በአዲስ አበባ ከአሠሪዋ ድብደባ ለማምለጥ ከአራተኛ ፎቅ የወደቀችው የ13 ዓመት ታዳጊ

የሕጻናት ብዝበዛ

የፎቶው ባለመብት, gan chaonan

ገና 13 ዓመቷ ነው። በቤት ሠራተኛነት ከተቀጠረች ውስን ዓመታት መቆጠራቸውን በቅርብ የሚያውቋት ሰዎች ይናገራሉ።

ብርቱካን ትባላለች [ለደኅንነቷ ሲባል በመጀመሪያ ስሟ ብቻ እንጠራታለን]። ራሷ ልጅ ብትሆንም የአሠሪዎቿን ልጆች የመንከባከብ ኃላፊነት ወድቆባት ቆይቷል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ብርቱካን አትማርም። በአሠሪዎቿ ትንጓጠጣለች። ትሰደባለች። ባስ ሲልም በተደጋጋሚ እንደምትደበደብ ፖሊስም ለቢቢሲ አረጋግጧል።

ሚያዝያ 21/2014 ዓ. ም. የደረሰባት ግን ከመቼውም የባሰ ነው። እንግልት የሞላው አጭር ሕይወቷ ከፍ ያለ መከራ ገጠመው።

የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የብርቱካን አሠሪዎች ጎረቤቶች፣ ብርቱካንን በቅርብ የሚያውቋት ሰዎች እና የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሴቶችና ሕጻናት ጽሕፈት ቤት እንደነገሩን በዕለቱ የደረሰባት ይህ ነው።

ክስተቱ ሰሚት ኮንዶሚኒየም ውስጥ ነው የተፈጸመው። ረፋድ ላይ አሠሪዋ "ከቤት እቃ ጠፍቷል፤ የት አለ?" ይላታል። ምንም እንደማታውቅ ትናገራለች።

አሠሪዋ ግን "አላውቅም" ማለቷን ሳይቀበል ይደበድባት ጀመር። የልጅ አካሏ ከሚችለው በላይ ስትደበደብ ራሷን ሳተች። አሠሪዋ ውሃ ሲያፈስባት ነቃች።

ድብደባው እንደማያቋርጥ የተገነዘበችው ብርቱካን ነፍሴን ባድን ብላ ከቤቱ በመስኮት ዘላ ወጥታ ከአራተኛ ፎቅ ወደ ምድር ተወረወረች።

አንድ ሱቅ ጣሪያ ላይ አርፋ ከመሬት ወደቀች። የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪዎች ተረባርበው ወደ ጤና ጣቢያ ወሰዷት። አሠሪዋን ደግሞ ለፖሊስ አስረከቡ።

ብርቱካን ይህ ዘገባ በወጣበት ወቅት በተወሰነ ደረጃ አገግማለች።

ቢቢሲ ግንቦት 05/2014 ዓ. ም. ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፣ ግለሰቡ አሁንም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ነው ቢሉም፣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የወረዳ 5 የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊት ለሊሴ ብላታ ደበላ ግን ግለሰቡ በዋስ ከእስር መለቀቁን መረጃ እንደደረሳት ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ ገልጻለች።

የሰሚት ኮንዶሚኒየም ሁለት ነዋሪዎችም ግለሰቡ ከቀናት እስር በኋላ ተለቆ ጊቢ ውስጥ እንዳዩት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"ሲጨንቃት፣ ሲመራት አምልጣ ራሷን ከፎቅ ወረወረች"

ዘመን (ስሟ ተቀይሯል) ብርቱካንን በቅርብ ታውቃታለች።

ለደኅንነቷ በመስጋቷ የትውውቃቸው ደረጃ በይፋ እንዲገለጽ አልፈለገችም።

"ሰውዬው ላፕቶፕ መሰለኝ ጠፋብኝ ያለው። 'ላፕቶፑን አምጪ' ብሎ መኝታ ቤት አስገብቶ ሲቀጠቅጣት፣ ሲቀጠቅጣት ራሷን ሳተች። ውሃ ሲያፈስባት ተመልሳ ተነሳች። ሲደበድባት 'ተወኝ አትግደለኝ' እያለች ትለምነው ነበር። ሲጨንቃት፣ ሲመራት አምልጣ ራሷን ከፎቅ ወረወረች" ትላለች።

