ታይላንድ፡ ታዳጊዎች ለ17 ቀናት መውጣት አቅቷቸው የቆዩበት ዋሻ ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ

የፎቶው ባለመብት, EPA/CHIANG RAI PROVINCIAL PUBLIC RELATIONS OFFICE
ባለፈው ዓመት 12 ታዳጊዎች አንድ ዋሻን ለመጎብኘት በገቡበት ዋሻው በውሃ በመሞላቱ ለ17 ቀናት መውጣት ሳይችሉ መቅረታቸው ይታወሳል። ታዲያ ይሄው ዋሻ ከአንድ ዓመት በኋላ ተከፍቶ ታይላንዳውያን መጎብኘት ጀምረዋል።
ኳስ ተጫዋቾቹ ልጆችና አሰልጣኛቸው ለዘጠኝ ቀናት ያህል ያሉበት ባለመታወቁ ጠፍተዋል ተብሎ የነበረ ሲሆን፤ በአስረኛው ቀን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በዋሻው ክፍተት በኩል ተመልክተዋቸዋል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞቹ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶች ለማድረስ ሲታገሉም ነበር።
ትናንት (አርብ) ከሰአት ላይ ለጎብኚዎች ክፍት የሆነውን ዋሻ ከአደጋው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙ ተመልካቾች ለመሆን 2000 ታይላንዳውያን ወደ ስፍራው መጉረፋቸው ተገልጿል።
'ዋይልድ ቦር' የሚል ቅጽል ስም ያለው የእግር ኳስ ቡድን አባላት የሆኑት ታዳጊዎች ከአሰልጣኛቸው ጋር በመሆን ወደ ዋሻው ከገቡ በኋላ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ በማጋጠሙ መውጣት እንዳልቻሉ እንደተሰማ የመላው ዓለምን ቀልብ ስበው ነበር።
ከ17 ቀናት በኋላም ከ90 በላይ የውሃ ጠላቂዎች በተሳተፉበት የማዳን ሥራ ከዋሻው መውጣት ችለዋል።
ባለፈው ዓመት ብቻ ከአንድ ሚሊየን በላይ ጎብኚዎች ዋሻውን የጎበኙ ሲሆን፤ በአደጋው ምክንያት በመዘጋቱ ግዛቲቱ ከፍተኛ የገቢ መቀነስ እንዳጋጠመ አስታውቃ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, EPA/CHIANG RAI PROVINCIAL PUBLIC RELATIONS OFFICE
የዛሬ ዓመት ምን ተፈጠረ?
ከሳምንት በላይ ጠፍተው የነበሩት 12 ታይላንዳውያን ልጆችና የእግር ኳስ አሰልጣኛቸው በታይላንድ ዋሻ ውስጥ በሕይወት እንዳሉ ታውቆ፤ ዋሻው በጎርፍ በመሞላቱ ጎርፉ እስኪቀንስ ለወራት መጠበቅ፤ ወይም ደግሞ ዘለው በዋና ሊወጡ እንደሚገባም ተገልጾ ነበር።
በመጀመሪያ ልጆቹ እንደሚገኙ ያወቁት እንግሊዛውያን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች፤ ልጆቹ ጎርፍ በሞላው ዋሻ አጠገብ በሚገኝ አፋፍ ተቀምጠው እንደታዩና በጣም እንደተራቡ ገልጸዋል።
በመጀመሪያ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ለታዳጊዎቹ ምግብና መጠጥ ለማድረስ ተቸግረው ነበር። በዚህ ሁኔታም ለ17 ቀናት የመላው ዓለም አይን የታይላንዱ ዋሻ ላይ ሆኖ ነበር።
ዋሻው የሚገኝበት ሰሜናዊ ታይላንድ በዝናብ ወቅት በጎርፍ የሚጥለቀለቅ ሲሆን፤ ይህም እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ የሚቀጥል ነው።












