የህጻናትን ዘረ መል ማስተካከል ክልክል ነው?

ማህጸን ውስጥ ያለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰው ልጆች ተክሎችን ማዳቀልና እንደገና መፍጠር ይችላል። ይህ ብቻም ሳይሆን የእንስሳትን ተፈጥሮ መቀየርና የሰው ልጅ የዘረ መልን እስከ ማስተካከልም ተደርሷል።

በቅርቡ አንድ ቻይናዊ ተመራማሪ የመንትዎችን ፅንስ ኤች አይ ቪ ኤድስ እንዳይዛቸው አድርጎ ውስጣዊ አወቃቀራቸውን አስተካክያለው ማለቱም የሰሞኑ ዜና ነው።

ነገር ግን የሰው ልጅን ተፈጥሮአዊ የዘረ መል አወቃወር መቀየርና ማስተካከል በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት የሌለውና እንደውም እንደ ወንጀል የሚቆጠር ነው።

ቻይናዊው ፕሮፌሰር እንደሚለው ከመንትዮቹ ሽል ውስጥ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ንጥረ ነገሮችን በማስወገድ ብቻ ኤች አይቪ በሽታ እንዳይዛቸው ማድረግ ችሏል።

እንደዚህ አይነቶቹ የዘረ መል ጥናቶች አንዳንድ ከቤተሰብ የሚተላለፉ በሽታዎችንም ለማስቀረት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።

የዘረ መል ማስተካከያው መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ነገር ግን ገና ባልተወለዱ ህጻናት ላይ የሚከናወነው የዘረ መል ማስተካከልና መቀየር ሂደት ለሚቀጥለው ትውልድ የሚተላለፍ ችግር ሊሆን እንደሚችል የሚሰጉ ብዙዎች ናቸው።

በገዛ እራሳችን ምርምር በሽታን ብንፈጥርስ የሚሉም አልጠፉም። ብዙዎቹ ሙከራዎችም በሰዎች ላይ ባይደረጉ ይመርጣሉ።

እንግሊዝ ውስጥ ተመራማሪዎች መወለድ የማይችሉ ጽንሶች ላይ የዘረ መል ማስተካከል እንዲያደርጉ የሚፈቀድላቸው ሲሆን፤ ምንም አይነት ችግር የሌለባቸውና ያለምንም ችግር መወለድ የሚችሉ ጽንሶች ላይ ግን ምርምሩን ማካሄድ ክልክል ነው።

አሜሪካ ከዚህ ጋር በተያያዘ ቀለል ያለ ህግ ያላት ሲሆን፤ ጃፓን ደግሞ ምረምሩን ለመፍቀድ እያሰበች ነው ተብሏል።

ቻይናዊው ሳይንቲስት የሚሰራበት ሸንዘን የሚገኘው ሳውዘርን ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ ስለ ምርምሩ ምንም እንደማያውቅ ጠቅሶ በአስቸኳይ ምርመራ እንደሚጀምርም አሳውቋል።

በቻይና ህግ መሰረት ገና ባልተወለዱ ህጻናት ላይ የዘረ መል ማስተካከያ ምርምሮችን ማድረግ ክልክል ነው።

የሃገሪቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምክትል ሚኒስተር ዡ ናንፒንግ እንደተናገሩት ዜናውን ሲሰሙ በጣም ደንግጠዋል። ሰውዬው የሰራው ምርምርም የቻይናን ህግ የጣሰ ህገወጥ ተግባር ነው ብለዋል።

የካንሰር በሽታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በለንደኑ ሴንት ጆርጅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሰሩት ዶክተር ያልዳ ጃምሺዲ እንደሚሉት የዘረ መል ማስተካከል የተደረገባቸው ህጻናት ወደፊት ምን አይነት ችግሮች ሊገጥሟቸው እንደሚችል ማወቅ ከባድ ነው።

ከዚህ ለየት ያለ ሃሳብ ያላቸው ደግሞ ምርምሩ ሊያመጣ የሚችለውን ችግር ካለማወቃችን በተጨማሪ ይላሉ፤ የዘረ መል ማስተካከል የተደረገባቸው ህጻናት ከሌሎች የተለዩ ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ ይላሉ።

ይህ ደግሞ ከሌሎች የተለየ ጥቅም እንዲያገኙ አልያም እንዲገለሉ ሊያደርጋቸው እንደሚችል በመጥቀስ መቅረት አለበት በማለት ይከራከራሉ።

ፅንሱ ላይ የተቀየረው የዘረ መል አይነት ወደፊት ለሚቀጥለው ትውልድ የሚተላለፍ እንደሆነ በመስጋትና በተፈጥሮ ጣልቃ መግባት መሆኑን በማሰብ ብዙዎች መከልከል አለበት ቢሉም፤ ቻይናዊው ሳይንቲስት ግን በሽታ ሳይከሰት በፊት ማስቀረት ምንድነው ችግሩ ባይ ነው።

እ.አ.አ. በ2012 የተጀመረው የዘረ መል ማስተካከል ምናልባት ሃያላን ሰዎችን ለመፍጠር ጥቅም ላይ ውሎ በዓለማችን ያለውን የአቅምና የጉልበት ልዩነት ይበልጥ እንዳያሰፋው የሚሰጉም አልጠፉም።