እራስን ለማጥፋት ከማሰብ ወደ ሚሊየነርነት

ሪቻርድ ፒርሰን እና ኤንዲ ፐዶኮምብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሪቻርድ ፒርሰን እና ኤንዲ ፐዶኮምብ በ1212 የራሳቸውን ድርጀት መስርተዋል

ኤንዲ ፐዶኮምብ እንደማንኛውም እንግሊዛዊ ኑሮውን ይገፋ ነበር። ነገር ግን በድንገት ባጋጠሙት አሳዛኝ ሁነቶች ሕይወቱ አስቦት ወደማያውቀው አቅጣጫ ተጉዛለች።

የ22 ዓመት ወጣት እያለ በአንድ ምሽት ከጓደኞቹ ጋር ለመዝናናት በመዲናዋ ለንደን ወደሚገኝ ግሮሰሪ ጎራ ይላሉ። ከግሮሰሪው ወጥተው በር ላይ ቆመው ሳለ አንድ ያልጠበቁት አስደንጋጭ ነገር ተከሰተ።

ጠጥቶ ሲያሽከረክር የነበረ አንድ ግለሰብ በፍጥነት መጥቶ ገጫቸው። በአደጋው ኤንዲ ሁለት የሚወዳቸውን ጓደኞቹን አጣ። ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ እህቱ በሳይክል አደጋ ሕይወቷ አለፈ።

ሃዘኑ በዚህ አላበቃም ነበር። የቀድሞ የፍቅር ጓደኛው ሆስፒታል ውስጥ ቀዶ ጥገና እየተደረገላት በድንገት ሞተች።

በወቅቱ ኤንዲ በስፖርት ሳይንስ ዲግሪውን ለመያዝ እየተማረ ነበር። ነገር ግን በድንገት ባጋጠሙት አሳዛኝ ሁነቶች ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገደደ። በተደጋጋሚም እራሱን ለማጥፋት ይፈልግ ነበር። በመጨረሻ ግን ወደ ሂማልያ ተራራ ለመጓዝና የቡድሃ መነኩሴ ለመሆን ወሰነ።

ሙሉ የእስያ አህጉርን በመዞር ለ10 ዓመታት በጥሞናና በተመስጦ አሳለፈ። በቀን ለ16 ሰአታትም ያለምንም እንቅስቃሴ በጥሞና ያሳልፍ ነበር። በዚህ ምክንያት በሕይወቱ ለነበሩት ብዙ ጥያቄዎችም ምላሽ ማግኘቱን ኤንዲ ይናገራል።

''አስተሳሰቤ በሙሉ ተቀይሯል- ስለራሴ እያሰብኩ የማሳልፈውን ጊዜ እንድቀንስ እና ስለሌሎች ሰዎች ደስታ እንዳስብ አድርጎኛል'' ይላል የአሁኑ የ46 ዓመት ጎልማሳ።

ኤንዲ ፐዶኮምብ

የፎቶው ባለመብት, Andy Puddicombe

የምስሉ መግለጫ, ኤንዲ ፐዶኮምብ

ጓደኞቹና የቅርብ ቤተሰቦቹ በመጀመሪያ አካባቢ በሁኔታው ተደናግጠው ነበር። ''እንዴት የተደላደለ ሕይወቱን ትቶ ተራራ ላይ ሄዶ መነኩሴ ይሆናል? '' እያሉ ያስቡ ነበር ይላል ኤንዲ።

እ.አ.አ. በ2005 ኤንዲ ወደ ትውልድ አገሩ እንግሊዝ በመመለስ ጥሞናን ለአገሩ ሰዎች ለማስተዋወቅ ሞክሮ ነበር። ነገር ግን እምብዛም ተቀባይነት አላገኘም።

ለንደን ውስጥ የራሱን የጥሞና ማስተማሪያ በመክፈት የብዙ ሰዎችን ሕይወት ቀስ በቀስ መቀየር መቻሉን ይናገራል።

ዛሬ ላይ ኤንዲ እና ባልደረባው ሪቻርድ ፒርሰን በጥምረት የሰሩት የጥሞና መተግበሪያ በጣም ተወዳጅ ሆኖ 16 ሚሊየን ሰዎች በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ላይ ጭነውታል። በዓመት እስከ 100 ሚሊየን ዶላር ትርፍም ያገኙበታል።

ባልደረባው ሪቻርድ በ2005 ከኤንዲ ጋር ሲተዋወቅ በሥራውና በሕይወቱ ደስተኛ አልነበረም። ጥሞናን ከተማረ በኋላ ግን ብዙ ነገሮች ባላሰበው ፍጥነት መቀየር መጀመራቸውን ያስታውሳል።

''ይሄን የመሰለ ሕይወት የሚቀይር እውቀት ይዞ በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ጊዜውን ሲያሳልፍ ማየት ከባድ ነበር። ለዛም ነው ትምህርቶቹን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሳደግ የሚችልበትን መንገዶች ማውራት የጀመርነው። እሱ ጥሞናን አስተማረኝ እኔ ደግሞ ብዙ ሰዎችን መድረስ የሚችልትን መንገድ አሳየሁት።''

ቀስ በቀስ የኤንዲ እና ሪቻርድ ተቀባይነት እጨመረ መጥቶ በእንግሊዝ ስማቸውን የማያውቅ ሰው ጠፋ። ብዙዎችም በኤንዲ ትምህርቶች ሕይወታቸውን ማስተካካል ስለመቻላቸው ምስክረነቶችን ሰጥተዋል።

ከአምስት ዓመታት በኋላ በ2010 ሙሉ እንግሊዝን በመዞር ብዙ ትምህርቶችን ሰጥተዋል። በ2013 ደግሞ መቀመጫቸውን ከለንደን ወደ አሜሪካዋ ሎስ አንጀለስ ከተማ አዞሩት።

በአሁኑ ሰአት ድርጅታቸው 300 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ከጥሞና ባለፈ በተለያዩ ጤና ነክ ሥራዎች ላይም ብዙ ሚሊየን ዶላሮችን ፈሰስ በማድረግ ይሠራል።

ከዚህ ባለፈም እንደ ጉግል፣ ሊንክድኢን፣ ጀነራል ኤልክትሪክና ዩኒሊቨር ከተባሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በትብብር ይሠራል። ለድርጅቶቹ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ዕለታዊ የጥሞና ትምህርቶችን ይሰጣል።

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመዘዋወርም ስለ ጥሞና ጥቅሞች ያስተምራሉ።