የዝንጀሮ ፈንጣጣ እንዴት ይተላለፋል? ምን ያህልስ ያሰጋናል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ)፣ አሜሪካ፣ ካናዳ እና አውስትራሊያን ጨምሮ በ12 አገራት የዝንጀሮ ፈንጣጣ (መንኪፖክስ) መከሰቱ ተገልጿል።
ዩኬ ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎች በበሽታው እስካሁን መያዛውን አስታውቃለች። አገሪቱ ለቅድመ ጥንቃቄ ክትባትም ገዝታለች።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምንድን ነው?
በሽታው የሚከሰው መንኪፖክስ በተባለ ቫይረስ ነው።
ለፈንጣጣ (ስሞልፖክስ) ከሚያጋልጠው ቫይረስ ጋር ዝርያው ይቀራረባል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ከፈንጣጣ ጋር ሲነጻጸር የሚሰራጭበት ፍጥነት አናሳ ከመሆኑም በላይ ሕመሙም አይበረታም።
በመካከለኛውና ምዕራብ አፍሪካ አገራት በገጠራማ አካባቢዎች ነው በብዛት የሚከሰተው። በተለይም በጥቅጥቅ ደን (ሬንፎረስት) አቅራቢያ ያጋጥማል።
ቫይረሱ ሁለት ዓይነት ዝርያ ያለው ሲሆን፣ አንደኛው የምዕራብ አፍሪካ ሁለተኛው ደግሞ የማዕከላዊ አፍሪካ የሚባሉ ናቸው።
ዬኬ ውስጥ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ሁለቱ ከናይጄርያ የተጓዙ ናቸው ተብሏል። ስለዚህ የተገኘባቸው የምዕራብ አፍሪካው ቫይረስ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።
ይህ ቫይረስ ለከፋ ሕመም አያጋልጥም።
በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች መካከል ይህ ነው የሚባል ግንኙነት አልተስተዋለም።
የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ታማሚዎችም ይገኙበታል።
ሰዎቹ ዩኬ ውስጥ ቫይረሱ ከተሰራጨ በኋላ በበሽታው እንደተያዙ ይገመታል።

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ሙቀት፣ ራስ ምታት፣ የጀርባ ሕመም፣ የጡንቻ ሕመም፣ የሰውነት እዚህም እዚያም ማበጥ እና በማንኛውም ነገር ላይ ፍላጎት ማጣት ይታይባቸዋል።
ሙቀቱ ጋብ ሲል ሰውነት ከፊት ጀምሮ ማሳከክ ይጀምራል። መላው ሰውነትን ቢያሳክክም ክንድና እግር የበለጠ ያሳክካሉ።
የሚከሰተው እከክ በጣም የሚያምና በተለያየ ደረጃ የሚያልፍ ነው።
ቆዳ ላይ የሚከሰተው እብጠት ኋላ ላይ ቆዳ እንዲቆስልና እንዲረግፍም ያደርል። ጠባሳ ጥሎም ሊያልፍ ይችላል።
ሕመሙ በራሱ ጊዜ የሚጠፋ ሲሆን ከ14 እስከ 21 ቀናት ይወስድበታል።
በሽታው እንዴት ይይዛል?
በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ሰዎች ተጋላጭ ናቸው።
በቆዳችን ክፍተቶች በኩል፣ በዓይን፣ በአፍንጫ ወይም በአፍ በኩል ቫይረሱ ወደ ሰውነታች ይገባል።
በወሲብ ወቅት ባለ ንክኪም ቫይረሱ ይተላለፋል።
በቫይረሱ ከተያዙ ዝንጀሮዎች፣ አይጦች ወይም ሌሎች እንስሳት ጋር ንክኪ ከተደረገ ቫይረሱ ወደ ሰው ይተላለፋል።
ቫይረሱ በልብስ ወይም በሌሎችም ንክኪ ባላቸው ጨርቆች በኩልም ይተላለፋል።
ምን ያህል አስጊ ነው?
አብዛኞቹ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ለከፋ ሕመም አይዳረጉም።
ልክ እንደ ፈንጣጣ በተወሰኑ ሳምንታት ውስጥ ይጠፋል። ሆኖም ግን በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ሊደርስም ይችላል።
በምዕራብ አፍሪካ በበሽታው ሳቢያ የሞቱ ሰዎች አሉ።
በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ወሲብን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት ንክኪ ሲኖር የበሽታው የመተላለፍ ዕድም ያለው ሲሆን፣ በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ወንዶች ዘንድ ለበሽታው የመጋለጥ ዕድል ጨምሮ ታይቷል።
ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በማቆያ ውስጥ ባለ ዝንጀሮ ላይ ነበር።
እአአ ከ1970 ወዲህ በ10 የአፍሪካ አገራት በሽታው ተከስቷል።
በ2003 በአሜሪካ ሲከሰት ከአፍሪካ ውጪ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር። ወደ አገሪቱ ከገቡ እንስሳት ላይ አንድ ውሻ በቫይረሱ ተይዞ ነበር ሕመሙ የተነሳው።
81 ሰዎች በቫይረሱ ቢያዙም የሞተ ሰው አልነበረም።
በ2017 በናይጄሪያ ቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ ተሰራጭቶ 172 ሰዎች መያዛቸው ይታወሳል።
75 በመቶ ታማሚዎች ከ21 እስከ 40 ዓመት የሆናቸው ወንዶች ናቸው።
ሕክምና አለው?
ለዝንጀሮ ፈንጣጣ ሕክምና የለውም።
ነገር ግን ስርጭቱን መቆጣጠር ይቻላል።
ክትባቱ በሽታውን በመከላከል ረገድ 85 በመቶ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል።
በዩናትድ ኪንግደም የጤና ደኅንነት ተቋም የሚሠሩት ፕሮፌሰር ጆናታን ባል እንደሚሉት፣ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ግንኙነት ከነበራቸው 50 ሰዎች አንዱ ብቻ በቫይረሱ መያዙ፣ የቫይረሱ የስርጭት መጠን ውስን መሆኑን ያሳያል።
















