እስራኤል ድንበሮችን እስከምትከፍት እየተጠባበቁ የሚሞቱት የጋዛ ሕጻናት

ጋዛ ውስጥ የበርካታ ሰዎች ሕይወት እንጥልጥል ላይ ነው።
በጋዛ በሚገኘው ናስር ሆስፒታል የተለያዩ ዋርዶች ውስጥ ሁለት የ10 ዓመት ሕጻናት ተኝተዋል። አንዱ በእስራኤል ጥይት ተመትቶ፤ ከአንገቱ በታች ያለው የሰውነት ክፍሉ የማይታዘዝ ሆኗል። አንዱ ደግሙ የጭንቅላት እጢ አለበት።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ለተሻለ ሕክምና በአስቸኳይ ከጋዛ መውጣት ያለባቸው 15 ሺህ ታማሚዎች አሉ።

እናት ኦላ አቡ ሰይድ በእስራኤል ጥቃት የተጎዳው ልጇን አማር ጸጉር በስሱ እየዳሰሰች ተቀምጣለች።
የ10 ዓመቱ ሕጻን በተተኮሰ ጥይት እና እና በእስራኤል ድሮን የተመታው በደቡባዊ ጋዛ በሚገኝ ድንኳን ውስጥ ተቀምጦ በነበረበት ሰዓት መሆኑን ቤተሰቦቹ ይናገራሉ። ታዳጊውን የመታው ጥይት በአክራከሪ አጥንቱ መካከል በመቀርቀሩ ፓራላይዝ አድርጎታል።
"አስቸኳይ ቀዶ ሕክምና ያስፈልገዋል" ስትል እናቱ ኦላ ትናገራለች። "ግን ውስብስብ ነው። [ጉዳቱ] ለሞት፣ ስትሮክ ወይም አንጎል ውስጥ ለሚከሰት መድማት ሊዳርገው እንደሚችል ሐኪሞች ነግረውናል። በደንብ የተሟላ [የሕክምና መሣሪያ] ባለበት ቦታ ሕክምና ያስገልገዋል" በማለት ስጋቷን ታስረዳለች።
በአሁኑ ሰዓት ጋዛ እንዲህ አይነት ታሪኮች ብቻ የሚሰሙባት ቦታ ሆናለች። የሁለቱ ዓመቱ ጦርነት ሆስፒታሎቿ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደገኙ አድርጓቸዋል።

ከታናሽ ወንድሟ አህመድ አል ጃድ አጠገብ አልጋ ላይ ቁጭ ያለችው እህቱ ሻህድ የሌላኛውን ታዳጊ እናት ስጋት ትጋራለች። በሁለቱ ዓመቱ ጦርነት እና መፈናቀል ወቅት መጽናናትን ታገኝ የነበረው በወንድሟ እንደነበር ታስታውሳለች።
"ገና 10 ዓመቱ ነው። የነበርንበት ሁኔታ በጣም በከፋበት ወቅት ወጥቶ ውሃ እየሸጠ ገንዘብ በማምጣት ይረዳን ነበር" ትላለች።
አህመድ ሕመም እንደያዘው የሚጠቁሙ ምልክቶችን ማሳየት የጀመረው ከጥቂት ወራት በፊት ነበር።
"የአህመድ አፍ ወደ አንድ ጎን መዝመም ጀመረ" በማለት የመጀመሪያውን ምልክት ታስታውሳለች። "አንድ ጊዜ 'ሻህድ ጭንቅላቴን ያመኛል' እያለ ይነግረኝ ነበር፤ እኛ ፓራሲታሞል ነበር የሰጠነው። በኋላ ግን ቀኝ እጁ መንቀሳቀስ አቆመ" ስትል ጉዳቱን ትገልጻለች።
በአንድ ወቅት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረችው ሻህድ ወንድሟ ወደ ሌላ አገር ተጎዞ ያለበት የጭንቅላት እጢ እንዲወገድለት እጅጉን ትሻለች።
"ልናጣው አንችልም። አሁንም ቢሆን አባታችን፣ ቤታችን እና ህልማችን አጥተናል" ሻህድ ትናገራለች። "የተኩስ አቁም ሲደረግ ምናልባት አህመድ ወደ ውጭ ተጉዞ ህክምና የማግኘት አንድ ፐርሰንት ዕድል አለው የሚል ትንሽ ተስፋ ሰጠን" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዓለም የጤና ድርጅት፤ በቅጡ ያልጸናው የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ረቡዕ ዕለት የመጀመሪያው ዙር ሕክምና ተሽከርካሪዎች ከጋዛ እንዲወጡ አመቻችቷል።
41 ታካሚዎች እና 145 ተንከባካቢዎችን የጫኑት ተሽከርካሪዎች በእስራኤል ከረም ሻሎም መተላለፊያ በኩል ተጉዘዋል። ከዚያ በኋላ ደግሞ በአምቡላንሶች እና ባሶች ተጭነው ወደ ዮርዳኖስ ይወሰዳሉ።
የተባበሩት መንግሥታቱ ተቋም በጋዛ ለሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ታማሚዎች እና የቆሰሉ ሰዎች ለመድረስ ሲባል ታካሚዎችን ለማስወጣት የሚደረገው ጉዞ ቁጥር እንዲጨምር ጥሪ አቅርቧል። ከዚህ ቀደም ሲያደርግ እንደነበረው ታካሚዎችን በጋዛው ራፋህ በኩል ወደ ግብፅ ማሻገር ይፈልጋል።
እስራኤል ግን ሐማስ ሕይወታቸው ያለፈ ታጋቾች አስከሬንን በመመለስ በተኩስ አቁሙ የተጣለበትን ግዴታ "እስኪያሟላ" ድረስ ድንበሩን እንደዘጋች እንደምትቆይ አስታውቃለች።
እስራኤል በጋዛ በኩል የሚገኘውን የግብፅ ድንበር የዘጋችው ግንቦት 2024 አካቢውን ከተቆጣጠረች በኋላ ነበር።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ሐሙስ ዕለት በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባደረጉት ንግግር "እጅጉን ተጽዕኖ የሚኖረው እርምጃ" ያሉትን አማራጭ አቅርበዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ፤ ከዚህ ቀደም ይደረግ እንደነበረው የጋዛ ታካሚዎች ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ጨምሮ በወረራ ወደተያዘው ዌስት ባንክ ተወስደው እንዲታከሙ እስራኤል እንድትፈቅድ ጠይቀዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ከ20 በላይ የሚሆኑ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከዚህ ቀደም ይህንኑ ጥሪ አቅርበው ነበር። "የገንዘብ መዋጮ፣ የጤና ባለሙያዎች ወይም አስፈላጊ መሣሪያዎችን ለማቅረብም" ቃል ገብተዋል።

