የ27 ፈጠራዎች ባለቤት የሆነው የ17 ዓመቱ ታዳጊ ኢትዮጵያዊ፡ ኢዘዲን ካሚል

ኢዘዲን ካሚል ለፈጠራ ሥራዎቹ ከጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ሰርቲፊኬት ሲቀበል

የፎቶው ባለመብት, Asegid Sileshi

የምስሉ መግለጫ, ኢዘዲን ካሚል ለፈጠራ ሥራዎቹ ከጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ሰርቲፊኬት ሲቀበል

በፀሐይ ኃይል ያለ ፔዳል እንደ ሞተር የሚንቀሳቀስ ብስክሌት? ...

... በተራመዱ ቁጥር ስልክዎን ቻርጅ ለማድረግ የሚበቃ ኃይል ከፀሐይ የሚያመነጭ ጫማ፣ የዘይት ጄሪካን ላይ ስልክ ተገጥሞለት የእሳት አደጋ ሲከሰት ጥሪ የሚያደርግ መሣሪያ፣ ድንገት ቁርስ ሠርተው ከረፈደብዎ ምድጃ ማጥፋት ረስተው ወደ ሥራ ቢሄዱ ከስልክዎ የሚያጠፉት ማብሰያና ከሌሎች 23 የፈጠራ ሥራዎች በስተጀርባ አንድ ታዳጊ አለ ኢዘዲን ካሚል።

ኢዘዲን ካሚል የ17 ዓመት ኢትዮጵያዊ ወጣት ሲሆን እስካሁን በአጠቃላይ 27 የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የፈጠራ ሥራዎችን ከ14 ዓመቱ ጀምሮ ሲሠራ ቆይቷል። ሃሳቦቹን ከየት አመጣቸው? ለፈጠራስ እንዴት ተገፋፋ? ወደፊትስ ምን የማድረግ ሕልም አለው?

ኢዘዲን ካሚል

ኢዘዲን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሲሆን ያደገው የወልቂጤ ክፍለ ከተማ በሆነችው ጉብሬ ውስጥ ነው። ወደ ቴክኖሎጂ ፊቱን ሲያዞር ገና የ14 ዓመት ታዳጊ የነበረ ቢሆንም ለፈጠራዎቹ ከተለያዩ ተቋማት ከሥራዎቹ በቁጥር የማይተናነሱ ሰርቲፊኬቶች ተሰጥተውታል።

ያደገበት ከተማ ለቴክኖሎጂ ያላት ቅርበት እንደ አዲስ አበባ ስላልሆነ ለፈጠራ ሥራው የሚያስፈልጉት እንደ ላፕቶፕ፣ ኢንተርኔትና ሌሎች ቁሳቁሶችን እንደልብ አለማግኘቱ ኢዘድንን ተስፋ አላስቆረጠውም።

ለዚህም በአካባቢው ከሚያገኛቸውም ሆነ አንዳንድ ጊዜ አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ አገልግለው የተወገዱ ወይም የወዳደቁ ዕቃዎችን ከመርካቶ በትንሽ ዋጋ በመግዛት ያሰባቸውን አዳዲስ ፈጠራዎች እውን እንደሚያደርግ ይናገራል።

ከፀሐይ ኃይል ማመንጨትንና ባደጉ ሃገራት ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ አጠቃላይ የቤት ውስጥ መገልገያ ቴክኖሎጂዎችን አስቦና አስተውሎ መሥራት ያልተሳነው ይህ ወጣት "ማንም ሰው ምንም ነገር ለመፍጠር ሲያስብ ከችግር ተነስቶ ነው ሊፈጥር የሚችለው" በማለት የሥራዎቹን መነሻ ምክንያት ይናገራል።

በጫማ ቻርጅ የሚደረግ ስልክ

የፎቶው ባለመብት, Ezedin Kamil

የምስሉ መግለጫ, በጫማዎ ስልክዎን ቻርጅ ማድረግ አስበው ያውቃሉ?

የኢዘዲን የፈጠራ ሥራዎች

ብዙውን ጊዜ በቀን ሩጫ የተጠመደ ሰው ማለዳ ስልኩን ሙሉ በሙሉ ቻርጅ አድርጎ ቢወጣም አንዳንድ ጊዜ በቀኑ መጨረሻ ግን የስልኩ ባትሪ ሊያልቅ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች አይጠፉም።

አንዳንዴ ለአካባቢ ብክለት ታስቦም ይሁን ብዙ ገንዘብ የማያስወጣና የማያደክም የትራንስፖርት አማራጮችን የሚፈልጉም ሰዎች ከመካከላችን ላይጠፉ ይችላሉ።

አልፎ አልፎ በችኮላ መካከል ጠዋት ተጥዶ የነበረውን ሻይም ሆነ መጥበሻ እዚያው ከማብሰያው ላይ ተረስቶ የሚወጡባቸውም ቀናት ሊያጋጥሙ ይችላሉ ወይንም የተረሳ ሻማ ቃጠሎ የሚፈጥርበት ጊዜስ ብለን ብናስብ. . . ?

