ጓደኛ ጤና ላይ ያለው ተፅዕኖ እንዴት ያለ ነው?

ጓደኛዎት ጤናዎትን እያቃወሱት ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አዲስ ዓመት ሲመጣ ዕቅድ ይወጣል፤ ውጥን ይወጠናል፤ መላ ይመታል. . . አዲስ ይለበሳል፤ አዲስ ይታሰባል።

ታድያ የግሪጎሪ ቀን ኦቆጣጠር 2020 መምጣቱን ተከትሎ ብዙዎች የአዲስ ዓመት ዕቅዴ ያሉትን ጤናማ ትልም ጀባ እያሉ ነው።

አመጋገብን ጤናማ ከማድረግ ጀምሮ እንቅስቃሴ መጀመር ሰዎች ብዙ ጊዜ ሊተግብሯቸው ዕቅድ ከሚይዙላቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው።

ታድያ ለእነዚህ ዕቅዶች እውን መሆን ጓደኛ፣ ቤተሰብ እና ወዳጅ ዘመድ ትልቅ ቦታ አላቸው። የጓደኞቻችን እና የምናደንቃቸው ሰዎች ባሕሪይ ይጋባብናል። ሌላው ቀርቶ ለጤናችን አስጊ የሆኑ ባሕሪያትን ለምሳሌ ትምባሆ መሳብ እና ብዙ መመገብን ሳይቀር ከወዳጆቻችን እንኮርጃለን።

ይህ ማለት እንደ ካንሰር፣ የልብ ሕመም እና ስትሮክ የመሳሰሉ የማይተላለፉ በሽታዎች ከወዳጅ ዘመድ ይተላለፉብናል ማለት ነው።

ጓደኞቻችን ያለልክ እንድንወፍር ምክንያት ናቸውን?

በሥራ ቦታም ሆነ በምናዘውትራቸው ሥፍራዎች የምናገኛቸው ሰዎች ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው።

ፋርሚንግሃም የተሰኘ የልብ ጥናት ተቋም ማሕበራዊ መስተጋብሮች ጤና ያላቸውን ተፅዕኖ ለበርካታ ዓሥርት ዓመታት ሲያጠና ቆይቷል። ዓመታትን በዘለቀው ጥናት መሠረትም ከልክ ያለፈ ውፍረት ያለው ጓደኛ ካለዎት የእርስዎም ዕጣ ፈንታ ወደዚያው ነው የሚል መደምደሚያ አስቀምጧል።

በተለይ ደግሞ ይላል ጥናቱ ሁለት ተመሳሳይ ፆታ ያላቸው ጓደኛሞች ተመሳሳይ ለሆነ የጤና መጓደል የመጋለጣቸው ዕድል የሰፋ ነው።

ፍቺ፣ ትምባሆ ማጨስ እና አልኮል መጠጣት ከቤተሰብ ቤተሰብ እየወረዱ የሚሙ መሆናቸውን ነው የጥናቱ ውጤት የሚያሳየው።

አልኮል፣ ትምባሆ፣ ያልተመጣጠነ አመጋገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ በዓለማችን ከ10 ሰው 7 ሰው ይቀጥፋሉ።

ማሕበራዊ መስተጋብሮች ዘርፈ ብዙ የባሕሪይና የአመል መቀያየር ችግር ሊያመጡ ይችላሉ። ለምሳሌ አጫሽ አዋቂ ሰዎች የሚበዙበት ማሕበረሰብ ውስጥ የሚያድጉ ታዳጊዎች የማጨስ አዝማሚያቸው ከፍ ያለ ነው።

ታድያ እንዴት አድርገን ከወዳጅ ዘመዶቻችን መልካም መልካሙን መቅሰም የምንችለው?

አውሮጳውያን ከአልኮል የፀዳ ጥቅምት፤ ከሥጋ የፀዳ ጥር. . . በማለት ወራትን እየከፋፈሉ ጤናማ ሕይወት ለመኖር ይተጋሉ። ባለሙያዎች መሰል ክበባት ጤናማ ሕይወት ለመምራት 'አሪፍ መላ' መሆኑን ይጠቁማሉ።

አልፎም ወዳጅ ዘመዶቻችን ጤናማ ሕይወት እንዲመሩ መገፋፋት አስፈላጊ መሆኑን ሳያሰምሩበት አያልፉም። እኛ ጎጂ ተፅዕኖ ከሚያድርብን፤ በጎ ተፅዕኖ ለምን አናሳድርም? ነው ዋናው ቁም-ነገር።