የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር መጀመሪያ ደረጃ ላይ ያለ ፕሮስቴት ካንሰር ሕክምና ተደረገላቸው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ካንሰር ሊያመጣ የሚችል እጢ እንደተወገደላቸው ዓመታዊ የሕክምና ሪፖርታቸው ማሳየቱን ተከትሎ "ጥሩ አካላዊ ጤንነት ላይ" እንደሚገኙ ተናገሩ።
ኔታንያሁ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ መደበኛ የሕክምና ክትትል በሚያደርጉበት ወቅት ሐኪሞች የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ያለ ወደ ካንሰር ሊቀየር የሚችል እጢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በወቅቱ ዶክተሮች ክትትል ሲያደርጉላቸው የነበረው ከዚያ አስቀድሞ ወደ ካንሰር የማይቀየር ፕሮስቴትን በተሳካ ቀዶ ጥገና ከሰውነታቸው ካስወገዱላቸው በኋላ መሆኑን አስረድተዋል።
ሕክምናው "ችግሩን አስወግዶታል፤ ምንም ምልክት አልተወም" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ባለበት ሁኔታ የሕክምና ሪፖርታቸው እንዳይወጣ ጠይቀው እንደነበር ገልጸዋል።
ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት ኢራን "እስራኤል ላይ የበለጠ ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ" እንዳታሰራጭ ለመከላከል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአውሮፓውያኑ 2024 ካንሰር ላልሆነ ፕሮስቴት የመጀመሪያ ደረጃ ቀዶ ሕክምና እንደተደረገላቸው የገለጹት የ76 ዓመቱ የእስራኤል መሪ፤ መደበኛ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መቆየታቸውን አክለዋል።
በቅርቡ በተደረገው ክትትል "ከአንድ ሴንቲሜትር የሚያንስ ትንሽ ነጥብ" መገኘቱንም አስታውቀዋል።
"ከፕሮስቴት ጋር የተያያዘ መጠነኛ የጤና ችግር አጋጥሞኝ የነበረ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ሕክምና ተደርጎለታል። ፈጣሪ ይመስገን፤ አልፏል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሰፈሩት ረጅም ጽሑፍ፤ ሕክምናውን ለማድረግ የወሰንኩት "ሊከሰት ስለሚችል አደጋ በሰዓቱ መረጃ ሲሰጠኝ፤ ወዲያውኑ ምላሽ መስጠት ስለምፈልግ ነው" ብለዋል።
የኔታንያሁ የጤና ሁኔታ ይፋ የሆነው ከሳምታት በኋላ በዋይት ሃውስ ጉብኝት ለማድረግ እየተዘጋጁ ባለበት እና አሜሪካም ከኢራን ጋር እየተደረገ ላለው ጦርነት ዘላቂ የሰላም ስምምነት ለመፈጸም እየጣረች ባለበት ወቅት ነው።
እስራኤል እና በኢራን ከሚደገፈው ሄዝቦላህ ጋር የገባችበትን ግጭት ለመግታት የተደረሰው የሊባኖስ ተኩስ አቁም ስምምነትም ለተጨማሪ ሦስት ሳምንታት ተራዝሟል።