"ወደ ኢስት ጀሩሳሌም ሆስፒታል ኔትዎርክ እና ዌስት ባንክ የሚገኙ ሆስፒታሎች የሚወስደው መንገድ እንደገና ከተከፈተ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታካሚዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በቀላሉ እና በብቃት ሊታከሙ ይችላሉ" ሲሉ የኦጉስታ ቪክቶሪያ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ፋዲ አትራሽ ይናገራሉ።
በምሥራቅ ኢየሩሳሌም የሚገኘውን ሆስፒታል የሚመሩት ዶ/ር ፋዲ፤ "በቀን ውስጥ ቢያንስ ለ50 እና ከዚያ በላይ ታካሚዎች የኬሞቴራፒ እና የጨረር ሕክምና መስጠት እንችላለን። ሌሎች ሆስፒታሎችም ብዙ ቀዶ ሕክምናዎችን ማከናወን ይችላሉ" ይላሉ።
"አሁንም ቢሆን አሠራሩ ስላለን፤ ወደ ምሥራቅ ኢየሩሳሌም ማዛወር የሚወስደው በጣም አጭር ርቀት ነው፣ እጅጉን ቀልጣፋ የሆነውም መንገድ ነው። አንድ ዓይነት ቋንቋ እንናገራለን፣ አንድ ዓይነት ባህል አለን። በብዙ ኬዞች ላይም የጋዛ ሕመምተኞች የሕክምና ፋይሎች አሉን። ከጦርነቱ በፊት ከአሥር ዓመት በላይ በምሥራቅ ኢየሩሳሌም ሆስፒታሎች ውስጥ ሕክምና ሲደረግላቸው ቆይተዋል" ሲሉ ምክንያታቸውን ያብራራሉ።
ቢቢሲ፤ የሕክምና መንገዱ ለምን አልተፈቀደም ሲል የጋዛን መተላለፊያዎች ለሚቆጣጠረውን የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት አካል ጥያቄ አቅርቧል።
ተቆጣጣሪው አካል ይህ ውሳኔ የሚተላለፈው በፖለቲካዊ አመራሮች መሆኑን በመግለጽ ጥያቄዎቹን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተላልፏል። ጽሕፈት ቤቱ በበኩሉ እስካሁን ድረስ ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጠም።
እስራኤል፤ የጋዛ ታካሚዎች በሌሎች የፍልስጤም ግዛቶች እንዲታከሙ ማድረግን በተመለከተ የምታነሳው ሐማስ በመስከረም 2016 ዓ.ም. ከፈጸመው ጥቃት ጋር የተያያዘ የደኅንነት ስጋትን ነው። ለጋዛ ነዋሪዎች ዋነኛ መተላለፊያ የሆነው ኤሬዝ በጥቃቱ ወቅት የሐማስ ተዋጊዎች ዒላማ እንደነበርም ትገልጻለች።
የጋዛ ጤና ሚኒስትር እንደሚገልጸው እስከ ነሐሴ 2017 ድረስ ባለው አንድ ዓመት ውስጥ 140 ሕጻናትን ጨምሮ በተጠባባቂ ዝርዝር ላይ የነበሩ 740 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
በአል ናስር ሆስፒታል የሕጻናት እና የእናቶች ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አህመድ አል ፋራ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ዶ/ር አል ፋራ፤ "አንድ ሐኪም አንድን በሽታ ለመየት ችሎ ነገር ግን አስፈላጊ ምርመራዎችን ማከናወን እና አስፈላጊውን ሕክምና ሳይችል ሲቀር ያለው ስሜት በጣም ነው" ይላሉ።
ይህ ሁኔታ በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥም የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ "በሚያሳዝን ሁኔታ ባለብት የአቅም ውስንንት ምክንያት በየዕለቱ ሕይወት ይጠፋል" በማለት ያስረዳሉ።
ምንም እንኳ የተኩስ አቁሙ ስምምነት ላይ ቢደረስም ታካሚዎች ተስፋቸው እየተሟጠጠ መሆን ዶ/ር አል ፋራ ይናገራሉ።
ባለፈው ሳምንት የአንጀት ካንሰር ይዞት የነበረው የስምንት ዓመቱ ሳዲ አቡ ታሃ ቀበር በሆስፒታሉ ቅጥር ውስጥ ተከናውኗል።
ከአንድ ቀን በኋላ ደግሞ የሦስት ዓመቱ ዛይን ታፌሽ እና የስምንት ዓመቱ ሉዬ ዱዌክ በሄፓታይተስ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።
ታማሚዎች የተሻለ ሕክምና የሚያገኙበት እርምጃ ካልተወሰደ በርካታ የጋዛ ነዋሪዎች በሰላም የመኖር ዕድልን የሚያገኙ አይመስልም።















