ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለ20 ዓመታት ብትገታ እንደሚቀበሉ ተናገሩ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ 'በኤር ፎርስ ዋን' ከጋዜጠኞች ጋር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቴህራን ለ20 ዓመታት የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ብትገታ እንደሚቀበሉ ያሳወቁ ሲሆን፤ ይህም ከዚህ በፊት ሙሉ ለሙሉ ማቆም አለባት ከሚለው አቋማቸው ለውጥ ማድረጋቸውን አሳይቷል።

ትራምፕ "እውነተኛ 20 ዓመት" መሆን አለበት ብለዋል።

ቀደም ሲል ፕሬዝዳንቱ ኢራን መሣሪያ ማምረት በሚያስችላት ደረጃ ዩራኒየም ማበልፀጓን ሙሉ በሙሉ እንድታቆም እና የኒውክሌር መሣሪያ ፈጽሞ እንዳታመርት ጠይቀው ነበር።

ፕሬዚዳንቱ ኢራን ላይ ያላቸው ተስፋ እየተሟጠጠ እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፤ እስካሁን በሚደረጉ ንግግሮች ወደ መፍትሄ ለመድረስ የታየ ምንም ምልክት የለም።

የእስራኤልና የአሜሪካ ጦሮች ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ ጦርነት ከፍተዋል። ካለፈው ወር ጀምሮ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የሰላም ውይይቶቹን ለማካሄድ ያስችላል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳይገኝ ቀርቷል።

በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገውን ንግግር ፓኪስታን እያሸማገለች ትገኛለች።

ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች በሀሳብ ተራርቀው የታዩ ሲሆን፤ አገራቱ ጦርነቱን ለማስቆም የቀረቡትን ሀሳቦች ውድቅ አድርገዋል።

የኢራን መገናኛ ብዙኃን ቴህራን ያቀረበችው ዕቅድ ጦርነቱን በሁሉም ግንባር በአፋጣኝ መቋጨት የሚያስችል እንደሆነ ዘግበዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሁሉም ግንባር የሚለው የሚያመላክተው የኢራን አቋም በሊባኖስ የሚገኘው እና በቴእሀራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ላይ የእስራኤል ጥቃቶች እነዲቆሙ እንዲሁም የአሜሪካ የባሕር ኃይል የዘጋውን የአገሪቱን ወደቦች እንዲከፍት እና ተጨማሪ ጥቃት እንዳይኖር ዋስትና መስጠትን እንደሚያካትት ተነግሯል።

ትራምፕ በቤይጂንግ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ውይይት ካደረጉት በኋላ 'በኤር ፎርስ ዋን' አውሮፕላን ላይ ለጋዜጠኞች፤ ሁለቱም ወገኖች ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት እና የሆርሙዝ ወሽመጥን መልሳ እንድትከፍት መስማማታቸውን ተናግረዋል።

አንድ ጋዜጠኛ ለ20 ዓመት የኒውክሌር መርሃ ግብርን መግታት በቂ አይደለም ብሎ ሲጠይቅ፣ ትራምፕ "20 ዓመት በቂ ነው፤ ግን ከእነርሱ የሚመጣው የዋስትና ደረጃ እውነተኛ 20 ዓመት መሆን አለበት" ሲሉ መልሰዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከዚህ ውጭ ማብራሪያ አልሰጡም።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ባለፈው ሚያዚያ ወር እንደዘገቡት ከሆነ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢዝላማባድ በተካሄደ ንግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ኢራን ለአምስት ዓመታት ዩራኒየም ማበልፀግ እንድታቆም ያቀረበችውን ሀሳብ ቢያንስ 20 ዓመት መሆን አለበት ብለው ምላሽ ሰጥተዋል።

ነገር ግን 20 ዓመት የሚለውን የጊዜ ገደብ አሁን ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳነሱት ይታመናል።

ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው እአአ በ2015 ዓ.ም በኦባማ አስተዳደር ወቅት ከኢራን ጋር የተደረሰውን የኒውክሌር ስምምነት ሰርዘዋል።

እስካሁን እስራኤል በትራምፕ ንግግር ዙሪያ አስተያየት አልሰጠችም። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን ጦርነቱ ተቋጭቷል ከመባሉ በፊት የኢራን የበለፀገ ዩራኒየም ከአገሪቱ "መውጣት" አለበት ብለዋል።

ኔታንያሁ የ2015 የኒውክሌር ስምምነትን በእጅጉ ተቃውመው ነበር።