የእስራኤል ጦር የቀድሞ የሕግ አማካሪ ሾልኮ ከወጣ የፍልስጤማውያን እስረኞች ቪዲዮ ጋር በተያያዘ ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, IDF
የእስራኤል ጦር የቀድሞ ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ሾልኮ ከወጣ እና አስከፊ ስቅይት የተፈፀመባቸውን ፍልስጤማውያን እስረኞችን ከሚያሳይ ቪዲዮ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ፖለቲካዊ ውጥረትን ተከትሎ ታሰሩ።
ሜጀር ጄነራል ይፋት ቶመር ይሩሻልሚ " ሾልኮ ለወጣው ቪዲዮ ሙሉ ኃላፊነት እወስዳለሁ" ሲሉ የሕግ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው ያገለግሉበት ከነበረው የእስራኤል መከላከያ ኃይል የለቀቁት ባለፈው ሳምንት ነበር።
ከሥራ መልቀቃቸውን ተከትሎም መከላከያ ሚኒስትሩ ካትዝ ድርጊታቸውን አውግዘዋል።
" የእስራኤልን መከላከያ ኃይል ወታደሮችን የሚያጠለሽ ማንኛውም ሰው የጦሩን የደንብ ልብስ ለመልበስ ብቁ አይደለም" ብለዋል ካትዝ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁም እሁድ እለት " የይሩሻልሚ ጉዳይ እስራኤል ከተመሰረተችበት ጊዜ ወዲህ የተፈፀመ የሕዝብ ግንኙነት አስከፊ ጥቃት ነው" ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩን ሃሳብ አስተጋብተዋል።
ይህን ካሉ ከሰዓታት በኋላም ነው ጀነራል ቶመር ይሩሻልሚ መጥፋታቸው በእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የተነገረው።ይህም ወደ ሌላ አሳዛኝ ክስተት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሮ ነበር።
በስፋት ፍለጋ የተጀመረ ሲሆን ከበርካታ ሰዓታት በኋላ በባሕር ዳርቻዋ ሄርዝሊያ "በሰላም እና በጥሩ ጤንነት" መገኘታቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
ምሽቱንም የፖሊስ ቃል አባይ ቪዲዮው ሾልኮ ከመውጣቱ ጋር በተያያዘ እና በሌሎች የወንጀል ድርጊቶች የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል።
ሁለቱ ግለሰቦች ጄነራል ቶመር ይሩሻልሚ እና የቀድሞ የጦር አዛዥ ጠበቃ ኮሎኔል ማታን ሶሎሞሽ መሆናቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
እሑድ ዕለት ይሩሻልሚ መጥፋታቸው መነገሩን ተከትሎ ሁኔታዎች መልካቸውን ለውጠው የነበረ ሲሆን ፖሊስ በሰሜን ቴልአቪቭ የባሕር ዳርቻ ለሰዓታት ፍለጋ አካሂዷል።
ከዚያ በኋላ የቀድሞ ከፍተኛ የሕግ አማካሪዋ በሕይወት መገኘታቸውን እና ወደ እስር ቤት መመወሰዳቸውን ፖሊስ ገልጿል።
በእስራኤል የዜና ቻናል ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የተላለፈው ቪዲዮው በደቡብ እስራኤል በስድ ቴማን የጦር ሰፈር የሚገኙ ተጠባባቂ ወታደሮች አንድን እስረኛ ወደ ጎን ሲወስዱ የሚያሳይ ሲሆን ሲደበደብ እና በስለት ሲወጋ እንዳይታይ የፖሊስ ጋሻዎች ሲከልሉት ያሳያል።
እስረኛው የከፋ ጉዳት አጋጥሞት ሕክምና ሲደረግለት ነበር።
አምስት ተጠባባቂ ወታደሮችም በእስረኛው ላይ ጥቃት በመፈፀም እና ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ ክስ ቀርቦባቸዋል። እነርሱ ግን ክሱን ውድቅ ያደረጉ ሲሆን ስማቸውም አልተጠቀሰም።
እሁድ እለትም ከአምስቱ መካከል አራቱ ፊታቸው እንዳይታይ ከልለው ከጠበቃዎቻው ጋር በእየሩሳሌም ከሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውጭ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝተዋል። ጠበቃዎቻቸውም ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
የቀኝ ክንፍ የእርዳታ ድርጅት ሆነው የሚሰሩት ጠበቃ አዲ ኬድር ደንበኛቸው "በሐሰተኛ ፣ አድሏዊ በሆነና ሙሉ በሙሉ ለተቀነባበረ የሕግ ሂደት" እንደተዳረጉ ገልጸዋል።
የቀድሞዋ ከፍተኛ የሕግ አማካሪዋ ጉዳይ በእስራኤል ልዩነትን ፈጥሯል።
በአንድ በኩል ቪዲዮው መውጣት የእስራኤልን ጦር ስም ማጥፋት ነው በሚል የተወገዘ ሲሆን የአገር ክህደት የሚደርስ ወንጀል ሆኖ ተቆጥሯል።
በሌላ በኩል ደግሞ የጄነራል ቶምር ይሩሻልሚ ቪዲዮው እንዲለቀቅ የወሰኑት ውሳኔ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን የሚያሳይ እንደሆነ ታይቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ቪድዮው፤ ከመስከረም 2016 ቱ የሐማስ ጥቃት ወዲህ ፍልስጤማውያን እስረኞች ላይ በደል እየደረሰ መሆኑን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ለወጡ ዘገባዎች ጠንካራ ማስረጃ ሆኖ ታይቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ኮሚሽን ባለፈው ዓመት ባወጣው ሪፖርት ከጋዛ የተወሰዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት እና አዋቂ እስረኞች "ለሰፊ እና ስልታዊ በደል፣ አካላዊ እና አእምሯዊ ጥቃት፣ እንዲሁም ወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃት" መጋለጣቸውን ይፋ አድርጎ ነበር።
የተፈጸሙት ድርጊቶች "በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል የሆነ ስቅይት፣ የጦር ወንጀል የሆነ መድፈር እንዲሁም ሌሎች የወሲባዊ ጥቃት ዓይነት" እንደሆኑም ገልጿል።
የእስራኤል መንግሥት የቀረቡበትን ወንጀላዎች ውድቅ አድርጓል። "በዓለም አቀፍ የሕግ ስታንዳርድ" ለመመራት ያለውን "ሙሉ ቁርጠኝትም" በአጽንኦት አንስቷል። በእያንዳንዱ አቤቱታ ላይም ጥብቅ ምርመራ እንደሚያኬድ አስታውቋል።















