታ እንዳለው አላውቅም» ትላለች የ22 ዓመቷ ጋብሪዬላ።
ብዙዎች ማሽተት አለመቻል ምን እንደሚመስል አያውቁት ይሆናል። የማሽተት ችግር ያለባቸው ሰዎች ቁጥር ከ5 በመቶ እንማይዘል ይገመታል።
ማሽተት ያለመቻል ጉዳቶች በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፤ ልማዳዊና ስሜታዊ በሚል። ከልጅነት እስከ አዋቂነት ተከትሎ የሚመጣ ነው።
«ከልጅነቴ ጀምሮ ማሽተት አልችልም። በጣም የሚገርመው ከእኔና እህቴ በቀር ቤተሰባችን ውስጥ ማንም እንዲህ ዓይነት ችግር የለበትም። ምናልባት ከቤተሰብ ዘር ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል።»
ማሽተት እንደማንችል እንዴት እናውቃለን?
ጋብሪዬላ ልጅ እያለች በተዘጋጀ አንድ የትምህርት ቤት ዝግጅት ላይ ምን ያህል ባይተዋርነት ተሰምቷት እንደነበር አትዘነጋውም።
«ሁሉም ጓደኞቼ ስለሽታ ነበር የሚያወሩት። የዚያኔ ነው ማሽተት እንደማልችል የገባኝ። ሁሉም ምሳሌ እያጣቀሰ ሲያወራ እኔ ግን ምንም የማስታወሰው ነገር አልነበረም።»
ጋብሪዬላ ማሽተት አለመቻሏ በልጅነቷ ልታስታውሳቸው የማትፈልጋቸው ክስተቶች እንዲገጥሟት አድርጓል። «እሣት በጣም ነው የምፈራው። ሁሌም የሚያሳቅቀኝ ተኝቼ እያለሁ ቤቴ ቢቃጠል ሽታው እንደማይቀሰቅሰኝ ሳስብ ነው።»
ልጅ እያለች የእሣቱ ሃሳብ በጣም ያስጭንቃት እንደነበር የምታወሳው ጋብሪዬላ አሁን ግን ሁኔታዎችን እየተለማመደች እንደመጣች ትናገራለች።
ልማዳዊ ችግር
ማሽተት የተሳናቸው ሰዎች ላይ ጥናት ያካሄዱት ተመራማሪው ፕሮፌሰር ካርል ፊልፖት ማሽተት አለመቻል ችግር ላይ ሊጥል እንዲሚችል ያሳስባሉ። ጭስ ወይንም የጋዝ ሽታ ማሽተት የማይችሉ ሰዎች ለችግር ሊጋለጡ ይችላሉ ይላሉ።
ጋቢም የምትለው ይሄንኑ ነው። «አስታውሳለሁ አንድ ጊዜ ምግብ እያበሰልኩ እናቴ መጣችና ቤቱ በጋዝ ሽታ መታፈኑን ነገረችኝ። ሁኔታው በጣም አስደንግጦኝ ነበር።»
በመሰል ክስተቶች የታጀበ ሕይወት እንዳሳለፈች የምትናገረው ጋብሪዬላ አሁን እጅግ በጣም ጠንቃቃ ሰው እንደሆነች ትናገራለች።
የውጭውን ዓለም ማሽተት ብቻ አይደለም ትልቅ ችግር የሆነው ይላሉ ተመራማሪው። ጥናቱ ላይ የተሳተፉ ሰዎች ከፍተኛ መሸማቀቅ የሚያደርስባቸው ራሳቸውን ማሽተት ያለመቻላቸው ጉዳይ መሆኑን በመጨመር።
ይህ ያስጨነቃት ጋብሪዬላ አንድ መላ ፈጥራለች። «ከወላጆቼ ጋር ሆነን አንድ መላ ዘየድን - የምልክት ቋንቋ። ከጓደኞቼ ጋር ቤት ስመጣ ጠረኔ ትክክል ካልሆነ አንድ ምልክት ይሰጡኛል፤ የዚያኔ ወደ መታጠቢያ ቤት እሮጣለሁ።
ጋብሪዬላ 'ኮንቴምፖራሪ' የተሰኘ ዳንስ ባለሙያ ናት። ዳንስ ደግሞ ብዙ እንቅስሴ ይጠይቃል።
«ሽቶም ሆነ ሌላ ሽታ ያለው ነገር ኖሮኝ አያውቅም፤ የአበባ ሽታም ሆነ መዓዛ ያለው የገላ መታጠቢያ ኖሮኝ አያውቅም፤ አይመቸኝምም። ቢሆንም ዳንሰኛ ስለሆንኩ 'ዲዮዶራንት' እጠቀማለሁ።»
ጋቢ ማሽተት አለመቻል የሚታፈርበት አይደለም ትላለች። ዋናው ነገር በዙሪያዎ ላሉ ሰዎች ማሽተት እንደማይችሉ ማሳወቅ ነው። ግልፅ መሆን ይጠቅማል ስትል ትመክራለች።
«ሁሌም አጠገቤ ያሉ ሰዎች ማሽተት እንደማልችል እንዲያውቁ አደርጋለሁ። 'እባካችሁ ንገሩኝ፤ አይዟችሁ አልቀየማችሁም' እላቸዋለሁ።»
ጋብሪዬላ ማሽተት ብችል ብላ ተመኝታ ታውቅ ይሆን? - «ኖሮኝ የማያውቅ ስለሆነ ያስፈልገኛል ብዬ ድርቅ አልልም። ብሞክረው ግን ደስ ይለኛል፤ ላጣጥማቸው የማልችላቸወን ነገሮች ማጣጣም እፈልጋለሁ።»













