የዩክሬን ጦርነት ዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል-ተመድ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ በቀጣይ ወራት ዓለም አቀፍ የምግብ እጥረት ሊያስከትል ይችላል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስጠነቀቀ።
ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንዳሉት ጦርነቱ በድሃ ሃገራት የዋጋ ንረትን በማስከተል የምግብ ዋስትና እጥረትን አባብሶታል።
የዩክሬን ወጪ ንግድ ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት ደረጃ ካልተመለሰ ዓለም ለዓመታት የሚዘልቅ ረሃብ ሊገጥማት ይችላል ሲሉም አክለዋል።
በአንድ ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው የሱፍ ዘይት፣ በቆሎ እና ስንዴ ወደ ውጭ ይልኩ የነበሩት የዩክሬን ወደቦች ከስራ ርቀዋል።
ይህም የዓለም አቀፍ አቅርቦትን ከመቀነስ ባለፈ የሌሎች አማራጮችን ዋጋ እንዲንር አድርጓል። እንደ ድርጅቱ ከሆነ የዓለም የምግብ ዋጋ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር በ30 በመቶ ብልጫ አለው።
ረቡዕ በኒውዮርክ ንግግር ያደረጉት ጉቴሬዝ ግጭቱ "በአስር ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ ዋስትና እጦት ምክንያት ሲሆን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና ረሃብ እንዳያስከትልም ያሰጋል" ብለዋል።
አክለውም "ተባብረን ከሠራን በዓለማችን ላይ በቂ ምግብ አለ። ችግሩን ዛሬ ካልፈታን በሚቀጥሉት ወራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ እጥረት ችግር ውስጥ እንገባለን"ብለዋል።
የዩክሬን የምግብ ምርት እንዲሁም የሩሲያ እና የቤላሩስ ማዳበሪያ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ከመቀላቀል ውጭ ለምግብ ቀውሱ ምንም አይነት ውጤታማ መፍትሄ የለም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የምግብ ምርቶችን ወደ መደበኛ ደረጃ ለመመለስ ከሩሲያ፣ ከዩክሬን፣ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር "ጠንካራ ግንኙነት" እኣደረጉ መሆናቸውን ጉቴሬዝ ተናግረዋል ።
"ውስብስቡ የጸጥታ፣ የኢኮኖሚ እና የፋይናንሺያል ሁኔታዎች በሁሉም በኩል መልካም ምላሽ ያስፈልጋቸዋል" ብለዋል።
የዋና ጸሐፊው አስተያየታቸውን በሰጡበት ዕለት የዓለም ባንክ የምግብ ዋስትና እጦትን ለሚፈቱ ፕሮጀክቶች የሚውል 12 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ይፋ ማድረጉን አሳውቋል።
እርምጃው በሚቀጥሉት 15 ወራት ለተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ያለውን ጠቅላላ ገንዘብ ወደ ከ 30 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ያደርሰዋል።
ከጦርነቱ በፊት ሩሲያ እና ዩክሬን 30 በመቶውን የዓለም የስንዴ አቅርቦት ያመርቱ ነበር። የዓለም የዳቦ ቅርጫት ተደርጋ ትታይ የነበረው ዩክሬን በወር 4.5 ሚሊዮን ቶን የግብርና ምርቶችን በወደቦቿ ወደ ውጭ ትልክ ነበር።
ሩሲያ ወረራ ከጀመረችበት ከየካቲት ወር በኋላ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ቀንሰዋል ዋጋቸውም አሻቅቧል። ህንድ ወደ ውጭ የሚላክ ስንዴ ላይ እገዳ መጣሏ ደግሞ ችግሩን አባብሶታል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀው ባለፈው ዓመት ከተሰበሰበው ምርት 20 ሚሊዮን ቶን እህል በዩክሬን ይገኛል። ይህ ቢለቀቅ በዓለም ገበያ ላይ ያለውን ጫና ሊቀንስ ይችላል።
የምግብ ዋስትና እጦት የተጋረጠባቸው ሰዎች ቁጥር ከወረራው በፊትም እየጨመረ ነበረ። የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ በበኩላቸው ሞስኮ ሁኔታውን የበለጠ የከፋ አድርጋለች ሲሉ ከሰዋል።
"ሩሲያ የዓለም የምግብ ቀውስ በማስነሳት የእህል ጦርነት ከፍታለች። ይህንንም ያደረገችው በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ እና በአፍሪካ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ እየተሰቃዩ ባለበት ወቅት ነው" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እንዳሉት ዓለም በዘመናችን ትልቁ የምግብ ዋስትና ቀውስ ገጥሟታል። ይህንንም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን "መርጠው በገቡበት ጦርነት" ተባብሷል ብለዋል።












