ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ያየሰው ሽመልስ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Facebook/Tariku Desalegn
የፍትህ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ኢትዮ-ፎረም በተባለ የዩቲዩብ ሚዲያ ላይ ይሰራ የነበረው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው መወሰዳቸውን ቢቢሲ ከባልደረቦቻቸውና ከጠበቃቸው አረጋገጠ።
ተመስገን ዛሬ ረፋድ ሐሙስ ግንቦት 18/2014 ዓ.ም. ከስራ ቦታው በሁለት መኪና ተጭነው በመጡ ኃይሎች ተይዞ መወሰዱንም ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ባልደረቦቹ ተናግረዋል።
ተመስገንን ይዘውት የሄዱት ኃይሎች መሳሪያ የታጠቁ ይሁኑ እንጂ የሲቪል ልብስ የለበሱ መሆናቸውንም አክለዋል።
በተመሳሳይ ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ የካ አባዶ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ከአዲስ አበባ ፖሊስ መምጣታቸውን በተናገሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠበቃው አቶ ታደለ ገ/መድኅን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ታደለ እንዳሉት ያየሰው ላለፉት ሁለት ዓመታት ትምህርት ላይ ማሳለፉን አስታውሰው፤ በአሁኑ ሰዓት በጋዜጠኝነት ሥራ ላይ አይገኝም ብለዋል። በአሁኑ ሰዓት
በጋዜጠኝነት ሥራ ላይ አይገኝም ያሉ ሲሆን፤ በተያዘበት ወቅት ለመያዙ ምንም አይነት ምክንያት እንዳልተሰጠው አስረድተዋል።
ያየሰው በአሁኑ ወቅት ሶስተኛ ተብሎ በሚጠራው ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኝ እና ደንበኛቸው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት ይቀርባል ብለው እንደሚጠብቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተመስገንን ደሳለኝን እና ያየሰው ሽመልስን ሳይጨምር ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ቁጥራቸው ከአስር በላይ የሚሆኑ በተለያዩ የመገናኛ መድረኮች ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች በፀጥታ ኃይሎች መያዛቸው ተዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Tariku Desalegn facebook
ከቀናት በፊት ተመስገን በጸጥታ ኃይሎች ተይዟል የሚል መረጃ መሰራጨቱን ተከትሎ ቢቢሲ ለጋዜጠኛው ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
ጋዜጠኛው በቁጥጥር ስር እንደሚውል መረጃው እንዳለው ገልጾ ነበር።
''እስከዛሬ ለዘገባዎቼ የመረጃ ምንጮቼ የነበሩት የደኅንነት አመራሮች በቁጥጥር ስር ልውል እንደምችል ነግረውኛል'' ሲል ገልጾ ነበር።
ለእስር ሊዳርገው የሚችል ነገር ይኖር ይሆን ወይ? ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄም ''መንግሥት ሙሉ በሙሉ ወደ ወጥ አምባገነንነት እየተቀየረ ስለሆነ ገበናውን ሊያጋልጡ የሚችሉ ሚዲያዎችን ወደ ማፈን ነው የሄደው። ይህ በ1970 ዓ.ም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም የዚያድ ባሬን ወረራ ከደመሰሱ በኋላ ወደ ተቃዋሚዎቻቸው ነበር የዞሩት። ኮሎኔል ዐብይም ይህንን ነው እያደረጉ ያሉት'' ሲል ተመስገን ተናግሮ ነበር።
በጋዜጠኛው እስር ላይ የአዲስ አበባም ሆነ የፌደራል ፖሊስ የሰጠው አስተያየት የለም።
ቢቢሲ የጋዜጠኛውን መታሰር አስመልክቶ የአዲስ አበባን ፖሊስ ለመጠየቅ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
ይሁን እንጂ የአዲስ አበባና የፌደራል ፖሊስ ጽህፈት ቤቶች ተወካዮች ሐሙስ ግንቦት 18/2014 ዓ.ም. ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት በከተማዋ ባለፉት ሳምንታት ከ340 በላይ ግለሰቦች በሽብር እና በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።
ተመስገን በጋዜጣና በመፅሔት ባለቤትነትና ዋና አዘጋጅነት በቆየባቸው ጊዜያት መንግሥትን በሚተቹ ጽሁፎቹ ይታወቃል።
በተደጋጋሚ ጊዜያት የህትመት ሥራዎቹ እንዲቋረጡ ከመደረጉ በተጨማሪ ለእስርም መዳረጉ ይታወሳል።
በተመሳሳይ ያየሰው ሽመልስም ባለፈው ዓመት ለወራት በእስር ላይ ቆይቶ ተፈትቷል።
ከሰሞኑ ከተመስገን እና ከያየሰው ሽመልስ በተጨማሪ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ከግንቦት 11/2014 ዓ.ም. ጀምሮ ቢያንስ 11 ጋዜጠኞችና የሚዲያ ሠራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን የሆኑት የአሻራ አምስት ጋዜጠኞች፣ አራት የቻናል ንስር ኢንተርናሽናል ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ኢትዮ ንቃት የተሰኘው ሚዲያ መስራች እና ዋና አዘጋጅ መስከረም አበራ እንዲሁም የገበያኑ ሚዲያ መስራችና እና ባለቤት አቶ ሰለሞን ሹምዬ ናቸው።
በተለያዩ ክልሎች እየተካሄደ ካለው የህግ ማስከበር ዘመቻን ተከትሎ ለእስር የተዳረጉት ጋዜጠኞች በአፋጣኝ እንዲፈቱ ዓለም አቀፎቹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲፒጄ እንዲሁም ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት አርኤስኤፍ ጠይቀዋል።
በተጨማሪ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከሰሞኑ ጋዜጠኞች እና ማኅብረሰብ አንቂዎች በጅምላ እየታሰሩ መሆኑ አንዳሰሰበው አስታውቋል።
ኤምባሲው የጅምላ እስሮቹን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባቀረበው ምክረ ሃሳብ መሠረት የፌደራል እና የክልል ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ሕጋዊ አሰራሮችን መከተል አለባቸው ብሏል።
ኢሰመኮ በበኩሉ ግንቦት 14/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ የጋዜጠኞችና ማኅበረሰብ አንቂዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለእስር እየተዳረጉ መሆኑን ኮንኖ ነበር።















