ሬፓን የሸርኮሌው ስደተኛ፡ የድንቅ ሥራዎች ፈጣሪ

ሬፓን ከሸምበቆ የገነባው ቤት ፊት

የፎቶው ባለመብት, REPAN

የምስሉ መግለጫ, ሬፓን ከገነባው ቤት ፊት

ይህ ሬፓን ሳዲቅ ነው። ከጀርባው የሚታየው ደግሞ ለመገንባት ሰባት ወራት የፈጀበት፣ በሸርኮሌ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሚገኘው ባለ 2 ፎቅ መኖሪያ ቤቱ ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ ሬፓን የኢትዮጵያን መሬት የረገጠው ገና በአንድ ዓመቱ ነበር። ሱዳን በጦርነት ስትታመስ ነው ቤተሰቡ የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጦ ሸርኮሌ የስደተኞች መጠለያ የገባው።

ያኔ ጨቅላ ነበር፥ ከሚነግሩት ውጪ ሁኔታዎች እንዴት እንደነበሩ አያስታውስም፤ ሁኔታዎች ተረጋግተዋል ተብሎ ወደ ትውልድ ስፈራው ከተመለሰ በኋላ ግን ያሰበው ሁሉ እንዳልነበር በመሆኑ ለሁለተኛ ጊዜ ስደተኛ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ግድ ሆኖበት ከዓመታት በኋላ ተመልሷል።

የዛሬ 14 ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ባለቤቱንና ስድስት ልጆቹን ይዞ ሲመጣ የ25 ዓመት ወጣት ነበር። ሬፓን ዛሬም ኑሮውን በቤኒንሻንጉል ጉሙዝ በሸርኮሌ የስደተኞች መጠለያ ነው።

ሬፓን ሱዳን እያለ የእንጨት ሥራ ባለሙያ ነበር። አባቱም የብረትና የእንጨት ሥራ ባለሙያ ነበሩ። ታዲያ ይህ የእጅ ሙያው በአካባቢው ታዋቂ አድርጎታል፤ ታዋቂነቱም ከሸርኮሌ መጠለያ አልፎ አዲስ አበባ ድረስ የናኘባቸው ጊዜያትም ነበሩ። በተለያዩ የስደተኛ መጠለያዎችም ሥራዎቹን ያቀርባል።

ሬፓን በሸርኮሌ መጠለያ ውስጥ ከሚያገኛቸውና አልፎ አልፎ ደግሞ ጥቅም ላይ ውለው ከተወገዱ ዕቃዎች የተለያዩ ፈጠራዎችን ይሰራል።

ቀን ቀን በካምፕ ውስጥ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር የስደተኞች ልጆችን የእጅ ሙያ ያስተምራል። ማታ ማታ ደግሞ ልቡን የሚያስደስተውን ነገር በመሥራት "በቂ እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር" እንደሚነጋ ይናገራል።

የሱዳን ዜናን ለማዳመጥ የሠራት ራድዮ

የፎቶው ባለመብት, REPAN

የምስሉ መግለጫ, የሱዳን ዜናን ለማዳመጥ የሠራት ራድዮ

ኢትዮጵያ ከመጣ ሬፓን የሚታወቀው በቀን ለሦስት ሰዓታት ብቻ እንቅልፍ በመተኛቱ መሆኑን የሚናገረው ሬፓን፤ ለእራሱ መኖሪያቤት ገንብቷል።

"ለመኝታ ያን ያህል ጊዜም የለኝ" የሚለው ሬፓን "ቡና እጠጣና ሌሊቱን ስሠራ አድራለሁ። በመጀመሪያ ግን በጭንቅላቴ ሃሳቡን ካውጠነጠንኩ በኋላ እና እንዴት እንደምሠራው ከደረስኩበት በኋላ ብቻ ነው ወደ ዋናው ሥራ የማመራው" ይላል።