ዘመን እንደምትለው፣ ድብደባው የጀመረው ረፋድ 4 ሰዓት አካባቢ ሲሆን ቢያንስ ለሁለት ሰዓታት ቆይቷል።

ብርቱካን ከፎቅ ራሷን ስትወረውር አሠሪዋ "ደንግጦ ነበር" ትላለች ዘመን።

ቤት ውስጥ ልጅ መንከባከብን ጨምሮ ሌሎችም ኃላፊነቶችን ታዳጊዋ ትወጣ እንደነበር ትናገራለች።

ከሚያዝያ 21ዱ ክስተት በፊትም በአሠሪዋ አካላዊ ጥቃት ደርሶባት እንደነበር ታክላለች።

ብርቱካን የዚያን ዕለት ድብደባ ከደረሰባት በኋላ አዲስ አበባ የምትኖር እህቷ ለዘመን እንደነገረቻት፣ ወገቧን ታማለች።

ብርቱካን ከአሠሪዋ ድብደባ ራሷን ለመከላከል ከአራተኛ ፎቅ ስትዘል የወደቀችበት ሱቅ

የፎቶው ባለመብት, SM

የምስሉ መግለጫ, ብርቱካን ከአሠሪዋ ድብደባ ራሷን ለመከላከል ከአራተኛ ፎቅ ስትዘል የወደቀችበት ሱቅ

"ሱቁ ጣሪያ ላይ ባታርፍ ኖሮ በሕይወት የምትተርፍ አይመስለኝም"

ግለሰቡ በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲውል በማድረግ ከፍተኛ ሚና ከተወጡ ነዋሪዎች መካከል አንዷ ፀሐይ (ስሟ ተቀይሯል) ናት።

ጉዳዩ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ሳያገኝ እንዳይቀር ስለክስተቱ ለቢቢሲ ጥቆማ ሰጥታለች።

በዕለቱ ጩኸት ሰምታ ከቤቷ ስትወጣ ታዳጊዋ ከአራተኛ ፎቅ ወድቃ፣ በጭቃ ተለውሳ፣ ፊቷ በልዞ፣ ራሷን ስታ መሬት ላይ ተዘርራ አገኘቻት።

የኮንዶሚንየሙ ነዋሪዎች በአካባቢው ያልፍ የነበረ ባለ መኪና ለምነው ብርቱካንን ወደ ጤና ጣቢያ ወሰዷት።

"አብሯት ወደ ጤና ጣቢያ የሚሄደው ማነው? ሲባል አንድ ሰው መኪና ውስጥ ገባ። ከዚያ 'እሱ እኮ ነው ከአራት ሰዓት ጀምሮ ሲደበድባት የነበረው' ሲባል ሰማሁ። አብሯት ከሄደ መንገድ ላይ ሊወርድ ይችላል ብዬ ፖሊስ ጠራሁ። ጤና ጣቢያ መጥተው ያዙት" ትላለች።

ብርቱካን በአካባቢው ከሚገኘው ሰሚት ጤና ጣቢያ ወደ የካቲት 12 ሪፈር ተጽፎላት ሕክምና አግኝታለች። ከቀናት በኋላም ከሆስፒታሉ ወጥታለች።

"እዚያ ቤት ስትሠራ ቢያንስ ሦስት ዓመት አልፏታል። ስለዚህ የመጣችው በ10 ዓመቷ ነበር ማለት ነው። ልጅ ያዥና የቤት ሠራተኛ ናት። የዚያን ቀን ሱቁ ጣሪያ ላይ ባታርፍ በሕይወት የምትተርፍ አይመስለኝም።"

ፀሐይ እንደምትለው፣ ብርቱካን እና ግለሰቡ "ዘመዶች ናቸው" ሲባል ሰምታለች። ጉዳዩ በፖሊስ ቢያዝም፣ ምናልባት ቤተሰባዊ ጫና ተደርጎ ብርቱካን ተገቢውን ፍትሕ ሳታገኝ ልትቀር ትችላለች የሚል ስጋት አላት።

"እኔም እናት ነኝ፤ እንደ ራስሽ አድርገሽ ስታስቢው ያሳዝናል"

ዓለም (ስሟ ተቀይሯል) ድርጊቱ የተፈጸመበት ኮንዶሚኒየም ውስጥ ነው የምትኖረው። ከፖሊስ የዓይን እማኝ ምስክሮች አንዷ ናት።

ብርቱካን የሱቅ ጣሪያ ላይ ከወደቀች በኋላ ጩኸት ሰምታ ነው ከቤቷ የወጣችው።

"ከጣሪያው መሬት ላይ ተጣጥፋ፣ በጎኗ ወደቀች። ራሷን ስታ ነበር። ሰውየው ደንግጦ እየሮጠ መጣና ጤና ጣቢያ ተወሰደች" ስትል ታስታውሳለች።

በዕለቱ ፖሊሶች ወደ ጊቢው ሄደው መረጃ እንደሰበሰቡና የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሴቶችና ሕጻናት ክፍል ባልደረቦችም የዓይን እማኞችን እንዳነጋገሩ ገልጻልናለች።

