በወጣቷ ጥያቄ የአሜሪካ ትልቁ መዝገበ ቃላት የ"ዘረኝነት" ትርጉምን ሊያሻሽል ነው

ኬኔዲ ሚችሀም

የፎቶው ባለመብት, KENNEDY MITCHUM

የምስሉ መግለጫ, ኬኔዲ ሚችሀም

የአሜሪካው ሜሪየም ዌብስተር መዝገበ ቃላት እንደ ኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ሁሉ ታዋቂና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ነው።

አንዲት ወጣት ጥቁር አሜሪካዊት ታዲያ ለዚህ መዝገበ ቃላት አሳታሚ በጻፈቸው ደብዳቤ ምክንያት መዝገበ ቃላቱ ዘረኝነት ወይም (racism) ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የትርጉም ፍቺ ማሻሻያ ለማድረግ ወስኗል።

ለቃሉ ትርጉም ፍቺ መሻሻል ምክንያት የሆነችው ወጣት ኬኔዲ ሚችሀም ትባላለች። 22 ዓመቷ ሲሆን ከአዮዋ ግዛት ደሬክ ዩኒቨርስቲ ገና መመረቋ ነው።

ያደገችው በፈርጉሰን ሚዙሪ ሲሆን፤ ይህ አካባቢ ደግሞ በጸረ ዘረኝነት ትግል ላይ ብዙ ታሪክ ያለው ቦታ ነው። ምናልባት አስተዳደጓና ያደገችበት ሰፈር ስለ ዘረኝነት ብዙ እንድታውጠነጥን ሳያደርጋት አልቀረም።

ወጣቷ ሚችሀም ለአሳታሚዎቹ በጻፈችው ደብዳቤ ዘረኝነት ለሚለው ቃል የተሰጠው ትርጉም "አንድ የጎደለው ነገር አለ" ስትል አስገንዝባለች። ይህም 'መዋቅራዊ ዘረኝነት' የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ መግደፉ ነው።

አንድ በድርጅቱ በአርታኢነት በከፍተኛ ኃላፊነት የሚሰሩ ሰው ልጅቱ ያነሳቸው ነጥብ መሠረታዊ በመሆኑ ማሻሻያው ይደረጋል ብለዋል። የመዝገበ ቃላቱ አሰናጆችም ይህንኑ አረጋግጠዋል።

አሳታሚው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በአሜሪካ ሜኔሶታ ግዛት፣ በሚኒያፖሊስ ከተማ ባለፈው ወር ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ ጥቁር በአንድ ነጭ ፖሊስ የተፈጸመበት አሰቃቂ ግድያን ተከትሎ ተቃውሞ በመቀጣጠሉ ነው።

ሚችሀም ለዚህ ያነሳሳት ዘረኝነትን በተለየ መንገድ ስትመለከትና ሰዎች ዘረኛ ስለመሆናቸው ስትነግራቸው ወደ መዝገበ ቃላቱ በመሄድ እንዴት ዘረኛ እንዳልሆኑ ሊያስረዷት እየሞከሩ ስላስቸገሯት ነው።

ከእነዚህ አጋጣሚዎች በኋላ ሚችሀም የመዝገበ ቃላቱ አሰናጆች ለዘረኝነት ሰፋ ያለ ትርጉም ሊሰጡት እንደሚገባ በማመኗ ደብዳቤውን ለመጻፍ ተነሳስታለች።

አሁን ለጊዜው ዘረኝነት በሜርየም ዌብስተር መዝገበ ቃላት ሦስት ትርጉሞች ብቻ ተሰጥቶት ይገኛል፤

1ኛ. ዘረኝነት ማለት አንድ ማኅበረሰብ በቆዳ ቀለሙ የበላይ ነው፤ አንዱ ከሌላው ይበልጣል ብሎ ማሰብ

2ኛ. ዘርን መሰረት ባደረገ ሁኔታ የተቋቋመ የፖለቲካ ፕሮግራም ወይም አስተሳሰቡን በዚሁ በዘር ልዩነት ላይ መሰረት አድርጎ ማደራጀት

3ኛ. የዘር ልዩነት እና መድልዎ ናቸው

ሚችሀም ለቢቢሲ እንደተናገረቸው ከላይ የተዘረዘሩት የቃሉ ብያኔዎች ያላካተቷቸው ሕያው የዘረኝነት ልማዶችና ከሃይል አሰላለፍ ጋር ያለውን ቁርኝቶች አሉ። ይህንንም ያስተዋለችው ከዛሬ አራት ዓመት በፊት እንደሆነ ሚችሀም ለቢቢሲ ተናግራለች።

