የዝንጀሮ ፈንጣጣ ለኢትዮጵያ ምን ያህል ስጋት ነው?

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library

የምስሉ መግለጫ, የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ

በአሁኑ ጊዜ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወይም ሞንኪፖክስ ቢያንስ በ13 አገራት ከ90 በላይ ሰዎች ላይ መከሰቱ የዓለም ጤና ድርጅት አረጋግጧል።

በሽታው በስፋት የታየው በአሜሪካ እና በአውሮፓ አገራት ውስጥ ነው።

በንክኪ የሚተላለፈው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ከኮቪድ-19 ጋር ሲነጻጸር የመዛመት ፍጥነቱ ዝቅተኛ ቢሆንም፣ እንደ ዩናይትድ ኪንግድም ያሉ አገራት "ችላ የምንለው አይደለም" ብለው በልዩ ትኩረት እየሰሩ ነው።

ለመሆኑ ይህ በሽታ ኢትዮጵያን ያሳስባታል?

በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲቲዩት የበሽታዎች ቅኝት እና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ወሰን የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወይም ሞንኪፖክስ በኢትዮጵያ የመከሰት "ከፍተኛ ዕድል አለው ብለን እናስባለን" ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ዳይሬክተሩ የወርርሽኞች አቅም እና የመተላለፊያ መንገዶቻቸው የበሽታውን አሳሳቢነቱን እንደሚወስኑ ያብራራሉ።

"ብዙ አገራትን የሚያዳርሱ በሽታዎች ብዙ ጊዜ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው የሚዛመቱት በትንፋሽ የሚተላለፉት በሽታዎች ናቸው" የሚሉት አቶ መስፍን ቀጥሎ ያለውን ደረጃ የሚይዙት ደግሞ በንክኪ የሚተላለፉት መሆኑናቸውን ጠቁመዋል።

በንክኪ የሚተላለፉ በሽታዎች በፍጥነት የመዛመት ዕድላቸው ዝቅ ያለ ነው። "ያ ማለት ግን ከአገር ወደ አገር አይተላለፍም ማለት አይደለም።"

እዚህ ጋር የዝንጀሮ ፈንጣጣ በንክኪ እንደሚተላለፍ ልብ በሉ።

ዳይሬክተሩ በሽታው እስካሁን በኢትዮጵያ እንዳልተከሰተ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በታሪክም በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዘ ሰው ተመዝግቦ አያወቅም።

ሆኖም በሽታው ከተከሰተባቸው አገራት የሚነሳ ማንኛውም ሰው የዝንጀሮ ፈንጣጣን "በቀላሉ" ወደ ኢትዮጵያ ይዞት ሊመጣ እንደሚችል ነው አቶ መስፍን የሚናገሩት።

"የኢትዮጵያ ሁኔታ ከአፍሪካ አገሮች ወደ አውሮፓ እና ከአውሮፓ ወደ አፍሪካ አገራት ብዙ ትራንዚት እና ከፍተኛ የሰዎች ዝውውር ስላለ ከፍተኛ የመከሰት ዕድል አለው... ለሌሎችም አገራት ስጋት እስከሆነ ድረስ ለእኛም ስጋት መሆኑ አይቀርም፤ እኛም እየተንቀሳቀስን ያለነው ለአገራችንም ስጋት ነው ብለን ነው" ብለዋል።

አቶ መስፍን ይህ በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ አገራት በስፋት እየታየ ያለው በሽታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ "በተቻለ መጠን" አስፈላጊውን ተግባር እያከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ራስ ምታት እና ከ35.5 በላይ የሆነ የሰውነት ሙቀት [ትኩሳት] ከዝንጀሮ ፈንጣጣ ምልክቶች ውስጥ መካከል ይካተታሉ። በዚህም መነሻ በአገሪቱ በሁሉም ዓለምአቀፍ የየብስ እና የአየር በሮች ላይ የሙቀት ልኬት እየተከናወነ ነው።

ከሚጠበቀው በላይ የሆነ የሰውነት ሙቀት ያላቸው ሰዎች ለዚሁ ዓላማ ወደተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ተወስደው ተጨማሪ ምርመራዎች እንደሚደረግላቸው ያነሱት ኃላፊው፣ ለባለሙያዎች ሥልጣና እየተሰጠ እና በሽታው ቢያጋጥም የሚወሰዱ እርማጃዎችን በሚመለከት "የምላሽ መመሪያ" እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።

በሸታው በቆዳ ላይ የሚያስከትለው ሽፍታ እና ቁስለት
የምስሉ መግለጫ, በሸታው በቆዳ ላይ የሚያስከትለው ሽፍታ እና ቁስለት

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰትስ?

አቶ መስፍን እንደሚሉት በሽታው ኢትዮጵያ ውስጥ ቢከሰት በሚል መነሻ አስፈላጊ ግብአቶችን የሟሟላት እና አቅም የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በሁሉም ክልሎች ይህንን በሽታ የሚቆጣጠሩ ግብረ ኃይሎችን ማቋቋም፣ የተያዙ ሰዎችን ጉዳይ ለመከታተል የሚስችሉ ሥርዓቶችን ማጎልበት፣ የፈጣን ምላሽ ቡድን ማዋቀር እና የአቅም ግንባታ ተግባራትን በክልሎች ለማከናወን "የዓለም ጤና ድርጀትን ጨምሮ ከሌሎች አጋሮች ጋር እየሰራን ነው" ሲሉም አክለዋል።

ወደ አገሪቱ መግቢያ እና መውጫ በሆኑ በሮች በሚደረጉ ምርመራዎች እስካሁን ከዝንጀሮ ፈንጣጣ ጋር የተያያዘ አሳሳቢ ሁኔታ አለመከሰቱን ኃላፊው አመላክተዋል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምንድን ነው?

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወይም ሞንኪፖክስ በተሰኘ ቫይረስ የሚከሰተው በሽታው 'ስሞልፎክስ' ተብሎ የሚጠራው የፈንጣጣ ዝርያ ውስጥ የሚካተት ነው።

ከሰው ብቻ ሳይሆን ከእንስሳት እና ቫይረሱ ካለባቸው ቁሶች ጋር በሚኖር ንክኪ የሚተላለፈው በሽታው ለምጀመሪያ ጊዜ እንደ አውሮፓውያኑ በ1958 በዝንጀሮ ላይ የተገኘ ነው።

በ1978 ደግሞ በዲሞክራቲክ ኮንንጎ በሰው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መገኘቱ ተረጋግጧል። በገጠራማ የማዕከላዊ እና ምዕራባዊ አፍሪካ አገራት በፋት የሚያጠቃው የዝንጀሮ ፈንጣጣ እጅግ አሳሳቢ የሚባል አይደለም። በሽታውን 85 በመቶ መከላከል እንደሚችል የተረጋገጠ ክትባትም አለው።

አንዳንድ ጊዜ ያለምንም ህክምና በራሱ ጊዜ ሊጠፋ የሚችል ነው ። ሆኖም በምዕራብ አፍሪካ በበሽታው ምክንያት ህይወት አልፏል።

የበሽታው የሞት ምጣኔ ከ3 እስከ 6 በመቶ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጀት ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል።

ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የሰውነት እብጠት፣ የጀርባ እና የጡንቻ ህመም ደግሞ የበሽታው ምልክቶች ናቸው።