የሚኖርበትን ቤት ገንብቶ ለመጨረስ ሰባት ወር እንደፈጀ የሚናገረው ሬፓን ከዚያ በኋላም እጆቹን አጣጥፎ አልተቀመጠም።

ቀስ በቀስ የሚያስፈልጉትን የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶችን ሰራ። በቤቱ የሚገኙት የውሃ ማሞቅያ፣ አየር ማቀስቀዣ እና ሌሎች የእጅ ስራው ውጤቶች ናቸው።

በዚህ ዓመት በተከበረው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን ሬፓን በአቅራብያው ወዳለው የባምባሲ የስደተኞች ካምፕ ተጋብዞ ሄዶ ነበር። የሠራውን ለየት ያለ የሙዚቃ ማጫወቻ መሣሪያ ይዞ በመሄድም የተለያዩ ክልሎችን ሙዚቃዎች በማጫወት በክብረ በዓሉ ላይ ተሳትፏል።

ለሙዚቃ ማጫወቻው ራሱን የቻለ 72 ዘፈኖችን የሚይዝ 'ሜሞሪ ካርድ' በአሉሚንየም ሠርቶለታል።

ሬፓን ሥራዎቹን ለመሥራት የሚጠቀምባቸው ዕቃዎች ከእንጨት፣ ከቀርከሃ፣ ከአሉሚንየም እና ከካርቶን አያልፍም።

ሬፓን የፈጠራ ውጤቶቹን ሲሠራ እንደ ግብዓት የተጠቀመባቸው ዕቃዎች በቀላሉ በአካባቢው የሚገኙ ቢሆኑም፤ እስካሁን አስቸጋሪ የሆነበት መሣሪያዎቹ በባትሪ ድንጋይ መሥራታቸው ነው። ቀስ ብሎም በፀሐይ ኃይል እንዲሠሩ ለማድረግ እንደሚያስብ የነገረን ሬፓን ሁሉም ባይሆን ቢያንስ የውሃ ማሞቂያው በፀሐይ እንዲሠራ ማድረጉን አጫውቶናል።

ሬፓን እና ቤተሰቡ

የፎቶው ባለመብት, REPAN

የምስሉ መግለጫ, ሬፓን እና ቤተሰቡ

ሬፓን አሁን በካምፑ ላሉት ስደተኞች በሙሉ ለእራሱ የሠራው ዓይነት ቤት መገንባት ፍላጎት እንዳለው ይናገራል። የሚገነባውን ፎቅ ቤት ከዋናው መንገድ በማይርቅ ቅርበት በማሳረፍ ጎብኚዎች እየመጡ እንዲያዩለት እንደሚያደርግ ነግሮናል።

"አንዳንዴ የሚያሰፈልጉኝን ነገሮች ለመግዛት ስወጣ ድንገት ሰዎች ገብተው ዕቃ ቢወስዱ፤ ስመለስ በመቆጣጠሪያ ክፍሌ ገብቼ የተፈጠረውን ነገር ማየት እችላለሁ" የሚለው ሬፓን በእጁ የሠራው የመቆጣጠሪያ መሣሪያ በቤቱ የሚፈጠረውን በሙሉ ቀርፆ እንደሚጠብቀው ገልጾልናል።

የቤቱ መቆጣጠሪያ መሣሪያ

የፎቶው ባለመብት, REPAN

የምስሉ መግለጫ, የቤቱ መቆጣጠሪያ መሣሪያ

የሬፓን ተሰጥዖ በእርሱ ብቻ የሚቀር አይመስልም፤ የዘጠኝ ዓመት ልጁ የሚሠራቸው አብዛኛዎቹን ሥራዎች እንደሚያግዘው ገልጾ፤ ወደፊትም ከልጁ ጋር በመሆን ብዙ ሥራዎችን እንደሚሠሩ እና ከአባቱ የተረከበውን ሙያ ወደ ልጁ ማስተላለፍ መቻሉ እርካታ እንደሚሰጠው ይናገራል።

ሬፓን "የምመኘው ነገር ቢኖር በስደተኛ ካምፕ ያሉት ሰዎች በሙሉ የእራሳቸውን ቤት መገንባት እንዲችሉ ማድረግ ነው" ይላል።