የጀርመኑ አየር መንገድ ሉፍታንዛ 22 ሺህ ሠራተኞቹን ሊቀንስ ነው

የፎቶው ባለመብት, DeFodi Images / Getty Images
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ምክንያት ኪሳራ ያጋጠመው የጀመርኑ ሉፍታንዛ አየር መንገድ 22ሺህ ሠራተኞቹን ሊቀንስ መሆኑን አስታወቀ።
ሉፍታንዛ ከሚቀንሳቸው ሠራተኞቹ ገሚሱ ጀርመን የሚገኙ ናቸው።
አየር መንገዱ ባስቀመጠው ግምት ከወረርሽኙ በኋላ የበረራው ኢንዱስትሪ ለማገገም ረዥም ጊዜ ይወስድበታል። በዚህም አየር መንገዱ እስከ 100 አውሮፕላኖቹን ሊያጣ ይችላል።
ኩባንያው ይህን እርምጃ መውሰድ ያስፈለገው፤ የኩባንያውን ሥራ ለማስቀጠል እና በተቻለ መጠን የበርካታ ሰዎችን ስራ ለማስቀጠል ነው ተብሏል።
ኩባንያው ከ135ሺህ በላይ ሠራኞች ያሉት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ግማሽ ያክሉ የሚገኙት በጀርመን ነው።
ባሳለፍነው ዓመት ሉፍታንዛ ኩባንያውን ለመታደግ ከጀመርን መንግሥት 9 ቢሊዮን ዩሮ መቀበሉ ይታወሳል። በዚህም የጀርመን መንግሥት የኩባንያው የ20 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል።
ይህ የጀመርን መንግሥት እና የሉፍታንዛ ስምምነት በአውሮፓውያን ኮሚሽን እና በኩባንያው የድርሻ ባለቤቶች ፍቃድ ማግኘት ይኖርበታል።
ሉፍታንዛ የቫይረሱ ስርጭት ባስከተለበት ኪሳራ ጀርመን ዊንግስ የተባለውን ርካሽ አየር መንገዱን ለመዝጋት ተገዷል።
ከሉፍታንዛ በተጨማሪ በርካታ አየር መንገዶች ሠራተኞቻቸውን ለመቀነስ ተገደዋል። ከእነዚህም መካከል ብሪቲሽ ኤርዌይስ ከ12ሺህ እስከ 45ሺህ ሠራተኞቹን ለማሰናበት አማራጮቹን እያጤነ መሆኑ ተነግሯል።
ራይንኤር በበኩሉ ወደ 3ሺህ የሚሆኑ ሠራተኞቹን ለመቀነስ ዝግጅቱን አጠናቋል። የአየር መንገዱ ኃላፊዎች እንዳሉት ከሆነ አየር መንገዱ ከገበያው ሳይወጣ ለመቆየት የሚፈልገው 15 በመቶ የሚሆኑ ሠራተኞቹን ብቻ ነው።
ኢዚ ጄት በበኩሉ 30 በመቶ የሚሆኑ ሠራተኞቹን ይቀንሳል። ይህም 4500 ሠራተኞች ገደማ ማለት ነው። 10ሺህ ሠራተኞች ያሉት ቨርጅን አትላንቲክ በበኩሉ 3ሺህ ሠራተኞቹን እንደሚያሰናብት አስታውቋል።













