አስገድዶ ሊደፍራት የሞከረውን የገደለችው ናይጄሪያዊት ታዳጊ ነጻ ተባለች

በርካቶች ታዳጊዋ እራሷን ለመከላከል ስትል በወሰደችው እርምጃ መጠየቅ የለባትም ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

የፎቶው ባለመብት, BBC/Chris Ewokor

የምስሉ መግለጫ, በርካቶች ታዳጊዋ እራሷን ለመከላከል ስትል በወሰደችው እርምጃ መጠየቅ የለባትም ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

የናይጄሪያ አቃቤ ሕግ አስገድዶ ሊደፍራት የሞከረውን የ51 ዓመት ግለሰብ የገደለችው የ15 ዓመት ታዳጊ ክስ ሊመሰረትባት አይገባልም አለ።

ከሦስት ወራት በፊት የአባቷ ጓደኛ ወደ ሆነው ግለሰብ መኖሪያ የቤት ውስጥ ሥራ ለመስራት ከሄደች በኋላ ግለሰቡ አስገድዶ ሊደርፍራት ሲሞክር በስለት እንደወጋችው ፖሊስ አስታውቋል።

አቃቤ ሕግ በእስር ላይ የነበረችው የ15 ዓመት ታዳጊ በ51 ዓመቱ ግለሰብ የግድያ ወንጀል ክስ ሊመሰረትባት የሚያስችል ማስረጃ ባለመኖሩ ክስ ሊመሰረትባት አይችልም ካለ በኋላ ታዳጊዋ ነጻ ወጥታለች።

በእስር ላይ በነበረችበት ወቅት በርካቶች እራሷን ለመከላከል ስትል በወሰደችው እርምጃ መጠየቅ የለባትም ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በናይጄሪያ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ይፈጸማሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ይቁሙ ሲሉ በኢንተርኔት አማካኝነት ፊርማ ሲያስባስቡ ቆይተዋል።

የታዳጊዋ ወላጆች በጉዳዩ ላያ ያሉት የለም።

በተመሳሳይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰ በኋላ በናይጄሪያ ጾታዊ ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉ ሴቶች ቁጥር በፍጥነት መጨመሩ ተነግሯል።

የናይጄሪያ የሴቶች ጉዳይ ሚንስትሯ ፖውሊን ታለን፤ በእንቅስቃሴ ገደቡ ወቅት ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በአስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ጭምሯል ብለዋል።

"ሴቶች እና ህጻናት ከበዳዮቻቸው ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ተቆልፎባቸዋል" ብለዋል።

እ.አ.አ. 2019 ላይ ኤንኦአይ የተባለ ድርጅት ይፋ ያደረገው ጥናት እንዳሳየው፤ ከሦስት ናይጄሪያዊያን ሴቶች አንዷ 25 ዓመት እስኪሆናት ድረስ የተለያያ አይነት መልክ ካላቸው ጾታን መሰረት ካደረጉ ጥቃቶች መካከል ቢያንስ አንድ ጥቃት ይሰነዘርባታል ይላል።

በናይጄሪያ በርካታ ሪፖርት ሳይደረጉ የሚቀሩ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ይኖራሉ። ጥቃት አድራሾቹ የቤተሰብ አባል መሆናቸው፣ አድሎ እና መገለልን በመፍራት ወይም በፍርድ ሂደት ላይ ዕምነት ማጣት ብዙ ጊዜ የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው።