ቤንያሚን ኔታንያሁ ምህረት እንዲደረግላቸው ለእስራኤል ፕሬዚዳንት ጥያቄ አቀረቡ

ቤንያሚን ኔታንያሁ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ቤንያሚን ኔታንያሁ ይቅርታ በእስራኤል ብሔራዊ እርቅ እንዲወርድ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል

በሦስት የሙስና ድርጊቶች ክስ የተመሠረተባቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ምህረት እንዲያደርጉላቸው ጠየቁ።

ሄርዞግ ይህንን "ከፍተኛ አንድምታ ያለው" ጥያቄ ከማጤናቸው በፊት ከፍትህ አካላት አስተያየቶችን እንደሚቀበሉ የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ተናግሯል።

ኔታንያሁ ላለፉት 5 ዓመታት በሙስና፣ በማጭበርበር እና በሦስት የተለያዩ ክሶች እምነትን በመጣስ ክስ ቀርቦባቸው ነበር። ኔታንያሁ በቀረቡባቸውን ክሶች በሙሉ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን በመግለጽ ይከራከራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት የፍርድ ቤት ክስ ሂደቱን እስከ መጨረሻው ማየትን ይመርጡ የነበረ ቢሆንም፣ አገራዊ ፍላጎት ግን "ከዚህ በተቃራኒው የሚፈለግ ነው" ብለዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ይቅርታ ከመጠየቃቸው በፊት ጥፋተኝነታቸውን ማመን አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሄርዞግ ለኔታንያሁ ሙሉ በሙሉ ይቅርታ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

በወቅቱ ሄርዞግ ይቅርታ እንዲደረግለት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ጥያቄውን በመደበኛው ስርዓት መሠረት ማቅረብ እንዳለበት ተናግረዋል።

እሁድ ዕለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ኔታንያሁ "የዚህን ያልተለመደ ጥያቄ አስፈላጊነት እና አንድምታው" ግምት ውስጥ በማስገባት በማለት ለፕሬዚዳንቱ የፃፉትን የይቅርታ ደብዳቤ ይፋ አድርጓል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፕሬዚዳንቱ መቼ ውሳኔ ላይ እንደሚደርሱ የሚጠቁም ነገር የለም።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ 2020 ቤንያሚን ኔታንያሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ችሎት ፊት የቀረቡ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የቀረበው የመጀመሪያው የክስ መዝገብ ውለታ እንዲዋልላቸው ከሚፈልጉ ከፍተኛ ባለሃብቶች ስጦታዎችን፣ በዋናነት ሲጋራ እና ሻምፓኝ መቀበላቸውን ተጠቅሷል።

በሁለተኛው ክስ ደግሞ የአንድ የእስራኤል ጋዜጣን ስርጭት ለማሻሻል በምላሹ አዎንታዊ ሽፋን ለማግኘት ቃል ገብተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በሦስተኛ ክስ አቃቤ ሕግ በአንድ የዜና ድረ ገጽ አዎንታዊ ሽፋን ለማግኘት በሚል ለአንድ የእስራኤል የቴሌኮም ኩባንያ ተቆጣጣሪ ባለአክሲዮን የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል ይላል።

ኔታንያሁ ሁሉንም ክሶች ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት የተከራከሩ ሲሆን ችሎቱን የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸው "የሌለን ነገር ለመፈለግ" የመሠረቱት ሲሉ ፈርጀውታል።

እሁድ ዕለት ባስተላለፉት ቪዲዮ መልዕክት፣ የቀረቡባቸው ክሶች ውሃ እየቋጠሩ አይደለም ነገር ግን ሂደቱ እስራኤልን ከውስጥ እየከፋፈላት ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም "የፍርድ ሂደቱ በአስቸኳይ መቋረጥ የተፈጠረውን ውጥረት በመቀነስ አገራችን በጣም የምትፈልገውን እርቅን በሰፊው ለማምጣት ትልቅ እገዛ ይኖረዋል" ብለዋል።

ኔታንያሁ በሳምንት ሦስት ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው መመስከር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረው ይህንንም "የማይቻል ጥያቄ" ሲሉ ገልፀውታል።

ይቅርታው እስራኤል "አገራዊ አንድነትን" በማጎልበት ዕድሎችን እንድትጠቀም እንደሚረዳት ገልፀዋል።

የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ኔታንያሁ ፍላጎታቸውን ከአገሪቱ ጋር ለማጣመር ሞክረዋል ሲሉ ከስሰዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ያየር ላፒድ ጥፋተኛ መሆናቸውን ካላመኑ፣ መፀፀታቸውን የሚገልጽ ምንም ነገር በሌለበት እንዲሁም ኔታንያሁ ከፖለቲካዊ ሕይወት ራሳቸውን እስካላገለሉ ድረስ ይቅርታ ማድረግ አይቻልም ብለዋል።

የግራ ክንፍ ፖለቲከኛ እና የቀድሞ የእስራኤል ጦር ምክትል አዛዥ ያየር ጎላን "ጥፋተኞች ብቻ" ይቅርታ ይጠይቃሉ ብለዋል።

በእስራኤል መደበኛ ሕግ መሠረት ፕሬዚዳንቱ "ወንጀለኞችን ይቅር የማለት እና ቅጣቱን የመቀነስ ወይም የመቀየር" ሥልጣን አላቸው።

ነገር ግን የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቱ የሕዝብ ፍላጎት ካለ አንድ ግለሰብ ጥፋተኛ ሆኖ ከመገኘቱ በፊት ወይም እጅጉን ከግል ጉዳይ ጋር የሚያያዝ ሁኔታ ካለ ይቅርታ ማድረግ ይችላሉ ሲል ወስኗል።

የኔታንያሁ ቀኝ ክንፍ ሊኩድ ፓርቲ እና ደጋፊዎቻቸው ለመሪያቸው ይቅርታ እንዲደረግላቸው ይፈልጋሉ።