አሜሪካ ወታደሮቼ ሶሪያ ውስጥ ሆነ ብለው ሰው አልገደሉም አለች

በሶሪያ የደረሰው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካ ጦር ሠራዊት በፈረንጆቹ 2019 ሶሪያ ውስጥ በተፈፀመው የአየር ድብደባ ወታደሮቼ ሆነ ብለው ሰው አልገደሉም ብሏል።

የጦር ሠራዊቱ ምርመራ በአየር ድብደባ በርካቶች ቢገደሉም የአሜሪካ ወታደሮች ግን ጥፋት አላጠፉም ብሏል።

ሠራዊቱ ምርመራ ያደረገው ኒው ዮርክ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ የአሜሪካ ጦር ኢስላሚክ ስቴትን አጠቃሁ በሚል ሰበብ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል ሲል ማስነበቡን ተከትሎ ነው።

ምርምራው ሲመሩ የነበሩት ግለሰብ ግን ይህ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል።

ነገር ግን የተለያዩ "የፖሊሲ ጉዳዮች" ምርመራው በጊዜ እንዳይጠናቀቅ ምክንያት ሆነዋል ሲሉ ገልጠዋል።

በአሜሪካ የሚመራው ፀረ አይኤስ ጥምረት ከ2014 ጀምሮ በኢራቅና ሶሪያ 1417 ሰላማዊ ሰዎች መግደሉን አምኖ ነበር።

ቢሆንም ኤርዌይስ የተሰኘው ቡድን በአሜሪካና አጋሮቿ የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር ከ8 ሺህ እስከ 13 ሺህ ሊደርስ ይችላል ይላል።

የአየር ጥቃቱ የተሰነዘረው ባጉዝ በተሰኘችው የሶሪያ ከተማ ነበር።

በወቅቱ በአሜሪካ የሚደገፈው የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይል የኢስላሚክ ስቴትን የመጨረሻ ይዞታ ለማስለቀቅ እየታገለ ነበር።

የፔንታጎንን ምርመራ የመሩት ጄኔራል ሚካኤል ጋሬት በዘገባቸው የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ከአይኤስ ጥቃት ከተሰነዘረበት በኋላ የአየር ኃይል እርዳታ መጠየቁን አስረድተዋል።

"በወቅቱ መሬት ላይ የነበረው የአሜሪካ ጦር የአይኤስን ጥቃት አመዛዝኖ እንዲሁም በሥፍራው ሰላማዊ ዜጎች አለመኖራቸውን አረጋግጦ የአየር ድጋፍ አድርጓል" ብለዋል መርማሪው።

"ነገር ግን ከአሜሪካ ጦር እውቅና ውጭ በሆነ መልኩ በሥፍራው ሰላማዊ ነዋሪዎች ነበሩ፤ አደጋም ደርሶባቸዋል" ሲሉ አክለዋል።

ኒው ዮርክ ታይምስ ባለፈው ኅዳር ባወጣው ዘገባ የአየር ጥቃቱ በደረሰበት አካባቢ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ በአይኤስ የተያዙ ምርኮኞች እና ቁስለኞች ነበሩ ብሏል።

ዘገባው አክሎ የአሜሪካ ጦር በፈፀመው ጥቃት 70 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ሲል አስነብቧል።

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ግን አራት ሕፃናትና አንዲት ሴት ሲገደሉ 15 ሰላማዊ ዜጎች ደግሞ ቆስለዋል ይላሉ።

ጄኔራል ጋሬት ባወጡት የምርመራ ዘገባ በወቅቱ የነበረው አዛዥ የተሰጠውን መረጃ ተከትሎ ነው እርምጃ የወሰደው ብለዋል።

ነገር ግን ሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰውን አደጋ በተለመከት ምርመራው መዘግየቱ ተገቢ አይደለም ብለዋል መርማሪው።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን የጥቃቱ የመጀመሪያ ምርመራ ውጤት መዘግየቱ እንዳበሳጫቸው ተናግረዋል ተብሏል።