በቺካጎ ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ በርካታ ሰዎች ሞቱ

ቺካኮ በ60 ዓመት ታሪኳ በቀን ከፍተኛ ሰዎች የሞቱበትን ቀን አስተናገደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቺካጎ ከተማ በስድሳ ዓመት ውስጥ በአንድ ቀን በርካታ ሰዎች የሞቱበትን ቀን አስተናግዳለች።

በዕለተ እሁድ ግንቦት 23 ከጆርጅ ፍሎይድ ሞት ጋር በተያያዘ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ 18 ሰዎች ተገድለዋል።

ግንቦት 22 እና 23 በተደረጉ ሰልፎች 85 ሰዎች በጥይት የተመቱ ሲሆን 24 ሰዎች ደግሞ መገደላቸውን ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቺካጎ የወንጀል ምርመራ ክፍል የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።

መረጃው እንደሚያሳያው አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች ጥቁር አሜሪካውያን ናቸው።

ቺካጎ ሰን-ታይም ጋዜጣ ይዞት የወጣው ዘገባ እንደጠቆመው ከተገደሉት እና ጉዳት ከደረሰባቸው 24 ሰዎች መካከል ተማሪዎች፣ ወላጆች እና ሠራተኞች ይገኙበታል።

ከቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የወንጀል ምርመራ ክፍል የተገኘው መረጃ ከ1961 (እአአ) ጀምሮ ያለውን ታሪክ የያዘ እንደሆነ በማስታወስ "እንዲህ አይነት ነገር በፍጹም ተመልክተን አናውቅም" ሲሉ ተመራማሪው ማክስ ካፑስቲን ለቺካኮ ሰን-ታይመስ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በቺካጎ ከተማ ታሪክ በአንድ ቀን ውስጥ በርካታ ሰዎች የሞቱት 13 ሰዎች ሲሆኑ ዕለቱም ሐምሰሌ 23/1983 ዓ.ም. ነበር።

የቺካጎ ከንቲባ ሎሪ ላይትፉት እንዳሉት 18 ሰዎች ተገድለዋል በተባለበት ቀን ለፖሊስ የተደረገው የድረሱልኝ ጥሪ ከ65 ሺህ በላይ ነበር። ይህም በአማካይ ለከተማው ፖሊስ ከሚደርሰው ጥሪ በ50 ሺህ የሚበልጥ ነው።

የቺካጎ ከተማ ፖሊስ ለሰን-ታይምስ እንደተናገረው፤ ግንቦት 22 እና 23 ለፖሊስ በርካታ ጥሪዎች መደረጋቸውን በማስታወስ፤ በዜጎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን እና መነሻዎችን እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።

"በአመጹ ህይወታቸውን ላጡ እና ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ፍትህ ለመስጠት እንሰራለን" ብሏል የከተማዋ ፖሊስ።

ቺካጎ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ይመዘግብባት የነበረው የግድያ ወንጀል ከፍ ያለ ነው። ቺካጎ ከሁለቱ የአሜሪካ ግዙፍ ከተሞች በላይ ብዙ የግድያ ወንጀሎች ተመዝግበውባታል።

እአአ 2018 በቺካጎ 561 ሰዎች በሌላ ሰው የተገደሉ ሲሆን ይህም በተመሳሳይ ዓመት በኒው ዮርክ እና ሎስ አንጀለስ ከተሞች ከተመዘገበው የግድያ ወንጀል ድምር በላይ ነው።