በአዲስ አበባ ያጋጠመው የማደንዘዣ መድኃኒት እጥረት የፈጠረው ችግር

የኮሮና ህመምተኛ

የፎቶው ባለመብት, AMANUEL SILESHI

በአዲስ አበባ በሚገኙ የመንግሥት ጤና ማዕከላት የሰመመን (ማደንዘዣ) መድኃኒት እጥረት በማጋጠሙ የቀዶ ህክምና አገልግሎት በበቂ ሁኔታ መስጠት አለመቻላቸውን በተለያዩ ሆስፒታሎች የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎች ለቢቢሲ ገለጹ።

የምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል የአንስቶዮሎጂ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ቦንሳ ሃብሉ እንደሚሉት ሰክሶሚቶኒየም የተባለው አጠቃላይ የሰመመን መድኃኒት እጥረት በማጋጠሙ በቋሚነት የሚሰሩ የቀዶ ህክምና አገልግሎት መቆማቸውን ተናግረዋል።

"እጥረቱ የተከሰተው ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መድኃኒቱን እየተጠቀምን ያለነው ለድንገተኛ ህመሞች፣ በቀዶ ጥገና ለማዋለድና አደጋ ደርሶባቸው ለሚመጡ ሰዎች ብቻ ነው" ብለዋል።

ሰክሳሚቶኒየም የተሰኘው የሰመመን መድኃኒት ሁሉንም የቀዶ ህክምና አገልሎቶች ለመስጠት ወሳኝ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተሩ፣ ይህንን በተወሰነ መልኩ የሚተኩ ማደንዘዣዎች ቢኖሩም ሙሉ በሙሉ የዚህን መድኃኒት ሥራ መተካት እንደማይችሉ ያስረዳሉ።

በዚህም የተነሳ በቋሚነት የሚሰሩ የቀዶ ህክምና አገልግሎቶችን በማቆም ያሏቸውን መድኃኒቶች ለወላዶችና ድንገተኛ አደጋ ለደረባቸው ሰዎች ብቻ ለመጠቀም ውሳኔ ላይ ተደርሷል ብለዋል።

ሌላኛው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉና በአንድ መንግሥት ሆሰፒታል ውስጥ የሚሰሩ የቀዶ ህክምና ባለሙያ የሰመመን መድኃኒት እጥረት ካጋጠመ መቆየቱን አመልክተው፣ ሆስፒታሎችም ያልተመዘገበና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚገባ ማደንዘዣ ከጥቁር ገበያ እየገዙ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አወል ሐሰን ሰክሳሚቶኒየም የተባለው የሰመመን መድኃኒት እጥረት ማጋጠሙን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። እጥረቱ ሰክሳሚቶኒየም የተባለውና ለቀዶ ጥገና በጣም ወሳኝና ብቸኛ የሆነ ግብዓት ነው ይላሉ።

የሰመመን (ማደንዘዣ) መድኃኒት

የፎቶው ባለመብት, Alamy

መድኃኒቶችን በመላው አገሪቱ ለሚገኙ የመንግሥት የጤና ማዕከላት ግዢ በማከናወንና በማሰራጨት አገልግሎት የሚሰጠው ተቋሙ ለማደንዘዣነት በዝርዝሩ ውስጥ ካካተታቸው አስራ ሁለት አይነቶች በአንዱ ላይ እጥረት ተከስቷል ብለዋል። ሌሎቹ ግን በአስራ ሰባቱም የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ቅርንጫፎች በበቂ መጠን አለ ብለዋል ለቢቢሲ።

ዳይሬክተሩ ይህንን ይበሉ እንጂ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት የቀዶ ህክምና ባለሙያው ጡንቻን ለማፍታታት የሚጠቅመው ዲክሮኒየም የተባለ ማደንዘዣ ሙሉ በሙሉ ከከተማው ውስጥ ጠፍቶ እንደነበር ይገልጻሉ።

ጠቅላላ ቀዶ ህክምና ሲደረግ የሚሰጠው ዲክሮኒየም የሚባለው የዚህ ማደንዘዣ እጥረት በአሁኑ ወቅትም እንዳለ የሚያስረዱት ሐኪሙ ከዚህም ጋር ተያይዞ ከእጥፍ በላይ በሆነ ገንዘብ ሆስፒታሎች ለመግዛት ተገደዋል ብለዋል።

የሰክሳሜቶኒየም እጥረት ለምን እንደተከሰተ የተጠየቁት የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ተቋም የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ አወልም ከዓለም አቀፍ የግዢ ሂደት ጋር የተያያዘ እንደሆነም አስረድተዋል።

ሰመመን ሰጪ መድኃኒቶቹ በአገር ውስጥ የሚመረቱ እንዳልሆነና ሁሉም በሚባል ደረጃ ከውጭ አገራት የሚመጡ ከመሆናቸው አንፃር የአቅርቦት መቆራረጥ በአንድም ሆነ በሌላም ጊዜ ያጋጥማል ይላሉ።

ለዚህም የአቅርቦት ችግር ብለው ከሚጠቅሷቸው አንደኛው ምክንያት ከመጠን ጋር የተያያዘ ወይም ምን ያህል እንደሚያስፈልግ ከመገመት 'ፎርካስት' ከማድረግ ጋር ያይዙታል።

በተጨማሪም ከአቅርቦት ሰንሰለት ጋር እንዲሁም መድኃኒቶቹ ወደ አገር ውስጥ በሚመጡበት ወቅት ረዥም ጊዜ ከመውሰዱ እጥረቱ በጊዜያዊነትም ቢሆን መፈጠሩን ያስረዳሉ።

ችግሩ ጊዜያዊ ነው የሚሉት አቶ አወል "ዛሬ እጥረት አለ ማለት ነገ እጥረት ይፈጠራል ማለት አይደለም" ብለዋል።

ዳይሬክተሩ መድኃኒቶቹ ወደ አገር ውስጥ መግባት መጀመራቸውን ጠቅሰው በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ማሰራጨት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

ችግቱን በአጭር ጊዜ ለመቅረፍና የተፈጠረውን እጥረት ለማስተካከል ከጎረቤት አገር ጭምር በአስቸኳይ በአየር ትራንስፖርት ምርቱ እንደሚገባና ወደ ጤና ተቋማቱም እንደሚሰራጭ አስረድተዋል።

የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምርቱ ከሚመረትበት አገር በባሕር ትራንስፖርት ተጓጉዞ ይሰራጫል ብለዋል።