ለእንደዚህ ዓይነት የዕለት ተዕለት ችግሮችና ከባድም ሆነ ቀላል ጉዳትን ሊያስከትሉ ለሚችሉ አደጋዎች መፍትሄ የሚሆኑ ዘዴዎችን ኢዘዲን ሠርቷል። የፀሐይን ኃይል በመጠቀም የእጅ ስልክ ቻርጅ የሚያደርግ ጫማ፣ ተቀምጠው ብቻ የፀሐይን ብርሃን በመጠቀም እንደ ሞተርሳይክል ያለ ፔዳል በእራሱ የሚሄድ ብስክሌት፣ ያልጠፉ የቤት መገልገያ ዕቃዎችን የሚያጠፋ እና የእሳት አደጋን የሚጠቁም መሣሪዎች ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።

የኢዘዲን የፈጠራ ሥራዎቹ በአጠቃላይ 27 ሲሆኑ ከአስደናቂዎቹ ናሙናዎች (ፕሮቶታይፖች) መካከል የተወሰኑት ከዚህ በታች ባለው ምስል ይታያሉ።

ኢዘድን እና የተለያዩት ፈጠራዎቹ

የፎቶው ባለመብት, Ezedin Kamil

ሌባ ያደገበትን ቤት ሲያንኳኳ ...

ሰው ችግሩን ለመቅረፍ በማሰብ ነው ወደ ፈጠራ የሚሰማራው የሚለው ኢዘዲን አንድ ቀን የእጅ ስልኩን ቻርጅ እንዲያደርግ ቤቱ ትቶት ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ ሲመለስ የጠበቀው ክስተት በጄሪካን ለሠራው ፈጠራ ጅማሬ መሆኑን ያስታውሳል።

"ስመለስ የጎረቤታችን ቤት በእሳት ጋይቶ ጠበቀኝ። መጀመሪያ ላይ ድንጋጤው እንድነቃነቅ አላደረገኝም ነበር። ከዚያ ግን ሰው ሁሉ ሲሯሯጥ እኔም እሳቱን ለማጥፋት ለማገዝ ሞከርኩ" የሚለው ኢዘዲን ቻርጀር ላይ ተሰክቶ የነበረው ስልኩን አስታውሶ ለእሳት አደጋው ደራሽ ቢሆን የሚል ሃሳብ እንደሆነው ይነግረናል።

ሃሳቡን ወደ ተግባር በመለወጥ ቤት ውስጥ የሚፈጠርን ጭስ በመለየት የእሳት አደጋ ምልክትን በአቅራቢያ ላሉ ሰዎች በድምፅ ይሰጣል። በዚህም በቅርብ ያሉ ሰዎች እርምጃ ካልወሰዱ በመሣሪያው ላይ በተገጠመ ስልክ አማካይነት መዝግቦ ለያዛቸው ሁለት ቁጥሮች ለምሳሌ ለቤቱ ባለቤት እና ለእሳት አደጋ መከላከያ በመደወል የእሳት አደጋ ጥሪ ያስተላልፋል።

የ Facebook ይዘትን ይለፉት

የሚፈልጉት ይዘት የለም

በ Facebook ተጨማሪ ይመልከቱቢቢሲ ከሌሎች ድረ-ገጾች ለሚመጡ መረጃዎች ሀላፊነት አይወስድም.

የ Facebook ይዘት መጨረሻ

'ኤክስ ፋየር' ብሎ የሰየመው ይህ ፈጠራው "የእሳት አደጋ ሲከሰት ሦስት የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናል። መጀመሪያ ላይ በአቅራቢያ ለሚገኙ ሰዎችና ጎረቤቶች የድረሱልኝ ጥሪ ያሰማል፣ ቀጥሎ ደግሞ የእሳት አደጋ መነሳቱን ለቤቱ ባለቤትና ለእሳት አደጋ ተከላካዮች በመደወል ያሳውቃል፤ ይህንን እያደርገ ካርቦን ዳይዮክሳይድ በመርጨት እሳቱን ለማጥፋት ጥረት ያደርጋል" ሲል የሚናገረው ኢዘደኒን ለዚህ ፈጠራው አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እውቅና እንደሰጠው ይጠቅሳል።

