ተጠርጣሪዋን ከሞተር ሳይክል ጋር አስረው እንድትጎተት ያደረጉ ፖሊሶች ታሰሩ

ከሞተር ሳይክል ጋር ታስራ መሬት ላይ የተጎተተችው ሰው

የፎቶው ባለመብት, @DCI_Kenya

የምስሉ መግለጫ, ከሞተር ሳይክል ጋር ታስራ መሬት ላይ የተጎተተችው ሰው

በኬንያ የ21 ዓመቷ ተጠርጣሪ ከሞተር ሳይክል ጋር ታስራ መሬት ላይ ከተጎተተች በኋላ ሦስት የኬንያ ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

አንዱ የፖሊስ አባል ሞተር ሳይክሉን ሲያሽከረክር፣ ሌላኛው ደግሞ ወጣቷን ሲገረፍ ሦስተኛው የፖሊስ አባል ድግሞ ድርጊቱን በሞባይል ስልኩ ሲቀርጽ ነበር።

በስርቆት ወንጀል ተባባሪ ነሽ ተብላ የተጠረጠረችው ሜርሲ ቼሪኖ፤ ሶሰቱ የፖሊስ አባላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ስትማጸን ነበር።

"እንዴት በሕይወት እንደተረፍኩ አላውቅም" ስትል ጥቃቱ የደረሰባት የ21 ዓመት ወጣት ለኬንያው ስታንዳርድ ጋዜጣ ተናግራለች።

እንደ ጋዜጣው ዘገባ ከሆነ ድርጊቱ የተፈጸመው ከመዲናዋ ናይሮቢ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ኦሌንጉሩኔ ተብሎ በሚጠራ አከባቢ እሁድ ዕለት ነበር።

የአከባቢው ነዋሪዎች ጣልቃ ከገቡ በኋላ ወጣቷ ወደ ሆስፒታል ተወስዳ ህክምና እየተደረገላት ነው ተብሏል።

ፖሊስ ባደረሰባት ጥቃት አንድ እግሯ መሰበሩን እና ሌሎች ጉዳቶቸም እንደደረሱባት ተነግሯል።

በበርካታ ኬንያውን ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰው ድርጊት ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተጋርቷል። ወጣቷ ከሞተር ሳይክል ጋር ታስራ፤ ልብሷ እና የውስጥ ሱሪዋ እስከ ጉልበቷ ድረስ ወርዶ ስትጎተት ያሳያል። የተንቀሳቃሽ ምስሉ መጨረሻ በበርካታ ሰዎች ተከባ ያሳያል።

"ምሕረት እንዲያደርጉልኝ ስማጸን ነበር። ማናቸውም ግን ሊሰሙኝ አልፈቀዱም" ስትል ለስታንዳርድ ጋዜጣ ከሆስፒታል አልጋ ላይ ሆና ተናግራለች። "ይህ ሁሉ ሲፈጸምብኝ ምክንያቱን አላውቅም" ስትል ሜርሲ ጨምራ ተናግራለች።

ሲቲዝን የተባለው ቴሌቪዥን እንደዘገበው ደግሞ፤ ሜርሲ ከአንድ የፖሊስ ባልደረባ መኖሪያ ቤት ንብረት የዘረፉ ወጣቶች ተባባሪ ነሽ የሚል ክስ ቀርቦባታል።

Presentational grey line

የናኩሩ ግዛት አስተዳዳሪ የፖሊሶቹ ተግባር ተቀባይነት የሌለው እና የማንታገሰው ነው ብለዋል። የኬንያ የወንጀል ምርመራ ክፍል በበኩሉ ሦስቱ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውሶ፤ በፖሊስ አባላቶቹ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ስለመሆኑ ተጠቁሟል።

የኬንያ ፖሊስ በተለይ ደግሞ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተጣሉ ክልከላዎችን ሲያስፈጽም በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥስተ ይፈጽማል ተብሎ ይወቀሳል።

ባሳለፍነው ሳምንት ፖሊስ መንግሥት የጣለውን ሰዓት እላፊ ሲያስፈጽም 15 ሰዎችን ገድሏል ሲል አንድ ገለልተኛ የሆነ ተቋም አስታውቋል።