አጭር ወንዶች የፍቅር ጓደኛ ለማግኘት ይቸገራሉ?

ሮበርት እና የቀድሞ የፍቅር ጓደኛው
የምስሉ መግለጫ, ሮበርት እና የቀድሞ የፍቅር ጓደኛው

አለን ሞት የተባለው ጸሃፊ በቅርቡ አጭር ወንዶች የፍቅር ግንኙነቶች ላይ ስላላቸው አመለካከት ጽፎ ነበር። በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ባሰፈረው መልዕክትም እንዲህ ብሏል። ''አጭር ስትሆን ከአስር ሴቶች ስምንቱ ገጽታህን በመመልከት ብቻ የፍቅር ጥያቄህን ውድቅ ያደርጉታል።''

የአለንን ጽሁፍ ያነበቡ ብዙ ሰዎች ምላሻቸውን በመስጠታቸው ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆኗል። ብዙዎች ጥሩና መጥፎ ያሏቸውን አጋጣሚዎች አካፍለዋል። ለመሆኑ አጭር መሆንና የፍቅር ግንኙነት ምን ያህል ግንኙነት አላቸው? እስቲ የአንዳንድ ወንዶችን አስተያየት እናስነብባችሁ።

"አጭር ወንዶች የፍቅር ጓደኛ ለማግኘት እንቸገራለን ይላሉ፤ እኔ ግን ተቸግሬ አላውቅም"- ሮበርት

ስዊድናዊው ሮበርት አንድ ሜትር ከሃምሳ ሴንቲ ሜትር ነው የሚረዝመው። ''ምንም እንኳን ስዊድን የረዣዥም ወንዶች አገር ብትሆንም ከሰዎች የተለየሁ አይነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም''ይላል።

ሁሌም ቢሆን በትንሹ ከአንድ ሜትር ከሰማንያ ሴንቲ ሜትር እስከ አንድ ሜትር ከዘጠና ሴንቲ ሜትር በሚረዝሙ ጓደኞቹ ተከቦ እንደሚኖር የሚገልጸው ሮበርት፤ በሰዎች መሀል ስሆን አይጨንቀኝም ይላል።

''የማልዋሸው ነገር አንዳንድ ጊዜ ረዥም ብሆን ብዬ አስባለው። አጭር ወንዶች የፍቅር ጓደኛ ለማግኘት እንቸገራለን ይላሉ፤ እኔ ግን ምንም ተቸግሬ አላውቅም።''

ሮበርት ከሴቶች ጋር ማንኛውም አይነት ወዳጅነት መመስረት አይቸግረኝም ይላል። "ከነሱ ጋር ማውራት አስጨንቆኝ አያውቅም። አጭርነታቸውን ከአካላቸው የሆነ የጎደለ ነገር እንዳለ አድርገው የሚቆጥሩ ብዙዎች ናቸው። ከኔ ከሚረዝሙም ከሚያጥሩም ሴቶች ጋር የፍቅር ግንኙነት መስርቼ አውቃለው።''

"ከአንድ ሜትር ከሰማንያ በታች የሆኑ ወንዶች በሴቶች በብዛት አይመረጡም"- ክሪስ

ክሪስ የሚኖረው እንግሊዝ፣ ለንደን ውስጥ ሲሆን፤ አንድ ሜትር ከሰባ ሴንቲ ሜትር ይረዝማል። ክሪስ እንደሚለው 'ኦኬኩፒድ' በተባለው የፍቅር አጋር አገናኝ መተግበሪያ ላይ የራሱን ሙከራ አድርጓል።

''በመጀመሪያ ቁመቴ አንድ ሜትር ከሰባ ሴንቲ ሜትር እንደሆነ ገልጬ ነበር፤ መልዕክት ከላኩላቸው ሴቶች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ምላሽ የሰጡኝ ሲሆን፤ እነሱም ቢሆን ሜትር ከሰማንያ በታች የሆነ ወንድ ብዙም እንደማያስደስታቸው ገልጸውልኛለል።''

ክሪስ እንደሚለው፤ መተግበሪያው ላይ ቁመቱ ሜትር ከሰማንያ አምስት እንደሆነ አድርጎ አስተካከለ። "በሚገርም ሁኔታ ብዙ ሴቶች ግንኙነት መመስረት እንደሚፈልጉ ገለጹልኝ። እኔ መልዕክት ከላኩላቸው መካከልም 50 በመቶዎቹ የፈቃደኝነት ምላሽ ሰጡኝ።''

"የቀድሞ የፍቅር ጓደኛዬ አጭር ወንድ ትወድ ነበር"- አድሪያን

አድሪያን አንድ ሜትር ከስልሳ ሶስት ሴንቲ ሜትር ይረዝማል። የአነስተኛ ጀልባ ቀዘፋ ተወዳዳሪ ነው። በ1984ቱ የሎስ አንጀለስ ኦሎምፒክ ከቡድን ጓደኞቹ ጋር በመሆን ለአገሩ እንግሊዝ የወርቅ ሜዳልያ አስገኝቷል።

አድሪያን እና የቡድን ጓደኞቹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አድሪያን እና የቡድን ጓደኞቹ

በቁመቴ ምክንያት ምንም አይነት ጥቃት ደርሶብኝ አያውቅም የሚለው አድሪያን፤ በፍቅር ግንኙነት ዙሪያ ቢሆንም እድለኛ እንደነበር ይገልጻል።

''የቀድሞ የፍቅር ጓደኛዬ አጭር ወንድ ትወድ ነበር። እሷ ሜትር ከሰማንያ ብትሆንም አንድም ቀን እንደ ችግር ስታነሳው ሰምቻት አላውቅም። እንደውም ሰዎች ሁለታችንን አይተው በልዩነቱ ሲገረሙ ምንም ችግር የለውምኮ ትላቸዋለች።''

አንድርያን አክሎም ''ሰዎችም ቢሆን በጣም ጥሩ ባህሪ ቢኖረው ነው እንጂ እንዴት አብረው ሆኑ ብለው ያስባሉ። በዘመናዊው የፍቅር ግንኙነት ዓለም ውስጥም ብዙ ሴቶች አጭር ወንዶችን ምርጫቸው ሲያደርጉ አይታዩም" ይላል።

በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያ የሆኑት አዳም ጎፕኒክ እንደሚሉት፤ ምንም እንኳን አጫጭር ወንዶች በብዙ ሴቶች ለፍቅር ግንኙነት ባይመረጡም ወደ ትዳር ከገቡ ግን በጣም ታማኝና የተረጋጉ ባሎች ይሆናሉ።