"በማኅበራዊ ሚዲያ ገጼ ላይ ሰዎች ስለ ዘረኝነት ሀሳባቸውን እንዲያጋሩኝ ጠይቄ ነበር፤ እኔ በኮሌጅም ይሁን በዩኒቨርስቲ የሚደርስብኝን ዘርን መሰረት ያደረገ ረቂቅ መድልዎ እምብዛምም የሚያስተውለው የለም" ብላለች።

ይህን ረቂቅ ዘረኝነት ጉዳይ ስታነሳ ግን ሰዎች ቶሎ ብለው መዝገበ ቃላቱን በማንሳት እሷ እንደተሳሳተች ሊያሳምኗት ሲሞክሩ ቆይተዋል።

አንዳንድ ሰዎች "ስለ ዘረኝነት ምንም የምታውቂው ነገር የለም፤ ዝም ብለሽ አትዘባርቂ" እያሉ ሲያንቋሽሹኝ ነበር ብላለች ሚችሀም።

አንዳንዶች በተለይ የዚህን መዝገበ ቃላት ትርጓሜን እየቀዱ በእኔ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ በመለጠፍ አንዱ ዘር ከሌላው ይበልጣል ብለው እስካላመኑ ድረስ በፍጹም ዘረኛ ሊባሉ እንደማይገባ ይሟገቷት ነበር።

አንዳንዶችማ ጭራሽ "ይኽው ጥቁር ሆነሽ ዩኒቨርስቲ ገብተሻል፤ ከእኛው እኩል ጥቅሞችሽ ተከብረውልሻል፤ ምን ይሁን ነው የምትይው?" ይሏት ነበር።

እሷ በበኩሏ የተሰጡኝ ዕድሎች እንዳሉ ሆነው በቆዳ ቀለሜ ምክንያት ብቻ ከፊቴ የሚደነቀሩብኝን መሰናክሎች ሰዎች ሊያይዋቸው አልቻሉም ትላለች። ሊያይዋቸው ያልቻሉት ደግሞ እነዚያ መሰናክሎች በእነርሱ ሕይወት ውስጥ ስለሌሉ ነው።

በዚህም ምክንያት ነገሩን ስታብሰለስለው ቆይታ በግንቦት 28 ለመዝገበ ቃላቱ አርታኢያን ደብዳቤ ልካለች።

በዚህ ደብዳቤዋ ላይ አጽንኦት የሰጠችው ዘረኝነት ሲባል "ማኅበራዊና ተቋማዊ" ረቂቅ ቅርጽ ሊኖረው እንደሚችልና በቆዳ ቀለም የተነሳ አንዱ ለሌላው የሚሰጠው የአስተሳሰብ ብያኔም ዘረኝነት እንደሆነ አብራርታለች።

"ባልጠበቅኩት ሁኔታ ለዚህ ደብዳቤዬ በቀጣዩ ቀን ምላሽ ተላከልኝ" ትላለች ሚችሀም።

ከተከታታይ የደብዳቤ ልውውጦች በኋላ የመዝገበ ቃላት አሳታሚው ይህ ጉዳይ በአፋጣኝ ሊስተካከል እንደሚገባና የቃላት ብያኔው እርሷ እንዳለችው ሆኖ መታተም እንዳለበት ይፋ አድርጓል።

የሜሪየም ዌብስተርስ መዝገበ ቃላት የአርታኢያን ሥራ አስኪያጅ ፒተር ሶኮሎውስኪ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ማሻሻያው "ረቂቅና ተቋማዊ ዘረኝነቶችን የሚይዝ ትርጓሜ እንዲያካትት ይደረጋል። ይህን የተመለከተ አንድ ሁለት ምሳሌም አብሮ ተካትቶ ይታተማል" ብለዋል።

አዲሱን ማሻሻያ የተደረገበትን ቅጽም በነሐሴ ወር ታትሞ ይወጣል ብለዋል ሥራ አስኪያጁ።

ምንጊዜም ቢሆን "ሰዎች ዘረኝነትን በተመለከተ ያላቸው ትርጉም ተመሳሳይ ሊሆን ይገባዋል፤ መግባባት ይኖርብናል" ይላሉ ፒተር ሶኮሎዉስኪ።

ዘረኝነት የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ ወይም በገቢር የሚፈጸም ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብ ውስጥ የሚቀበር ረቂቅ መልክ እንዳለው ለዘመናት ቸል ሲባል የቆየ ጉዳይ ነው። ይህ በመዝገበ ቃላት ደረጃ መቀመጡ ሰዎች ዘረኝነትን በተቀራራቢ ትርጉም እንዲረዱት ያግዛቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።