ታሪክ ሰሪው ኤርትራዊ ብስክሌተኛ በሻምፓኝ ቡሽ ዓይኑ በመመታቱ ውድድሩን ለማቋረጥ ተገደደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግሪዮ ዲ ኢታሊያ የተሰኘውን የብስክሌት አለም አቀፍ ውድድር አንድ ዙር በማሸነፍ የመጀመሪያዊ አፍሪካዊ በመሆን ታሪክ የሰራው ቢንያም ግርማይ በአደጋ ምክንያት ውድድሩን ለማቋረጥ ተገዷል።
ኤርትራዊው ቢንያም ግርማይ በትናንትናው ዕለት 10ኛውን ዙር አሸንፎ የነበረ ሲሆን ይህንንም ደስታውን ለመግለፅ ፕሬስኮ የተሰኘውን ሻምፓን ቡሽ ሲከፍት ግራ ዓይኑ በመታቱ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።
በኋለም ከቡድን አጋሮቹ ጋር ድሉን አብሮ ቢያጣጥምም በዛሬው ዕለት የነበረውን ውድድር ለመጀመር ብቁ አልነበረም።
የኢንተርማቼ ዋንቲ ጎበርት ብስክሌተኛ የሆነው ቢንያም በአሁኑ ወቅት "ደህና ነኝ" ቢልም ማገገም እንዳለበትም ተናግሯል
" በሻምፓኙ መክፈት ላይ በተፈጠረው ነገር ትንሽ አዝኛለሁ። እንዲሁም የቡድን አጋሮቼም ፈርተው ነበር" ብሏል ቢንያም
"በዛሬው ዕለት በውድድሩ አልተሳተፍኩም ምክንያቱም አይኔ ተጨማሪ እረፍት ስለሚያስፈልገው ነው። በትናንትው ዕለት ከሆስፒታል ስመለስ ድሌን ከቡድን ጓደኞቼ ጋር አብረን በደስታ አሳልፈነዋል"
"አሁን ደህና ነኝ። ለረዱኝ ሁሉ አመሰግናለሁ።"
የቡድኑ ዶክተር ፒየት ዳንኤልስ በበኩላቸው አደጋው ከደረሰበት በኋላ በተደረገለት ምርመራ ቢንያም በግራ አይኑ ላይ የደም መፍሰስ እንዳጋጠመውና ይህም ሁኔታ ወደ ሌላው የሰውነት አካሉ እንዳይዛመት ስጋቱን ለመቀነስ በውድድሩ እንዳይሳተፍ መደረጉን ተናግረዋል።
የመጀመሪያ ግራንድ ቱር ውድድሩን በጣሊያን ያደረገው የ22 አመቱ ወጣት ሆላንዳዊውን ማቲዩ ቫን ደር ፖልን ጄሲ በተሰኘው መስመር በአስደናቂ ፍጥነት አሸንፏል።
ቢንያም ድሉን "የማይታመን" ሲል የገለጸው ሲሆን ነገር ግን ከውድድሩ በኋላ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሆስፒታል በመወሰዱ መገኘት አልቻለም።
ቢንያም አክሎም "በመጀመሪያ ሁሉንም የቡድኑን አባላት ሰራተኞቹን አመሰግናለሁ። ቡድኑ ከውድድሩ መጀመሪያ አንስቶ እስከ ፍፃሜው ድረስ 99 በመቶ የሚቻለውን ያህል አድርጓል" ብሏል።
"ቡድኑ ባደረገው ነገር በጣም ደስተኛ ነኝ። ከውድድሩ በፊት ሁሉም ሰው እጅግ እያበረታታኝ ነበር። ድሉ የቡድኑ ነው" ብሏል።
ቀጣዩ ውድድር 'ሰቴጅ 11' (ደረጃ 11) ከሳንታርካንጄሎ ዲ ሮማኛ ወደ ሬጂዮ ኤሚሊያ ያለውን 203 ኪ.ሜ መንገድ የሚሸፍን ሲሆን ለ 22 አመቱ ወጣት ሌላ የማይረሳ ድል እንዲያገኝ እድል ይሰጠው ነበር።
በጊሮ የመክፈቻ ውድድር ላይ በቫን ደር ፖኤል ድል የተነፈገው ቢንያም በመጋቢት ወር በቤልጂየም ገንት ዌቨልገም ክላሲክ ዓለም አቀፍ ውድድር ያሸነፈ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ነው












