የዝንጀሮ ፈንጣጣ፡ የዓለም ጤና ድርጅት ዓለም በኮቪድ ፣ በዝንጀሮ ፈንጣጣ እና በጦርነት እየተፈተነች ነው አለ

የዝንጀሮ ፈንጣጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዓለም የኮቪድ 19-ወረርሽኝ ወረርሽኝን፣ የዩክሬን ጦርነትን እና የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ሞንኪፖክስ)ን ጨምሮ አስፈሪ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ነው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ይህንን ያሉት የተባበሩት መንግሥታት የጤና ባለሥልጣናት ከአፍሪካ ውጪ በ15 አገራት በተከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ዙሪያ በጀኔቫ በተካሄደው ውይይት ላይ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው እስካሁን በመላው ዓለም 92 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ 28 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሳይያዙ እንዳልቀረ ተጠርጥሯል።

ሆኖም በሽታው ወደ ብዙኃኑ ሕዝብ የመሠራጨት እድሉ ዝቅተኛ መሆኑ ተነግሯል።

በመካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪካ ገጠራማ አካባቢዎች በአብዛኛው የተለመደ የሆነው የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ሞንኪፖክስ) ቫይረስ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ የመተላለፍ ዕድሉ ዝቅተኛ ሲሆን ህመሙም ያን ያህል የከፋ አይደለም።

እንደ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ከሆነ በቫይረሱ የተያዙ አብዛኞቹ ሰዎች በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከበሽታው ያገግማሉ።

የወረርሽኙ መከሰት ተመራማሪዎችን ያስገረመ ሲሆን፣ የዩኬ የጤና ባለሥልጣናት በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ለሦስት ሳምንታት እንዲያገሉ መክረዋል።

ቤልጂየም በበሽታው የተያዘ ሰው ለሦስት ሳምንት ራሱን እንዲያገል አርብ ዕለት ያሳወቀች ሲሆን፣ ይህን ውሳኔ በማሳለፍም የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።

እሁድ ዕለት በተካሄደው የዓለም ጤና ጉባኤ ላይ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም "በዓለማችን ያለው ቀውስ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ብቻ አይደለም። በዓለም ዙሪያ ያሉ ባልደረቦቻችን በዲሞክራቲክ ኮንጎ ለኢቦላ ወረርሽኝ፣ በአፍጋኒስታን፣ በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶሪያ፣ በዩክሬንና በየመን ደግሞ ለዝንጀሮ ፈንጣጣ፣ ለሄፓታይተስ [የጉበት በሽታ] እና ውስብስብ ለሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት እየሰሩ ነው" ብለዋል።

"በወረርሽኝ፣ በድርቅ፣ በረሃብ እና በጦርነት ምክንያት አስፈሪ ሁኔታን ተጋፍጠናል" ብለዋል ዳይሬክተሩ።

ቀደም ብሎ የዓለም ጤና ድርጅት በዝንጀሮ ፈንጣጣ ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ በርካታ ሰዎች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጾ ነበር።

ቫይረሱ ሊገኝባቸው ይችላል ተብለው የተጠረጠሩ አገራትን ያልጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ተጨማሪ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

በቫይረሱ የተያዘ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በዩናይትድ ኪንግደም ሲሆን ከዚያ በኋላ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።

እስካሁን በስፔን፣ በፖርቹጋል፣ በጀርመን፣ በቤልጂየም፣ በፈረንሳይ፣ በኔዘርላንድስ፣ በጣሊያን፣ በኦስትሪያ፣ በስዊትዘርላንድ፣ በስዊድን፣ በካናዳ፣ በአሜሪካ እና በአውስትራሊያ በበሽታው የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው ተረጋግጧል።

ይሁን እንጂ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን ያሳወቁ ሌሎች አገራም አሉ።

የዩኬ የጤና ደኅንነት ተቋም እስካሁን 21 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ያስታወቀ ሲሆን የተቋሙ የጤና አማካሪ ኃላፊ ዶ/ር ሱሳን ሆፕኪንስ "በየቀኑ አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ተጨማሪ ሰዎች እያገኘን ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶክተር ሱሳን እንዳሉት ቫይረሱ በማኅበረሱ ውስጥ እየተሰራጨ ነው። በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል በሽታው ወረርሽኝ ወደ ሆነበት ምዕራብ አፍሪካ ተጉዘው ከነበሩ ሰዎች ጋር ንክኪ ያልነበራቸው ይገኙበታል።

ይሁን እንጂ ወደ አጠቃላይ ሕዝቡ የመዛመት አደጋው በጣም ዝቅተኛ ነው ያሉት ዶ/ር ሱሳን፣ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በተወሰኑ ከተማ አካባቢዎች የሚኖሩ እና ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ የሆኑ ናቸው ብለዋል።

ለዝንጀሮ ፈንጣጣ የራሱ የሆነ ክትባት ባይኖረውም፣ በርካታ አገራት ስሞልፖክስ የተባለ ክትባት እያከማቹ ነው።

ስሞልፖክስ ቫይረስ እና ሞንኪፖክስ ቫይረስ ዝርያቸው ተመሳሳይ በመሆናቸው ስሞልፖክስ ክትባት ወረርሽኙን 85 በመቶ የመከላከል አቅም አለው።

ሞንኪፖክስ ምንድን ነው? ምልክቱስ?

ምልክቶቹ

  • ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ እብጠት፣ የጡንቻ መቆረጣጠም እና መድከም
  • በአብዛኛው ፊት፣ እጅ እና እግር ላይ የሚከሰት ሽፍታ እና ቁስል

እንዴት ይተላለፈላል?

  • በበሽታው ከተያዘ ሰው ወይም እንስሳት ጋር በሚደረግ ንክኪ
  • በበሽታው የተያዘ ሰው የተገለገለባቸውን ልብሶች፣ አንሶላ ወይም አልጋ ልብስ በመንካት

ሕክምናውስ?

  • ስሞልፖክስ ክትባት ወይም ፀረ ቫይረስ መድኃኒቶችን መውሰድ ምልክቶቹን ለማጥፋት ይረዳል።
በቆዳ ላይ የሚታይ ውሃ የቋጠረ እብጠት

ይህ ወረርሽኝ ባለተጠበቀ መልኩ አሁን ለምን እንደተከሰተ ግልጽ የሆነ ነገር የለም።

ሁለት መላ ምቶች ግን አሉ።

አንደኛው ምንም እንኳን ቫይረሱ አዲስ ዝርያ መሆኑን የተወሰኑ ጥናቶች ቢጠቁሙም፣ ቀድሞ የነበረው ቫይረስ ራሱን ለውጦ ሊሆን ይችላል የሚል ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ቫይረሱ ራሱን ለማሳደግ ትክክለኛው ቦታ እና ጊዜ በመሆኑ ነው የሚል ነው።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ፣ የፈንጣጣ (ስሞልፖክስ) ክትባት በስፋት ከሚሰጥበት የቀደመው ጊዜ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በቀላሉ የመዛመት እድሉ ከፍተኛ ነው።