የዝንጀሮ ፈንጣጣን መቆጣጠር እንደሚቻል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ቅንጣቶች

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library

የምስሉ መግለጫ, የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ከፍተኛ ትኩሳት፣ የሰውነት ህመም እና ሽፍታን ያስከትላል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ(ሞንኪፖክስ) ባልተለመደባቸው ከአፍሪካ ውጭ ባሉ አገራት የቫይረሱን ሥርጭት መቆጣጠር እንደሚቻል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

እስካሁን ድረስ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና አውስትራሊያ ትኩሳትና በሰውነት ላይ ሽፍታ የታየባቸው ከ100 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ይሁን አንጂ ቁጥሩ ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል ይጠበቃል፤ ነገር ግን ባለሙያዎች ሰፊ ሕዝብ ለዚህ አደጋ የመጋለጥ እድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው ብለዋል።

ቫይረሱ በመካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪካ ገጠራማ አካባቢዎች የተለመደ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት የሚከሰቱ አዳዲስ በሽታዎች መሪ ማሪያ ቫን ኬርክሆቭ ቫይረሱን መቆጣጠር የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ ሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

" ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ ማቆም እንፈልጋለን" ያሉት መሪዋ፣ በቅርቡ በሽታው የተገኘባቸው አውሮፓንና ሰሜን አሜሪካን ጠቅሰው "በሽታው ወረርሽኝ ባልሆነባቸው አገራት ይህንን ማድረግ እንችላለን" ብለዋል።

ቫይረሱ እስካሁን ከአፍሪካ ውጭ በ16 አገራት ተገኝቷል።

ምንም እንኳን ይህ በ50 ዓመታት ውስጥ ከአፍሪካ ውጭ በስፋት የተከሰተ በሽታ ቢሆንም የዝንጀሮ ፈንጣጣ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ እንደማይተላለፍ እንዲሁም ህክምናውም ቢሆን ከኮሮናቫይረስ ጋር እንደማይወዳደር ባለሙያዎች ተናግረዋል።

"ቫይረሱ የሚተላለፈው በሽታው ካለበት ሰው ጋር በሚኖር የቆዳ ንክኪ ነው። አብዛኛው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም ቀለል ያለ ህመም ነው ያጋጠማቸው" ብለዋል ቫን ካርክሆቭ።

ሌላ የዓለም ጤና ድርጅት ባለሥልጣንም አሁን የተከሰተውን ወረርሽኝ መንስዔ በተመለከተ ቀደም ብለው ሲሰራጩ የነበሩ መላምቶችን ተከትሎ በሰጡት ምላሽ፣ ሞንኪፖክስ ልውጥ ቫይረስ መሆኑን የሚያሳይ ምንም መረጃ አለመኖሩን ገልጸዋል።

በዓለም ጤና ድርጅት የስሞልፖክስ ኃላፊ ሮሳመንድ " የቫይረሱ ዝርያ ራሱን የመለወጥ ባሕርይ የለውም። ይልቁንስ ዝርያዎቹ ባሉበት የመቆየት ባህርይ ነው ያላቸው" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ባለሥልጣን የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሌሎቹ በበለጠ ለአደጋው ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

የአውሮፓ በሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ዳሬክተር ዶክተር አንድሪያ አሞን እንዳሉት በሰፊው ሕዝብ ዘንድ በሽታው የመተላለፍ እድሉ አነስተኛ ነው፤ ይሁን እንጂ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ሰዎች ለምሳሌ ከተለያዩ ሰዎች ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈፅሙ ሰዎች ለበሽታው የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ሞንኪፖክስ) ቀደም ብሎ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ በሽታ አለመሆኑ የተገለጸ ቢሆንም በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት በሚኖር ቀጥተኛ ንክኪ ሊተላለፍ ይችላል።

ዶክተር አሞን አክለውም የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለመከላከልም ውጤታማ ነው የተባለውን ስሞልፖክስ ክትባት እንዳላቸው አገራት ማረጋገጥ እንዳለባቸው መክረዋል።

55 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በተገኙባት ዩናይትድ ኪንግደም፣ ባለሥልጣናት በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ለ21 ቀናት እንዲያገሉ መክረዋል።

አንድ ሰው በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈፅሞ ከሆነ ፣ አንሶላ እና ሌሎች አልባሳትን ተጋርቶ ከሆነ አሊያም የበሽታው መከላከያ የህክምና ቁሳቁሶችን በጋራ ተጠቅሞ ከሆነ ለበሽታው ተጋልጦ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል።

ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት፣ ማሳከክ፣ በኋላ ላይ ውሃ የሚቋጥር እብጠት የሚያስከትል ሽፍታ የበሽታው ምልክቶች ሲሆኑ እነዚህ ብዙውን ጊዜ ቀለል ያሉ ናቸው።

አብዛኛው ሰውም ከሁለት እስከ አራት ሳምንታት ባሉት ጊዜ ውስጥ ከበሽታው ያገግማሉ።