"ልጅቷ ፖሊስ ጣቢያ ቃሏን ስትሰጥ ደንግጣ ዝም ብላ ነበር። ብታያት ታሳዝንሻለች። ከዚያ በፊትም ጊቢ ውስጥ አያታለሁ። ፊቷ ላይ ደስታ አይታይም። እኔም እናት ነኝ። እንደ ራስሽ አድርገሽ ስታስቢው ያሳዝናል።"

ድብደባው እንደማያቋርጥ የተገነዘበችው ብርቱካን ነፍሴን ባድን ብላ ከቤቱ በመስኮት ዘላ ወጥታ ከአራተኛ ፎቅ ወደ ምድር ተወረወረች።

የፎቶው ባለመብት, SM

የምስሉ መግለጫ, ድብደባው እንደማያቋርጥ የተገነዘበችው ብርቱካን ነፍሴን ባድን ብላ ከቤቱ በመስኮት ዘላ ወጥታ ከአራተኛ ፎቅ ወደ ምድር ተወረወረች።

"ብዝበዛን አይታችሁ፣ እንዳላየ አትለፉ"

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የወረዳ 5 የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊት ለሊሴ ብላታ ደበላ እንደምትለው፣ ብርቱካን አሁን ጤናዋ እየተሻሻለ ቢመጣም የወገብ ሕመም ገጥሟታል።

"አሁን ያለችው አክስቷ ቤት እንደሆነና ተጠርጣሪው በዋስ መውጣቱንም መረጃው አለኝ" ትላለች።

በጊቢው ከሚኖሩ ጎረቤቶች ባገኘችው መረጃ መሠረት ከቤት ውስጥ "እቃ ጠፍቷል፤ የት እንዳደረሽው አውጪ" በሚል ሰበብ ነው ድብደባው የተፈጸመው።

"ትምህርት እንኳን እንደማትማር እና በየጊዜው ድብደባ እንደሚደርስባት ሰምቻለሁ" ስትል ታስረዳለች።

ለሊሴ እንደምትለው፣ ከዚያ ቀደምም በዚያው ሰፈር ሌላ የ12 ዓመት ታዳጊ "መደብደብና መጎሳቆል ሰልችቷት በመስኮት ልትዘል ስትል ይዘን ለፖሊስ አስረክበን እናውቃለን።"

መሰል ጥቃቶችን፣ አይቶ እንዳላየ ከማለፍ ይልቅ እያንዳንዱ ሰው ጥቆማ ቢሰጥ የሕጻናት የጉልበት ብዝበዛንና በደልን ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ትመክራለች።

"አብዛኛው የኮንዶሚኒየም ነዋሪ፣ ከገጠር ዘመድንም የጎረቤት ልጆችንም በማምጣት በር ዘግቶባቸው ጉልበታቸውን ይበዘብዛል፤ ያጎሳቁላቸዋል። ሴት ሕጻናትን ትምህርት በመከልከል የወደፊት አገር ተረካቢ ትውልድ እያሳጡን ያሉ ብዙ ናቸው" ትላለች ኃላፊዋ።

ማኅበረሰቡ መጀመሪያ ቤቱን እንዲፈትሽ፣ አልፎም ብዝበዛን ከማለፍ ይልቅ አጥቂዎችን እንዲያጋልጥ በአጽንኦት ታሳስባች።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፣ የ13 ዓመት ታዳጊዋ ከድብደባ ለማምለጥ ስትሞክር ከፎቅ ስለመውደቋ ከፖሊስ መዝገብ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

"ከምርመራ መዝገቡ መረዳት እንደተቻለው ደብዳቢው ግለሰብ በእናቷ በኩል ዝምድና አለው። ከክልል ከተማ እንዳመጣት ነው መረጃዎች የሚያሳዩት። ግለሰቡ 'የት ሄድሽ?' 'ምን ስትሠሪ ነበር?' 'የት ቆየሽ?' እያለ ሁሌም ይደበድባት እንደነበረ ታዳጊዋ ከሰጠችው ቃል መረዳት ተችሏል" ይላሉ።

ብርቱካን ከየካቲት 12 ሆስፒታል ወጥታ አያቷ ጋር እንዳለች ገልጸው፤ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደምትገኝ መረጃ እንደደረሳቸው አክለዋል።

"በሕጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት በአገር ላይ የተቃጣ ጥቃት ተደርጎ ነው መታሰብ ያለበት" ያሉት ኮማንደር ማርቆስ፣ አጥፊዎችን ለፖሊስ በማጋለጥ ኅብረተሰቡ እንዲረባረብ ጠይቀዋል።

የቤት ሠራተኞች ላይ የሚደርሰው እንግልት መልኩ ብዙ ነው። ድብደባ፣ ወሲባዊ ትንኮሳ፣ የቃላት ጥቃት፣ ደመወዝ መቀማት፣ ስልክ መንጠቅ፣ የመኝታ ጊዜ ማሳጣት፣ ምግብ መከልከል እና ሌሎችም ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እንደሚፈጸሙ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።