እንደዚህ ዓይነት የቤትን ደህንነት መጠበቂያ ቴክኖሎጂዎች በውድ ዋጋ የሚቀርቡ በመሆናቸው የቅንጦት መሣሪያዎች ሊመስሉ ይችላሉ የሚለው ኢዘደን፣ በእሳት የተቃጠለውን የጎረቤቶቹን ቤት በማሰብ እንደዚህ ዓይነት መሣሪያዎች በሰው ላይ የሚደርስ ጉዳትንና የንብረት ውድመትን ሊያስቀሩ እንደሚችሉ ይናገራል።

ከዚህ በተጨማሪም በአንድ ወቅት ሌባ ወደቤታቸው መግባቱን የሚያስታውሰው ኢዘዲን ሌባ ወደ ቤት ለመግባት ሲሞክር በድምጽ ምልክት የሚሰጥ መሣሪያም እንዳለው ይናገራል።

"ሌባው ጓንት ቢያደርግ መሣሪያው ለይቶ ሊያውቀው አይችልም፤ ይህ መሣሪያ ምልክት የሚሰጠው ሌባው በእጁ ከነካው ብቻ ነው" የሚለው ኢዘዲን ይህ ፈጠራው የሚቀረው ነገር እንዳለና ሌሎች የሚያሰባቸው ብዙ ዓይነት የፈጠራ ሥራዎች እንዳሉት ለቢቢሲ ገልጿል።

(ከላይ በግራ) ኢዘዲን ከአንደኛው ጣልያን ስፖንሰር ጋር (ከላይ በቀኝ) ኢዘዲንና አባቱ (ሌላው) ለኢዘዲን ከተሰጡት ሰርቲፊኬቶች መካከል የተወሰኑት

የፎቶው ባለመብት, Cheramlak Mengistu/Ezedin Kamil

የምስሉ መግለጫ, (ከላይ በግራ) ኢዘዲን ከአንደኛው ጣልያን ስፖንሰር ጋር (ከላይ በቀኝ) ኢዘዲንና አባቱ (ሌላው) ለኢዘዲን ከተሰጡት ሰርቲፊኬቶች መካከል የተወሰኑት

ኢዘዲን ካሚል ዛሬ እና ነገ

ኢዘዲን እስካሁን ለሠራቸው የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎቹ ብዙ የሚያመሰግናቸው ሰዎች ቢኖሩም፤ በቀዳሚነት የሚማርበትን ዩኒቨርሲቲ ጠቅሶ እንደልቡ የሚመራመርበትን ክፍል ከማዘጋጀት ባሻገር በተለያዩ ጊዜያት ለፈጠራ ሥራዎቹ ያስፈልጉኛል ብሎ የሚጠይቃቸውን መሣሪያዎች እና ቁሳቁሶች እንዲገዙለት ማድረጋቸውን ይጠቅሳል።

በተጨማሪም ከካቶሊክ ሚሽን ጋር የተያያዙ ድርጅቶችና ሁለት ጣልያናዊ ሙዚቀኞች ለሦስት ተከታታይ ዓመታት እንደረዱት እንዲሁም 34 ሺህ ብር፣ አርድዊኖ የተባለ ሶፍትዌር እና 2 ላፕቶፕ ኮምፕዩተሮችን አበርክተውለታል።

የተለያዩ ውድድሮች ላይ ከመሳተፍ ወደ ኋላ የማይለው ኢዘዲን በቅርቡ በተሳተፈበት ውድድር ላይ የ300 ሺህ ብር ተሸላሚ መሆኑንና 6 የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ሠርቶ እንዲያቀርብ መጠየቁን ገልጿል። በዚህም "በጣም ደስ ብሎኛል አሁን ስድስት ሥራዎቼን በትክክለኛ ዕቃዎች ሠርቼ ማቅረብ እችላለሁ" ይላል።

ከተለያዩ ድርጅቶች፣ ማዕከላትና ተቋማት ሰርትፍኬትና ሽልማት ያገኘው ኢዘዲን ከሁሉም በላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እውቅና ተስጥቶት መሸለሙ ወደፊት ለሃገሩ ብቻ ሳይሆን አህጉሪቱንም ተሻግሮ ለዓለም ብዙ ነገሮችን ሊያበረክት እንደሚችል ተስፋ እንዳለው ነግሮናል።

ከሁሉም በላይ የወጣትነት ሕልሙ ምን እንደሆነ ሲጠየቅ "አሁን የውጪ ትምህርት ዕድል አግኝቼ ብዙ ነገሮችን ደግሞ ወደፊት መሥራት ብችል ደስታዬን አልችለውም" በማለት ያለውን የወደፊት ዓላማ ለቢቢሲ ተናግሯል።