የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ለታይም መጽሔት የቅሬታ ደብዳቤ ላከ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጽ/ቤት ለታይም መጽሔት የቅሬታ ደብዳቤ ላከ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ለታይም መጽሔት የቅሬታ ደብዳቤ የላኩት እውቁ መጽሔት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን የ2022 የዓመቱ 100 ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ካካተተ በኋላ ነው።
ታይም መጽሔት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ዝርዝር ሲያካትታቸው፤ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ሰላም ማውረዳቸውን ተከትሎ የኖቤል ሽልማት መቀበላቸውን አስታውሶ፣ በትግራዩ ጦርነት የተሳተፉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ ሆነዋል ይላል።
በዝርዝሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የገለጸችው የታይም ወኪል አሪያን ቤከር፤ "የዐቢይ ኃይሎች በጅምላ ግድያዎች፣ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና የዘር ማጽዳት ክስ ቀርቦባቸዋል። ሚሊዮኖችን የሚያሰጋ ረሃብ ተከስቷል" ብላለች።
ይህ ተከትሎ ቢልለኔ ስዩም ለታይም መጽሔት በጻፉት ኢሜይል ላይ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈው "ሆን ተብሎ ስም ለማጥፋት" በታሰበ መንገድ ነው ብለዋል።
ጨምሮም ይህ ድርጊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ግላዊ ማንነት ላይ ያነጣጣረ ከፍ ያለ ጥቃት ከመሆኑ በተጨማሪ ስለጦርነቱ በአንደኛው ወገን ብቻ የሚነገረውን ትርክት የሚያስተጋባ ነው በማለት መጽሔቱ ስለ ምን "ሃቁን በመተው የራሱን ትርክት በመላው ዓለም ማሰራጨት" እንደፈለገ ማብራሪያ እንዲሰጥ ቢልለኔ ጠይቀዋል።
የታይም መጽሔት የአፍሪካ ቢሮ ኃላፊ የሆነችው ቤከር ስለ ጠቅላይ ሚንስትሩ በጻፈችው ጽሑፍ ላይ ከጥቂት ወራት በፊት በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ሲባል የፌደራሉ መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጉን አስታውሳ፤ ይህ የተኩስ አቁም አዋጅ በአመዛኙ ስትራቴጂካዊ ከመሆኑ ባሻገር የደረሰው የእርዳታ መጠን አነስተኛ ነው ብላለች።
የትግራይ ኃይሎች የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት ከ19 ወራት በላይ አስቆጥሯል።
በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ውንጀላ ይቀርብበባቸዋል። በሌላ በኩል የፌደራሉ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ ክልል እንዳይደርሱ አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ታይም ተጽዕኖ ፈጣሪዎቹን እንዴት ይመርጣል?
ታይም የዓመቱ 100 ተዕእኖ ፈጣሪ ሰዎችን ለመመርጥ "ስንሰባሰብ አንድ መለኪያ ላይ ትኩረት እናደርጋለን" ይላል። ይህም ተጽእኖ ነው። "ማን ልዩነት ፈጠረ? ማን ጎልቶ ታይ፤ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ" ይላል መጽሔቱ የተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን ዝርዝር እንዴት እንደሚመርጥ ሲያትት።
ታይም በዘንድሮ የተጽዕኖ ፈጣሪ ዝርዝር ውስጥ በሁለት ጫፍ የተሰለፉትን የሩሲያውን ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እና የዩክሬኑን ፕሬዝደንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪን በዝርዝሩ ውስጥ ማካተቱን ይገልጻል።
"ከአስከፊ ጦርነት ጀርባ ያሉት የሩሲያው መሪ እና ወረራውን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ ያሉት ባላንጣቸው የዩክሬኑ ፕሬዝደንት" በዚህ ዝርዝር ውስጥ በአንድ ዘረፍ መካተታቸው ሁሉም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አዎንታዊ አለመሆናቸውን ይገልጻል ይላል መጽሔቱ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትምኒት ገብሩ
የ2022 የዓመቱ 100 ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱ ሌሎች ግለሰቦች መካከል የኮምፒውተር ሳይንቲስት የሆነቸው ትምኒት ገብሩ (ዶ/ር) ትገኝበታለች።
በታይም መጽሔት ላይ ስለ ትምኒት ሥራዎች ማብራሪያ የጻፈችው የዩሲኤልኤ ሴንተር ፎር ክሪቲካል ኢንተርኔት ኢንኳየሪ ዳይፌክተር ሳፊያ ኖብል "እንደ ጉግል ያሉ ግዙፍ ተቋሞችን መጋፈጥ ጥንካሬ ይጠይቃል" ስትል ገልጻታለች።
በጉግል የሰው ሠራሽ ልህቀት ሥነ ምግባር ክፍል ትሠራ የነበረችው ጉግል የተቋሙን ዘረኛ አሠራር በማጋለጥ ትታወቃለች። ተቋሙን በአደባባይ በመተቸቷም ከሥራዋ መባረሯ አይዘነጋም።
"ትምኒት ጉግል ውስጥ የኤአይን ሥነ ምግባር በሚቆጣጠር ዘርፍ መሪ በመሆን የምትታወቅ ጥቁር፣ ሴት ባለሙያ ነበረች። ቴክኖሎጂን የተሻለ ለማድረግ ስህተቶችን ነቅሳ እንድታወጣ ብትቀጠርም በሥራዋ መድልዎን በማጋለጧ ተባራለች" ስትል ሳፊያ በመጽሔቱ ጽፋለች።
ትምኒት ከጉግል ከመባረሯ በፊት ከሙያ ባልደረባዋ ጋር የሠራችው ጥናት በጉግል ውስጥ ያለውን የዘር መድልዎ እና ኤአይ በአካባቢ ላይ ያለውን ተጽዕኖ አጋልጧል።
በዚህ ጥናት ምክንያት ከጉግል ብትባረርም፣ የጥናቱ ግኝት በቴክኖሎጂው ዘርፍ ባለሙያዎች ዘንድ ተደንቋል፣ መነጋገሪያም ሆኗል።
ሳፊያ ለታይም በጻፈችው ላይ "የአርቴፍሻል ኢንተለጀንስን ክፍተት የምታሳየን የዘርፉ ቁንጮ ናት" ስትል ባለሙያዋን ገልጻታለች።
የሰውን ምሥል ወይም ተንቀሳቃሽ ምሥል በማየት ማንነታቸውን የሚለየው (ፌሻል ሪኮግኒሽን) በተመለከተ ትምኒት የሠራችው ጥናት፣ መሣሪያው በተለይም ጥቁርና ቡናማ ሴቶችን መለየት እንደማይችል በማሳየት መድልዎውን አጋልጧል።
"ሥራዋ በቴክኖሎጂ ውስጥ ያለውን የዘር መድልዎ ያሳያል። ይህም ሠራተኞች ላይ ከሚደርሰው ብዝበዛ እስከ አግላይ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይደርሳል" ስትል ሳፊያ አክላለች።












